ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ፥ “እግዚአብሔር በእኛ ላይ ያለውን እምነት አያቋርጥም” ሲሉ ገለጹ
ክቡራት እና ክቡራን የዝግጅቶቻችን ተከታታዮች፥ ከዚህ ቀጥሎ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ ለምዕመናኑ ያሰሙትን ቃለ-ምዕዳን ትርጉም ሙሉ ይዘቱን እንደሚከተለው እናቀርብላችኋለን፥
የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን
“ውድ ወንድሞች እና እህቶች፣ መልካም እሁድ ይሁንላችሁ! በዛሬው መስዋዕተ ቅዳሴያችን ከማቴ. 13: 1-23 ተወስዶ የተነበበው የወንጌል ክፍል የዘሪውን ምሳሌ ያቀርብልናል። ይህም እግዚአብሔር ቃሉን በልባችን ውስጥ የሚዘራበትን ልግስና እና እምነት ይገልጻል።
ቃል ሥጋ የሆነው እና ሕይወቱን ለድነታችን ሲል አሳልፎ የሰጠው ኢየሱስ ክርስቶስ በመሞቱ ምክንያት ብዙ ፍሬ እንዲያፈራ እግዚአብሔር በዓለም ሁሉ የሚዘራው ዘር ነው (ዮሐ 12፡24)። አንዳንድ ጊዜ እግዚአብሔር በእኛ ውስጥ ደረቅ እና ምንም የማያበቅል አፈር፣ በሌላ ጊዜ ደግሞ ያልተደላደለ እና ድንጋያማ መሬት ወይም እሾሃማ ቁጥቋጦዎች ያሉበት የተለያየ አፈር እንደሚያገኝ እውነት ነው። ሆኖም ግን የሚያበቅል እና ለም መሬት የሚያገኝባቸው ጊዜያትም አሉ። ከዚያም ሁሉንም ነገር የመለወጥ ኃይል ያላቸው የፍቅር ተአምራት መታየት ይጀመራሉ። እኛ ራሳችን በሕይወታችን ውስጥ እንዳጋጠመን ጥርጥር የለውም። በዚህ ምክንያት እግዚአብሔር መዝራትን አያቋርጥም። ምክንያቱም የፍቅሩ ኃይል ከድክመታችን የበለጠ ጠንካራ መሆኑን ያውቃል (2ኛ ቆሮ 12፡9-10)።
ቅዱስ ዮሐንስ ክሪዞስቶም በዘር ምሳሌ የቀረበውን የእግዚአብሔር ቃል ሲጠቅስ፥ ‘በእሾህ መካከል፣ በድንጋያማ መሬት ወይም በመንገድ ላይ መዝራት እንዴት ይችላል? በዘር እና በአፈር ረገድ የሚሆን አይደለም። ነገር ግን በነፍሳት እና በአስተምህሮ ረገድ ሙሉ በሙሉ ሊሆን የሚችል ነው’ (በማቴዎስ ወንጌል በማሰላሰል የቀረበ ስብከት 44:5)። ምክንያቱም በእግዚአብሔር እጅ ድንጋያማው መሬት ወደ ለም አፈር ሊለወጥ ይችላል። መንገድም በሰዎች እግር እንዳይረገጥ ወይም ለአላፊው አግዳሚው ሁሉ እንዳይጋለጥ፣ ለም አፈር እንዲሆን፤ እሾሁ ተነቅሎ እና ዘሩም ከጥፋት ተጠብቆ ማደግ ይችላል።
እግዚአብሔር ለእኛ ያለው ልግስና ሞኝነት ሳይሆን ጥበብ ነው። አንዳንድ ጊዜ እኛ ራሳችን ማወቅ የማንችለውን መልካም ነገር በውስጣችን እንዳለ ይመለከታል። በዚህ ምክንያት ልባችንን ከእኛ በተሻለ የሚያውቀው እግዚአብሔር፥ ራሳችንን በእምነት ለእሱ በአደራ ከሰጠን በእኛ ላይ ያለውን እምነት አያቋርጥም።
ስለዚህ ዘሩ በትሕትና እና በግልጽነት ከሚገኝ ልግስና እና እምነት የሚዘራ ከሆነ የመንፈስ ቅዱስ ፍሬዎች በውስጣችን ይበቅላሉ ያድጋሉ። ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ፥ ‘ፍቅር፣ ደስታ፣ ሰላም፣ ትዕግሥት፣ ቸርነት፣ በጎነት፣ ታማኝነት፣ ገርነት፣ ራስን መግዛት’ እንደሆኑ ያስተምራል (ገላ 5:22)። ዓለማችን በእነዚህ ፍሬዎች ምን ያህል መሞላት እና መለወጥ እንደሚያፈልገው ያስተምራል
ስለዚህ በተለይም በእነዚህ የበጋ የዕረፍት ቀናት የእግዚአብሔርን ቃል ለማዳመጥ፣ ለማንበብ እና ለማሰላሰል ጊዜን እንፈልግ። ከዚህ ጤናማ የዕረፍት እና የመዝናኛ ጊዜ ጋር ትርጉም ያለውን የጽሞና እና የጸሎት ጊዜዎችን ማሳደግ እንችላለን። በዚህ መንገድ ወደ ተለመደው የአካል እና የመንፈስ መታደስ ተግባሮቻችን እንመለሳለን። ወንጌልን ለማወጅ እና ለእግዚአብሔር መንግሥት መስፋፋት አስተዋጽኦ ለማድረግ ዝግጁ እንሆናለን።
በዚህም የሐዋርያት ንግሥት እና የወንጌል ብርሃን የሆነች እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ትረዳን።” በማለት ቃለ-ምዕዳናቸውን ድምድመዋል።
