ፈልግ

በቫቲካን ከተማ ከቅዱስ ጴጥሮስ ባዚሊካ ግንቦች መካከል በቫቲካን ከተማ ከቅዱስ ጴጥሮስ ባዚሊካ ግንቦች መካከል  

ቅድስት መንበር የሠራተኞች አስተዳደርን ወደ ኤኮኖሚ ጉዳዮች ጽሕፈት ቤት ማዛወሯ ተነገረ

በቅድስት መንበር የኤኮኖሚ ጉዳዮች ጽሕፈት ቤት ሥራ አስፈጻሚ ክቡር አባ አንቶኒዮ ጉዌሬሮ፣ ግንቦት 24/2014 ዓ. ም. ከልዩ ልዩ የቅድስት መንበር ጽሕፈት ቤቶች መሪዎች ጋር ተገናኝተው ተወያይተዋል። ክቡር አባ አንቶኒዮ ጉዌሬሮ በውይይታቸው ለቫቲካን መንግሥት ዋና ጽሕፈት ቤት በአደራ የተሰጠው የሠራተኛው የብቃት መመዘኛ ሃላፊነት ሽግግርን በተመለከተ ማብራሪያ ሰጥተዋል። የቅድስት መንበር ሠራተኞች ሙያዊ ብቃትን ለማሳደግ ማበረታቻዎች እና ሽልማቶች ማስተዋወቅ፣ ስልጠናዎችን መስጠት፣ እቅድ ማውጣት እና የሠራተኞች ምርጫ፣ ኅብረትን ማስተዋወቅ እና ሠራተኞቹ የተቀበሉትን ተልዕኮ መወጣት እና ተሳትፎአቸውን አስመልክቶ ጥናት እየተካሄደ መሆኑን ገልጸዋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

ከእሑድ ግንቦት 28/2014 ዓ. ም. ጀምሮ በሥራ ላይ በሚውለው “ወንጌልን ስበኩ” በሚለው አዲሱ ሐዋርያዊ መመሪያ ደንብ መሠረት የቅድስት መንበር ሠራተኞች አስተዳደር ከቅድስት መንበር ዋና ጽሕፈት ቤት ወደ ኤኮኖሚ ጉዳዮች ጽሕፈት ቤት የሚዛወር መሆኑ ታውቋል። የኤኮኖሚ ጉዳዮች ጽሕፈት ቤት ሥራ አስፈጻሚ ክቡር አባ አንቶኒዮ ጉዌሬሮ አዲሱን መመሪያ በማስመልከት ለሁሉም የቅድስት መንበር ጽሕፈት ቤቶች ሃላፊዎች በላኩት መልዕክት፣ አዲስ የተቋቋመው የሰው አቅም ማስተባበሪያ እና መምሪያ ቢሮ በጽሕፈት ቤታቸው ሥር መሆኑን አስታውቀዋል።

የኤኮኖሚ ጉዳዮች ጽሕፈት ቤት ሥራ አስፈጻሚ ክቡር አባ አንቶኒዮ ጉዌሬሮ፣ የአዲሱ ዳይሬክቶሬት የሥራ ዘርፎች የትኞቹ እንደሆኑ ይፋ ባደረጉት መልዕክታቸው፣ የሥራ ስምሪት ጥራትን ለማሻሻል ይረዳቸው ዘንድ የቅድስት መንበር ልዩ ልዩ ጽሕፈት ቤቶች ሃላፊዎች ምክር እና አስተያየት ጠይቀዋል። ከሁሉ አስቀድሞ ዋና ዓላማው ሠራተኞችን መምረጥ እና እቅድ ማውጣት፣ እያንዳንዱ አካል ዘላቂነት እና ፍትሃዊነት ባለው ኢኮኖሚያዊ ሥርዓት ውስጥ የሚያበረክተውን ሙያዊ ብቃት ለማረጋገጥ መሆኑ ታውቋል። ሞያዊ ብቃት እና የሥራ እንቅስቃሴን ማሳደግ አስፈላጊ መሆኑን የገለጹት ክቡር አባ አንቶኒዮ ጉዌሬሮ፣ ከውጪ በኩል አጋዥ ክህሎት የማግኘት አስፈላጊነት እና ለቅድስት መንበር መሥራት ምን ማለት እንደሆነ የሚያውቁ ተባባሪዎችን መቅጠር አስፈላጊ መሆኑን ገልጸዋል።  

በሁለተኛ ደረጃ፣ አዲሱ የተዋቀረው ጽሕፈት ቤታቸው በሰው ሀብት ልማት ላይ እንደሚሠራ የገለጹት ክቡር አባ አንቶኒዮ ጉዌሬሮ፣ በቅድስት መንበር ጽሕፈት ቤቶች የሚሰሩ የተለያዩ አካላት በስልጠና መርሃ ግብሮች በመታገዝ ሙያዊ ማሻሻያዎችን እንዲያካሂዱ ለማበረታታት መሆኑን ገልጸው፣ ለእያንዳንዱ ሰው ተጨባጭ የሥራ ግምገማ ሥርዓት እንዳለ፣ በቅድስት መንበር የኤኮኖሚ ጉዳዮች ጽሕፈት ቤት ሕጎቹ እና መመሪያዎቹ በትክክል መተግበራቸው ለማረጋገጥ መወሰኑን ገልጸዋል።

በቅድስት መንበር አዲስ የሥራ መስክ ለደመወዝ እና ለማበረታቻዎች የተሰጠው ትኩረት ጠቃሚ እንደሆነ የገለጹት ክቡር አባ አንቶኒዮ ጉዌሬሮ፣ የሠራተኞችን ተነሳሽነት ለማሳደግ በምዘና ሥርዓቱ ላይ ተመስርተው የሚገባቸውን ለመካስ የሚያስችል አሰራር መኖሩ በቋሚ ደመወዝ ላይ ጭማሪን ለማድረግ እድል ይሰጣል ብለዋል። የሥራ መስኮች እንክብካቤን ያሳሰቡት ክቡር አባ አንቶኒዮ ጉዌሬሮ፣ አዲሱ መመሪያ በቅድስት መንበር እና በቤተክርስቲያን ተልዕኮ ውስጥ መግባባትን እና የተሳታፊነትን ስሜት ማሳደግ እንደሚገባ፣ ዓላማው በውስጥ ግንኙነት፣ በስብሰባ ጊዜያት እና ከሥራ ውጪ ባሉት ጊዜያት የጋራ አገልግሎትን እና መንፈሳዊነትን ተግባራዊ ለማድረግ መሆኑን አስረድተዋል።

እነዚህን ዓላማዎች ለማሳካት የሁሉን ሰው ትብብር እንደሚጠይቅ እና በጊዜ ሂደት ተግባራዊ እንደሚሆን ገልጸው፣ አዲሱ መመሪያ ሥራ ላይ ከሚውልበት ከግንቦት 28/2014 ዓ. ም. ጀምሮ አንዳንድ የአሠራር ምልከታዎች ከግምት ውስጥ መግባት እንዳለባቸው፣ በቅድስት መንበር የኤኮኖሚ ጉዳዮች ጽሕፈት ቤት ሥራ አስፈጻሚ ክቡር አባ አንቶኒዮ ጉዌሬሮ፣ ለልዩ ልዩ የቅድስት መንበር ጽሕፈት ቤቶች መሪዎች በላኩት መልዕክት ገልጸዋል።

02 June 2022, 16:20