ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ፥ የጦርነት አዝማሚያ የሰላም ተስፋን ማጨለም የለበትም ሲሉ አሳሰቡ
የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን
የባሕር ቀን ታስቦ በዋለበት እሁድ ሐምሌ 5/2018 ዓ. ም. በወታደራዊ ውጥረት ምክንያት የሥራ ሁኔታቸው የበለጠ አስቸጋሪ ለሆነባቸው የባሕር ላይ ተጓዦች እና የወደብ ላይ ሠራተኞች ያላቸውን ቅርበት ገልጸው፥ በመጨረሻም የፖላንድ ምዕመናን የእመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ቤተ መቅደስ ወደሚገኝበት ጃስና ጎራ ያደረጉትን ዓመታዊ መንፈሳዊ ንግደት አስታውሰዋል።
ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ በካስቴል ጋንዶልፎ የበጋ ጊዜ ቆይታቸው የመጀመሪያ እሁድ ከሐዋርያዊ ሕንጻቸው ፊት ለፊት ከተሰበሰቡት ምዕመናን ጋር የመልአከ እግዚአብሔር ጸሎት ካደረሱ በኋላ፥ ጦርነት በሚካሄድባቸው በርካታ የዓለማችን ክልሎች ከፍተኛ ስቃይ የሚደርስባቸውን ሲቪሎች አስታውሰዋል።
በተለይ በአሜሪካ እና በኢራን መካከል ስምምነት ሊመጣ እንደሚችል ተስፋ የተጣለበት ድርድር ከተደናቀፈ በኋላ በመካከለኛው ምሥራቅ እና በሊባኖስ ውስጥ እንደገና የተከሰተውን ውጥረት ጠቅሰው፥ እንዲሁም በቅርብ ቀናት ውስጥ በሩሲያ እና በዩክሬን መካከል በተካሄደው ጦርነት በካርኪፍ፣ በዲኒፕሮ፣ በኪየቭ እና በኦዴሳ ላይ የተፈጸመው ከፍተኛ ጥቃት በማስታወስ ስጋቸውን ገልጸዋል።
ርዕሠ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ በንግግራቸው፥ አለመታደል ሆኖ የጦርነት አዝማሚያዎች በመካከለኛው ምሥራቅ፣ በዩክሬን እና በሌሎች በርካታ የዓለም ክፍሎች እንደገና ይታያሉ” ብለው፥ ዓመፅ፣ ሽብር እና ሞት በርካታ ንፁሃን ሰዎችን እንደገና እያጠቋቸው እንደሚገኝ ተናግረው፥ ሰዎች ተስፋቸውን እንዳይቆርጡ በማበረታት በአገራት መካከል ዘላቂ እርቅን ሊያመጣ ወደሚያስችል ብቸኛው የውይይት እና የድርድር መንገድ እንዲመለሱ አሳስበዋል።
የጦርነት ነፋስ ደካማ እና ብልጭ ድርግም የሚለውን የተስፋ እና የሰላም ነበልባል እንዲያጠፋ መፍቀድ እንደማይገባ አሳስበው፥ ጦርነት የሚካሄድባቸው አገራት በውይይት፣ እርስ በርስ በመገናኘት እና በዲፕሎማሲ መንገድ እንደሚጸኑ ያላቸውን ተስፋ ገልጸው፥ ወደ ፍትሃዊ እና ዘላቂ ሰላም ሊመራቸው የሚችል ብቸኛው መንገድ ይህ እንደሆነ እና በሕዝቦች መካከል እርቅ፣ የጋራ ደህንነት እና ለእያንዳንዱ ሰው ክብር እንዲኖር ሊያደርግ እንደሚችል አስረድተዋል።
የባሕር ላይ ተጓዦችን በጸሎት ማስታወስ
በተለምዶ በሐምሌ ወር ሁለተኛ እሁድ በሚከበረው የባሕር እሁድ፥ ካቶሊካዊት ቤተ ክርስቲያን በባሕር ላይ የሚኖሩትን እና የሚሠሩትን በጸሎታቸው እንዲያስታውሷቸው ምእመናንን በሙሉ የምትጋብዝበት ቀን እንደሆነ ታውቋል።
ወደ 90 በመቶ የሚሆነውን የዓለም ንግድ በሚደግፍ የኢንዱስትሪ አስፈላጊነት ላይ ያሰላሰሉት ቅዱስነታቸው፥ በጦርነቱ ምክንያት በባሕር ላይ የሚጓዙትን እና የሚሠሩ ሰዎችን በሚያጋጥማቸው አስቸጋሪ ሁኔታዎች ላይ ያላቸውን ስጋት ገልጸዋል።
