ፈልግ

በኢንዶኔዥያ መዲና ጃካርታ አጠገብ ለአጠገብ የሚገኙ የክርስትና እና የእስልምና ሃማኖቶች የማምለኪያ ቦታዎች በኢንዶኔዥያ መዲና ጃካርታ አጠገብ ለአጠገብ የሚገኙ የክርስትና እና የእስልምና ሃማኖቶች የማምለኪያ ቦታዎች  

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ፥ የእስያ ካቶሊካዊት ቤተ ክርስቲያን ኅብረትን እንድትገነባ አሳሰቡ

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ በኢንዶኔዥያ መዲና ጃካርታ ውስጥ ከሐምሌ 13-19/2018 ዓ. ም. ድረስ ለሚካሄደው 12ኛው የእስያ ብጹዓን ጳጳሳት ጉባኤ ፌዴሬሽን (FABC) ስብሰባ መልዕክት ልከዋል። የጉባኤው ልዩ መልዕክተኛ አድርገው ለሾሟቸው ብጹዕ ካርዲናል ኦስዋልድ ግራሲያስ በጻፉት መልዕክት፥ በእስያ የምትገኘው ካቶሊካዊት ቤተ ክርስቲያን የጊዜውን ሁኔታ ለማስተካከል በምታደርገው ጥረት ሳትፈራ በተግባሮቿ እና በውሳኔዎቿ መካከል እግዚአብሔርን እንድታስቀድም አሳስበዋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ በቅርቡ ይፋ ባደረጉት፥ “ማግኒፊካ ሂውማኒታስ” ወይም የሰብዓዊነት ታላቅነት በሚለው ሐዋርያዊ መልዕክታቸው ቁ. 16 ላይ፥ “መፍረሻቸው የተቃረቡ ‘ማማዎች’ ጌቶች ሳትሆኑ ኅብረትን የምትገነቡ እና የሚመጣው የእግዚአብሔር መንግሥት አገልጋዮች እንድትሆኑ” የሚለውን በመጥቀስ ጥሪያቸውን አቅርበዋል።

ቅዱስነታቸው ይህን ጥሪ ያቀረቡት በኢንዶኔዥያ መዲና ጃካርታ ከሐምሌ 13-19/2018 ዓ. ም. ድረስ ለሚካሄደው 12ኛው የእስያ ብጹዓን ጳጳሳት ጉባኤዎች ፌዴሬሽን ጠቅላላ ስብሰባ ልዩ መልዕክተኛ አድርገው ለሾሟቸው የቀድሞው የቦምቤይ ከተማ ሊቀ ጳጳስ ለነበሩት ብጹዕ ካርዲናል ኦስዋልድ ግራሲያስ በላኩት መልዕክት ነው።

በላቲን ቋንቋ በጻፉት መልዕክታቸው ምዕመናኑ እና ወንድም ብጹዓን ጳጳሳት በመተባበር የጊዜውን ሁኔታ ለመለወጥ በሚያደርጉት ጥረት ሳይፈሩ በእስያ የምትገኝ ካቶሊካዊት ቤተ ክርስቲያን እምነትን እና ሰብዓዊነትን በዘላቂነት ለማሳደግ በምታደርገው ተስፋ ላይ እንድትጸና አበረታተዋል።

ድሆችን፣ ስደተኞችን እና ሕሙማንን እንደ ‘ማዕዘን ድንጋይ’ መመልከት

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ የቤተ ክርስቲያን ማኅበረሰብ የጋራ ቁርጠኝነትን መሠረት በማድረግ መዝ. 85 ጠቅሰው በጻፉት ሐዋርያዊ ሠነዳቸው፥ የተናቁት ድሆች፣ ሕሙማን፣ ስደተኞች እና ዝቅተኞች ‘የማዕዘን ድንጋይ’ ይሆናሉ፤ ‘በምድር ላይ ፍቅር እና እውነት የሚገናኙበት፣ ፍትህ እና ሰላም የሚተቃቀፉበት’ ጠንካራ እና እንግዳ ተቀባይ የሆነ የጋራ ቤትን ይገነባሉ” ሲሉ አስረድተዋል።

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ በሐዋርያዊ የእረኝነት እና የአባትነት ልብ ለእስያ ብጹዓን ጳጳሳት ጉባኤዎች በጻፉት መልዕክት፥ የፈረሰውን የባቢሎን ግንብ የሚመስል ከመገንባት ይልቅ መሠረቱ ጠንካራ እና መልካም የሆነውን በመገንባት እንዲተባበሩ፣ የሰው ልጅ ውበቱን እንዳያጣ እና ዓለምም እግዚአብሔር በእያንዳንዱ የሰው ልብ ውስጥ መኖሪያው ሊያደርግ የሚፈልገውን ቦታ እንደገና እንዲያውቅ” በማለት ጥሪያቸውን አቅርበዋል።

የብፁዕ ካርዲናል ዶ ሮሳሪዮ ፌርራኦ ጥያቄ

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ ሰኔ 17/2018 ዓ. ም. በጻፉት መልዕክታቸው ላይ፥ “የርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ቋሚ መልዕክተኛ እንዲሾም” በማለት የጎዋ እና ዳማኦ ሜትሮፖሊታን ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ ካርዲናል ፊሊፔ ኔሪ አንቶኒዮ ሴባስቲአኦ ዶ ሮሳሪዮ ፌርራኦ ያቀረቡትን ጥያቄ አስታውሰዋል። በመጨረሻም ለሐዋርያዊ ወንድሞቻቸው ለሆኑት ብጹዓን ጳጳሳት በሙሉ የእመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም እና የቅዱስ ዮሴፍ ፍቅራዊ ጥበቃን ተመኝተውላቸዋል።

 

14 Jul 2026, 10:50