ፈልግ

“ከዓለም ፍጻሜ በፊት አንዳንድ ቃላት” በሚል ርዕሥ የተጻፈ መጽሐፍ “ከዓለም ፍጻሜ በፊት አንዳንድ ቃላት” በሚል ርዕሥ የተጻፈ መጽሐፍ  

በችግር ወቅት ቅዱስ ወንጌልን ማንበብ ዓለምን ይበልጥ ለመረዳት የሚያግዝ መሆኑ ተገለጸ

የዶሜኒካን ገዳማውያን ማኅበር አባል የሆኑት ፈረንሳዊ ካህን አባ አድሪያን ካንዲያርድ፣ “ከዓለም ፍጻሜ በፊት አንዳንድ ቃላት” በሚል ርዕሥ የጻፉትን መጽሐፍ ይፋ አድርገዋል። በቫቲካን ማተሚያ ቤት የታተመው መጽሐፉ፣ በደንብ ግንዛቤን ባላገኙ ርዕሠ ጉዳዮች ላይ ኢየሱስ ክርስቶስ ያቀረባቸውን ስብከቶች የሚመለከት እንደሆነ ተገልጿል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

የእስልምና ሃይማኖት ሊቅ የሆኑት አባ አድሪያን፣ በአውሮፓ ውስጥ መጽሐፎቻቸው በስፋት ከሚነበብላቸው እውቅ ክርስቲያን ደራሲዎች መካከል አንዱ ናቸው። አባ አድሪያን በሮም በኩል ሲያልፉ፣ በዚህ ጊዜ በመጽሐፍት መደብሮች ውስጥ ስለሚገኝ አዲሱ መጽሐፋቸው እንዲያስረዱ ተጋብዘዋል። “ከዓለም ፍጻሜ በፊት አንዳንድ ቃላት” በሚል ርዕሥ በቫቲካን ማተሚያ ቤት የታተመው መጽሐፉ፣ አንድ መቶ አራት ገጾች ያሉት እንደሆነ ታውቋል። "በችግር ጊዜ ቅዱስ ወንጌልን ማንበብ" የሚል ንዑስ ርዕስ የተሰጠው መጽሐፉ ግልጽ የሆነ አመለካከትን ምናልባት የዓለም ፍጻሜ ከሚለው አገላለጽ ትንሽ ያነሰ ሊሆን እንደሚችል ተገልጿል።

ከዓለም ፍጻሜ በፊት የሚለው የመጽሐፉ ርዕሥ፣ በተለምዶ የሚታመነውን የዓለም ፍጻሜን እንደማይገልጽ የተናገሩት የመጽሐፉ ደራሲ አባ አድሪያን፣ የዓለም ፍጻሜ የሚለው ቃል ከግሪክ ቃል የተገኘ መሆኑን ደራሲው በመግለጽ፣ ትርጉሙም 'የታሪክ ትርጉም መገለጥ' ማለት እንደሆነ አስረድተዋል። ኢየሱስ ስለ ርዕሡ የተናገረበትን የቅዱስ ወንጌል ክፍሎችን ከማንበባችን በፊት አስፈላጊ ማብራሪያን በመስጠት ይበልጥ ሰላማዊ ከሆኑ የኢየሱስ ክርስቶስ ስብከቶች ጋር ማያያዝ እንደሚያስፈልግ አስረድተዋል። ኢየሱስ ክርስቶስ የዓለም ፍጻሜን በማስመልከት ያቀረበው ስብከት ብዙም አይታወቅም ያሉት አባ አድሪያን፣ "በተለይ በማርቆስ ወንጌል ምዕ. 13 ላይ የሚገኝ እና ችግር በበዛበት እንደ ዛሬው ዓይነት ጊዜ ጠቃሚ ነው” ብለው፣ ኢየሱስ ክርስቶስ የተናገረው ስለ ዓለም ፍጻሜ ሳይሆን እኛ ስለምንገኝበት ስሜት እና ስለምንሄድበት አቅጣጫ እንደሆነ አባ አድሪያን አስረተዋል።

የዓለም ፍጻሜ ፍርሃትን ሳይሆን መለኮታዊ እይታን ይገልጻል

“ከዓለም ፍጻሜ በፊት አንዳንድ ቃላት” በሚል ርዕሥ አባ አድሪያን የጻፉት መጽሐፍ ከጦርነት እስከ ኤኮኖሚያዊ ሁኔታ እና እስከ የአካባቢ ቀውስ ድረስ የሚፈጠሩት ነገሮች በማንሳት ጥያቄን እንድንመልስ የሚያስችል መሆኑ ታውቋል። ቅዱስ ወንጌል ምን ሊጠቅመን ይችላል? ምንስ ሊናገረን ይችላል? በማለት የጠየቁት አባ አድሪያን፣ ቅዱስ ወንጌል የሚናገረን ነገር ባይኖረው ኖሮ ነፍሳችንን እና የጸሎት ጊዜያችንን ብቻ ይወስድብን ነበር እንጂ ሌላ ምንም አይጠቅምም ነበር" በማለት መልሰዋል። ቅዱስ ወንጌል ለግል ሕይወታችን በመንፈሳዊ ደረጃ ብቻ ሳይሆን በጋራ ታሪካችን ላይም የሚናገር መሆኑን በመጽሐፋቸው ውስጥ በትክክል ለመግለጽ መሞከራቸውን ገልጸዋል። 

መጽሐፉ ደራሲው እንደተናገሩት እርስ በርሱ የሚጋጭ አነጋገር የሚያብራራ በመሆኑ፣ ምናልባት በዚህ ዓለም ውስጥ ትንሽ ተስፋን ለማግኘት ስለ ዓለም ፍጻሜ በጥቂቱም ቢሆን መነጋገሩ አስፈላጊ እንደሆነ ልንስማማበት ይገባል። ኢየሱስ ክርስቶስ ስለ ዓለም ፍጻሜ ያቀረበውን ስብከት የያዙ ገጾችን እንደገና መመልከቱ ትምህርታዊ ዕይታን እንደሚጨምር ታውቋል። "ኢየሱስ ክርስቶስ ስለ ዓለም ፍጻሜ ትንቢት መናገሩ በዓይኖቻችን የምናያቸውን ነገሮች እንድንረዳ እንጂ ይብዛም ይነስም በከንቱ ሊያስደነግጠን አይደለም” ያሉት አባ አድሪያን፣ የዓለም ፍጻሜ በሰው ጥፋት የሚደርስ መለኮታዊ ቅጣት ሳይሆን የክፋት መስፋፋት እና የሚያስከትለውን አጥፊ ውጤት የሚያስጠነቅቅ ነው" ብለዋል። 

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በተደጋጋሚ እንደሚመክሩት፣ ቅዱስ ወንጌልን ማንበብ ዓለማችንን በተሻለ ሁኔታ ለመረዳት የሚያስችሉ ቁልፎችን እንደሚሰጥ፣ ክፋት ቢስፋፋም የጠንካራ ተስፋ ምንጭ የሆነውን ዓለማችንን ይበልጥ ለመረዳት እንደሚያግዝ አባ አድሪያን ተናግረው፣ አዲስ ያሳተሙት መጽሐፋቸው በትክክል ያነጣጠረው፣ ይህን አስደናቂ ጊዜ እየኖረ ለሚገኝ እና ከእግዚአብሔር ቃል ውስጥ ዕርዳታን ለማግኘት ለሚፈልግ ሰው እንደሆነ በማስረዳት ከቫቲካን የዜና አገልግሎት ጋር የነበራቸውን ቆይታ ደምድመዋል።

21 March 2023, 16:04