ር. ሊ. ጳ. ሊዮ 14ኛ፥ የሄይቲ ታጋቾች እንዲፈቱ እና ለኔፓል ሕዝብ ዕርዳታ እንዲደረግለት አሳሰቡ
የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን
በሄይቲ ኬንስኮፍ የተፈጸመውን ጭፍጨፋ አስከፊነት የሚገልጹ ዘገባዎችን ያስታወሱት ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ፥ በዚህ ጭፍጨፋ በርካታ ሰዎች ሕይወታቸውን እንዳጡ እና ሌሎች ደግሞ መታገታቸውን አስታውሰዋል። ቅዱስነታቸው ተጎጂዎቹን እና ቤተሰቦቻቸውን በጸሎታቸው አስታውሰው፥ ሁሉም ታጋቾች ቶሎ እንዲፈቱ ጠይቀው፥ የሕዝቡን ደህንነት ለማረጋገጥ እና ማንኛውንም ዓይነት ዓመፅ ለማስቆም ተጨባጭ ቁርጠኝነት እንዲኖር ኃላፊነት ለሚሰማቸው በሙሉ ልባዊ ጥሪያቸውን አቅርበዋል።
ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ ቅዳሜ ምሽት በአልባኖ ሐይቅ ዳርቻ በምትገኝ የእመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ቤተ ክርስቲያን የተካሄደውን ዑደት ከተሳተፉ በኋላ በነጋታው እሑድ እኩለ ቀን ላይ ከምዕመናን ጋር የመልአከ እግዚአብሔር ጸሎት ካደረሱ በኋላ ባደረጉት ንግግር ጥሪያቸውን አቅርበዋል።
የኔፓል እና የቲቤት ሕዝቦች ስቃይን ማቃለል
ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ ሄይቲ ውስጥ የታገቱት ሰዎች እንዲፈቱ ጥሪ ካቀረቡ በኋላ በኔፓል እና በቲቤት በደረሰው አውዳሚ የጎርፍ አደጋ ምክንያት የሞቱትን፣ የተጎዱትን እና የጠፉትን እንዲሁም ቤተሰቦቻቸውንም ጭምር በጸሎታቸው አስታውሰው፥ በአደጋው ወቅት ምላሽ በመስጠት የተሳተፉ የነፍስ አድን ሠራተኞችን ምእመናን በጸሎታቸው እንዲያስታውሷቸው አደራ ብለዋል።
“የሁሉም ሰው ቁርጠኝነት ስቃይን ለማስታገስ እና ለተጎዱት ሕዝቦች አስፈላጊውን ዕርዳታ ለማምጣት እንዲያግዝ” ሲሉ ጸሎታቸውን አቅርበዋል።
ቫቲካን ቅዳሜ ነሐሴ 23/2018 ዓ. ም. ባወጣው መግለጫ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ በበጎ አድራጎት አገልግሎት ጽሕፈት ቤት በኩል በአደጋው ለተጎዱት ሰዎች አስቸኳይ የገንዘብ ድጋፍ ለካሪታስ ኔፓል መላካቸውን አስታውቋል።
ከ700 በላይ ሰዎች ሲሞቱ በሺዎች የሚቆጠሩ ተፈናቅለዋል
በኔፓል ከሚገኝ የቅድስት መንበር ሐዋርያዊ እንደራሴ ጽሕፈት ቤት ጋር በመተባበር የርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ዕርዳታ ካሪታስ ኔፓልን እንደሚደግፍ ታውቋል። እነዚህ ዕርዳታዎች የተጀመሩት ከአደጋው በኋላ ባሉት የመጀመሪያዎቹ ሰዓታት ውስጥ ሲሆን፥ ዕርዳታው በአደጋው ምክንያት ሁሉንም ነገር ላጡ ሰዎች ምግብ፣ መሠረታዊ ፍላጎቶችን እና መጠለያ መስጠትን እንደሚያካትት ታውቋል።
በአደጋው በተጎዱት ክልሎች ውስጥ የሟቾች ቁጥር እየጨመረ የመጣ ሲሆን፥ የዕርዳታ ሥራም መቀጠሉ ተነግሯል። በኔፓል እና በቲቤት ውስጥ የሞቱት ሰዎች ቁጥር ከ700 በላይ መሆኑ ሲነገር ቢያንስ 3,000 ሰዎች እንደጠፉ ተዘግቧል።
ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ ሐሙስ ነሐሴ 21/2018 ዓ. ም. በቅድስት መንበር ዋና ጸሐፊ ብጹዕ ካርዲናል ፒዬትሮ ፓሮሊን በኩል በላኩት የቴሌግራም መልዕክት በደረሰው የሕይወት መጥፋት እና የንብረት ውድመት የተሰማቸውን ሐዘን ገልጸው፥ ለሞቱት ነፍሳት የእግዚአብሔር ምሕረት በመለመን ላዘኑትም መጽናናትን ተመኝተውላቸዋል።
በአደጋው ለተጎዱት ያላቸውን መንፈሳዊ ቅርበት አረጋግጠው፥ በፍለጋ እና በነፍስ ማዳን ሥራ ላይ የተሳተፉትን የአደጋ ጊዜ ሠራተኞችን በጸሎታቸው አስታውሰዋል።
ለሰላም የቀረበ አዲስ ጥሪ
ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ በመቀጠልም ምእመናን ለሰላም መጸለያቸውን እንዲቀጥሉ አሳስበው፥መታሰቢያ በተከበረበት ነሐሴ 22/2018 ዓ. ም. የቅዱስ አጎስጢኖስን ቃል አስታውሰዋል።
“የቅዱስ አጎስጢኖስ የሰላም ምስል በደቀ መዛሙርቱ እጅ እየጨመረ የመጣው እና ሲያከፋፍሉት የነበረው የተአምር እንጀራ ነው” ሲሉ አስታውሰው፥ “በዓለም ሁሉ ላይ የሰላምን እንጀራ በድፍረት የሚሰብሩ እና የሚያከፋፍሉ፣ መለያየትን በማሸነፍ ፍትህን የሚያበረታቱ እና ለጋራ ጥቅም ሲሉ ይቅርታን የሚያደርጉ ሰዎች ቁጥር እንዲጨምር” በማለት ጸሎታቸውን አቅርበዋል።
ስለ ፍጥረት የሚቀርብ ጸሎት
ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ በመጨረሻም፥ ነሐሴ 26 ቀን ቤተ ክርስቲያን የፍጥረት እንክብካቤ በማስመልከት ዓለም አቀፍ የጸሎት ቀንን እንደምታከብር አስታው፥ ዕለቱ የፍጥረት ወቅት መጀመሪያ መሆኑን እና በተለያዩ ቤተ እምነቶች ውስጥ የሚገኙት ምዕመናን ዘንድሮ ዕለቱን “ሕያው ውሃ’ በሚል ጭብጥ እንደሚያከብሩት አስረድተዋል።
ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ ዕለቱን በማስመልከት በላኩት መልዕክት “ለጋራ መኖሪያ ምድራችን እንክብካቤን ማድረግ የልብ መለወጥን ይጠይቃል፤ ጥፋት ለማድረስ የተጠቀሙበት ነገርም ወደ ሕይወት ይመራል” ሲሉ ማስታወሳቸውን ተናግረዋል።
ቅዱስነታቸው በመጨረሻም፥ “ሕያው የሰላም ውሃ መተላለፊያዎች እና የቆሰለውን ዓለማችን የሚያድስ የእግዚአብሔር ሰላም የሕይወት ውሃ መተላለፊያዎች እንድንሆን ሁሉም ሰው በጸሎት እና በተግባር እንዲተባበር እጋብዛለሁ” ሲሉ ንግግራቸውን ደምድመዋል።
