ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ፥ “ጸሎት እና ማኅበራዊ ፍትህ የማይነጣጠሉ ናቸው” ሲሉ አስገነዘቡ
የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን
ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ ዓርብ ነሐሴ 22/2018 ዓ. ም. ከዩናይትድ ስቴትስ ከመጡ የቅዱስ ቪንሰንት ደ ፖል ማኅበር ልዑካን ቡድን ጋር በቫቲካን ተገናኝተዋል።
እንደ ጎርጎሮሳውያኑ በ1833 ዓ. ም. የተመሠረተው ይህ ዓለም አቀፍ ማኅበር አባላቱ ለድሆች በግል በሚያቀርቡት አገልግሎት እንዲቀደሱ የሚፈል እና የሌሎች ካቶሊካዊ የቅዱስ ቪንሰንት ደ ፖል ማኅበራት ቤተሰብ አካል እንደሆነ ይታወቃል።
ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ በንግግራቸው፥ ማኅበሩ በመላው አሜሪካ ለሚገኙት ወንድሞቹ እና እህቶቹ ላደረገው ድጋፍ የቡድኑን አባላት አመስግነዋል።
“እግዚአብሔር የሰጣችሁን ስጦታና ተሰጥኦ በነፃ በማቅረባችሁ የእግዚአብሔርን መንግሥት ለመገንባት በአገልግሎት ላይ ባላችሁ እምነት ግልጽ ምስክርነትን ትሰጣላችሁ” ብለዋል።
ቅዱስነታቸው አባላቱ አገልግሎታቸው ወደሚያስፈልጋቸው ሰዎች እንዲያመራ ከኢየሱስ ክርስቶስ ጋር ያላቸውን ግንኙነት እንዲያጠናክሩ አደራ ብለዋል።
“ቅዱስ ቪንሰንት ደ ፖል፥ ጸሎት እና ማኅበራዊ ፍትህ እርስ በርስ የሚደጋገፉ ብቻ ሳይሆኑ የማይነጣጠሉ መሆናቸውን ጭምር አሳይቷል” ብለው፥ መንፈሳዊ ልጆቹ ምሳሌውን እንዲከተሉ አሳስበዋል።
ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ የቅዱስ አጎስጢኖስን ትምህርት በመጥቀስ፥ ድሆችን ማስታወስ በኢየሱስ ክርስቶስ ላይ የተመሠረተ መሆኑን እና እርሱን ለሚያገለግሉት ሰዎች እግዚአብሔርም ዘወትር ለጋስ ይሆናል” ሲሉ አስገንዝበዋል።
“ስለዚህ በፍቅር ተነሳስተው የተቸገሩትን ማስታወስ ችግረኞችን ብቻ ሳይሆን የደጋፊዎችን ልብ ለእግዚአብሔር ጸጋ እንደሚከፍት እናምናለን” ብለዋል።
በመሆኑም በዩናይትድ ስቴትስ የሚገኙት የቅዱስ ቪንሰንት ደ ፖል ማኅበርተኞች ጊዜያቸውን በልግስና እንዲያቀርቡ አሳስበዋል።
“በድሆች መካከል ኢየሱስ ክርስቶስን ማገልገል በእግዚአብሔር ጸጋ ልባችሁ እና አዕምሮአችሁ ሳያቋረጥ የሚጠራበት እና በባልንጀሮቻችሁ ውስጥ ኢየሱስ ክርስቶስን በቀላሉ የምታውቁበት መንገድ ነው” ብለዋል።
ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ በማጠቃለያቸው፥ ለቅዱስ ቪንሰንት ደ ፖል ማኅበር አባላት እና ለሚደግፏቸው በሙሉ ልባዊ ሰላምታቸውን አቅርበውላቸዋል።
