ፈልግ

ቅዱስ ፍራንችስኮስ ደ ላሳል ቅዱስ ፍራንችስኮስ ደ ላሳል 

ሊቀ ጳጳስ ፊዚኬላ፥ “በአንድነት ፍለጋ ላይ ቅዱስ ፍራንችስኮስ ደ ላሳልን መመልከት ያስፈልጋል!”

በቅድስት መንበር የስብከተ ወንጌል አገልግሎት ጳጳሳዊ ጽሕፈት ቤት ፕሬዚዳንት፣ ሊቀ ጳጳስ አቡነ ሪኖ ፊዚኬላ፣ አንድነትን ለማምጣት በሚደረግ ጥረት ዘወትር ቅዱስ ፍራንችስኮስ ደ ላሳልን መመልከት እንደሚያስፈልግ አሳሰቡ። ሊቀ ጳጳስ አቡነ ሪኖ ፊዚኬላ ይህን ያሳሰቡት፣ ጥር 16/2015 ዓ. ም. ሮም ከተማ በሚገኝ በሞንቴሳንቶ እመቤታችን ቅድስት ማርያም ባዚሊካ ውስጥ በቀረበው፣ የጋዜጠኞች ባልደረባ ቅዱስ ፍራንችስኮስ ደ ላሳል ዓመታዊ በዓል መስዋዕተ ቅዳሴ ጸሎት ላይ ነው። ቅዱስ ፍራንችስኮስ ደ ላሳል በውጥረት መካከል መረጋጋትን የሚያመጡ ማራኪ ጽሑፎችን በማቅረብ እና የእርስ በርስ ግንኙነቶችን በማሳደግ ለዛሬዎቹ ጋዜጠኞች መልካም ምሳሌ ሊሆኑ እንደሚችል ተናግረዋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

ሊቀ ጳጳስ ብጹዕ አቡነ ፊዚኬላ፣ “የእግዚአብሔር ፈቃድ” በሚለው መሪ ሃሳብ ላይ በማትኮር ባቀረቡት ስብከት፣ ሐዋርያው ቅዱስ ማርቆስ የጻፈው የወንጌል ክፍል፣ ሐዋርያው ጳውሎስ ለዕብራውያን ሰዎች የጻፈው መልዕክት እና ከዳዊት መዝሙር የተወሰደው ጥቅስ፣ ሦስቱ ንባባትም በእግዚአብሔር ፈቃድ ላይ የሚያተኩሩ እንደ ነበር ገልጸው፣ የእግዚአብሔር ፈቃድ ሰዎች በሙሉ የኢየሱስ ክርስቶስ ወንድሞች እና እህቶች እንዲሆኑ ያደርጋቸዋል ብለዋል። ቅዱስ አጎስጢኖስ ስለ እግዚአብሔር ፈቃድ ሲናገር፥ "እነሆ ፈቃድህን ላደርግ መጥቻለሁ" በማለት የተናገረው የወንጌል ቃል አነጋገር ውብ አገላለጽ እንደሆነ ተናግረው፣ የእግዚአብሔር ፈቃድ በሚታወቅበት ወቅት በቅዱስ ወንጌል ቃል ላይ ማሰላሰል እና መመርመር አስፈላጊ እንደሆነ ተናግረዋል።

“የጥምቀትን ምስጢር ከተቀበሉ በኋላ የእግዚአብሔርን ፈቃድ ለማወቅ ግድ የሌላቸው በርካቶች ናቸው” ያሉት ሊቀ ጳጳስ ብጹዕ አቡነ ፊዚኬላ፣ ነገር ግን ለሚያምኑት በሙሉ የእግዚአብሔር ፈቃድ፣ በእግዚአብሔርና በጎረቤት ፍቅር የተጠቃለለ መሆኑን ማጤን አለብን ብለዋል። ፍቅር የቅዱስ ወንጌል ማጠቃለያ እንደሆነ፣ ለኛ አማኞች ከተገለጠልን ፍቅር የበለጠ የተቀደሰ ሌላ ቃል እንደሌለ ገልጸው፣ “ነገር ግን በጊዜያችን እና በባሕላችን ስለ ፍቅር እውነቱን ማስተዋልና መመስከር፣ እንዲሁም የፍቅርን እውነት የመረዳት ብቃት እንዴት ልናገኝ እንችላለን?” በማለት ጠይቀዋል።

የፍቅር ማዕከል ኢየሱስ ብቻ ነው

በዕለቱ ከማር. 3: 31-35 ተወስዶ በተነበበው የቅዱስ ወንጌል ክፍል ላይ በማስተንተን ስብከታቸውን ያቀረቡት አቡነ ፊዚኬላ፣ በዚህ የወንጌል ክፍል ላይ የኢየሱስ እናት፣ ወንድሞች እና እህቶች ኢየሱስን ፈልገውት እንደመጡ፣ ውጭ ሆነ ውስጥ፣ እንዲሁም በዙሪያው ብዙ ሰዎች ተቀምጠው እንደ ነበር በማስታወስ፣ “እኛስ የት እንገኛለን? ከቤት ውጭ ሆነን የኢየሱስን መምጣት እየጠበቅን እንገኛለን? ወይስ ቤት ውስጥ ሆነን በዙሪያው ተቀምጠን ቃሉን እየሰማን እንገኛለን?” በማለት ጠይቀዋል። ሦስተኛ ምርጫ የለም ያሉት ሊቀ ጳጳስ አቡነ ፊዚኬላ፣ ኢየሱስ ወደ እኛ እስኪመጣ ድረስ እንጠብቀዋለን ወይም እርሱን በመካከላችን አድርገን እኛ በዙሪያው እንሆናለን” ብለው፣ ማዕከላችን የናዝሬቱ ኢየሱስ ክርስቶስ እንጂ እኛ አይደለንም”ብለዋል።

ሕይወቱን እንድንካፈል የተጠራን የኢየሱስ ወንድሞች ነን!

ከዕለቱ ቅዱስ ወንጌል የተገኘ ሁለተኛ ትምህርት የጠቆሙት ሊቀ ጳጳስ አቡነ ፊዚኬላ፣ ኢየሱስ በዙሪያው ወደተቀመጡት ሰዎች ተመልክቶ፥ “የእግዚአብሔርን ፈቃድ የሚያደርግ ሁሉ፥ እርሱ ወንድሜ፣ እህቴም፥ እናቴም ነው” ማለቱን በመጥቀስ፣ የእግዚአብሔር ቃል ሁልጊዜ ባለፈው ሳይሆን በአሁን ጊዜ ላይ በማትኮር ጥያቄን እንደሚያቀርብልን እና ለጥያቄውም ታማኝ ምላሽ መስጠት ያለብን አሁን መሆን እንደሚገባ ገልጸዋል። “ክርስቲያኖች የኢየሱስ ክርስቶስ ወንድሞች እና እህቶች ናቸው” ያሉት ሊቀ ጳጳስ አቡነ ፊዚኬላ፣ ቅዱስ አውግስጢኖስን በመጥቀስ “ኢየሱስ አንድያ ልጅ ነው፤ ነገር ግን እግዚአብሔር አብ ልጁ ኢየሱስ ክርስቶስ ብቸኝነት እንዳይሰማው ብዙ ወንድሞችን እና እህቶችን ሊሰጠው ፈለገ” ብለዋል።በመቀጠልም "እኛ የእግዚአብሔር ቤተሰብ ነን፤ የጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስን ሕይወት እንድንካፈል፣ ቃሉን እንድንሰማ፣ ትምህርቱን እንድንረዳ እና ሕይወታችን እንድናደርገው የተጠራን ነን" ብለው “ይህም የእግዚአብሔርን ፈቃድ ዕለት ዕለት ማድረግ ነው” በማለት አስረድተዋል።

የቅዱስ ፍራንችስኮስ ደ ላሳል የእርጋታ ምሳሌነት

ሊቀ ጳጳስ አቡነ ፊዚኬላ በስብከታቸው መደምደሚያ፣ ክርስቲያኖች የቅዱስ ፍራንችስኮስ ደ ላሳል ምሳሌ ተከትለው አንድነታቸውን እንዲያጠናክሩ በመጋበዝ፣ የቅዱስ ፍራንችስኮስ ደ ላሳል ዓመታዊ ክብረ በዓል ለክርስቲያኖች አንድነት ጸሎት በሚደረግበት ሳምንት መሆኑ በአጋጥሚ እንዳልሆነ አስታውሰዋል። ከቅዱስ ፍራንችስኮስ የሕይወት ታሪክ መረዳት እንደሚቻለው፣ ካልቪኖ ዕድሜው ከሰማንያ ዓመት በላይ ቢሆነውም በመካከላቸው ያለው ግንኙነት መልካም እና የወዳጅነት እንደ ነበር፣ በደረጃቸው መካከል ርቀት ቢኖርም የማያቋርጥ የአንድነት ፍለጋ እንደ ነበር፣ በጽሑፎቹ ሁሉ መረጋጋትን በመፈለግ ውይይቱን ወደ ሌላ አቅጣጫ ሳያመራ በእምነቱ ላይ ብቻ ይከራከሩ እንደነበር አስረድተዋል። እንደ ምዕመናን የዕለት ተዕለት ኑሮአችን እና በሥራ ላይ ያለን ሙያዊ ብቃታችን የእግዚአብሔርን ፈቃድ ለመፈጸማችን እውነተኛ ምስክር ይሆን ዘንድ የቅዱስ ፍራንችስኮስ ደ ላሳልን ምሳሌ ልንከተል ይገባል ብለዋል።

 

25 January 2023, 17:15