ፈልግ

የብፁዕ ካርዲናል ካንታላሜሳ፣ የዓብይ ጾም ወቅት ስብከት የብፁዕ ካርዲናል ካንታላሜሳ፣ የዓብይ ጾም ወቅት ስብከት  (Vatican Media)

ካርዲናል ካንታላሜሳ፥ “በውስጣችን ያለው ፍቅር የራሳችን ሳይሆን ከእግዚአብሔር የተቀበልነው ነው!”

ለርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት እና የቅርብ ተባባሪዎቻቸው መንፈሳዊ ስብከቶችን የሚያቀርቡት ብፁዕ ካርዲናል ራኒዬሮ ካንታላሜሳ፣ የዓብይ ጾም ወቅት ሦስተኛ ዙር ስብከታቸውን ለጳጳሳዊ ጽሕፈት ቤት አገልጋዮች አቅርበዋል። ብጹዕ ካርዲናል ካንታላሜሳ በስብከታቸው፥ “በልባችን ውስጥ ያለው ፍቅር የራሳችን ሳይሆን ከእግዚአብሔር የተቀበልነው እና መልሰን ለእርሱ የምንሰጠው ነው” ብለዋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

የፍራንችስካውያን ታናናሽ ወንድሞች ማኅበር አባል የሆኑት ብፁዕ ካርዲናል ራኒዬሮ ካንታላሜሳ፣ ዓርብ መጋቢት 8/2015 ዓ. ም. ያቀረቡት ሦስተኛ ዙር የአብይ ጾም ወቅት ስብከት ርዕሥ፣ “እግዚአብሔር ለሕዝቡ ያለው ፍቅር” የሚል እንደነበር ተመልክቷል።  

“የተከበራችሁ አባቶች፣ ወንድሞች እና እህቶች፣ የዛሬው አስተንትኖ ለእናንተ እና ለእኔ መጽናኛ እንዲሆን” በማለት ስብከታቸውን የጀመሩት ብፁዕ ካርዲናል ካንታላሜሳ፣ በዕለቱ ያቀረቡት ስብከት ሙሉ በሙሉ በእግዚአብሔር ላይ ያተኮረ እንደሆነ ገልጸው፣ ነገረ-መለኮታዊ ይዘት ያለው እና እግዚአብሔርን በሚመለከት የሚቀርብ ንግግር ከማንኛውም የቤተ ክርስቲያን ሕይወት እውነታ ሊለይ እንደማይችል ሁሉ፣ ከሲኖዶሳዊነት እውነታም ተለይቶ ሊታይ እንደማይችል ገልጸው፣ እምነት ያለ ነገረ-መለኮታዊ መሠረት ፍሬ አልባ ድግግሞሽ እንደሚሆን አስረድተዋል።

እግዚአብሔር ለሕዝቡ ያለው ቅርበት

“ይህን ተግባራዊ ለማድረግ ነገረ-መለኮት ራሱ ጥልቅ ተሃድሶ ሊደረግበት ይገባል” በማለት ሐሳባቸውን አቅርበዋል። "የእግዚአብሔር ሕዝብ የሚያስፈልገው፣ ሕይወት ያለው ነገረ-መለኮት ነው” ያሉት ብፁዕ ካርዲናል ካንታላሜሳ፣ ነገረ-መለኮትን ከዘመኑ የፍልስፍና ሥርዓት ጋር በማዛመድ ስለ እግዚአብሔር 'በሦስተኛ አካል' በኩል የሚናገሩ ከሆነ መረዳት የማይቻል መሆኑን ገልጸዋል። ከዚህ ይልቅ እግዚአብሔርን በቅርብ መንገድ መመልከት እንደሚያስፈልግ አሳስበዋል።

"ስብከታቸው በነገረ-መለኮት ላይ ተሃድሶን ለማካሄድ እንዳልሆነ ያስገነዘቡት ብፁዕ ካርዲናል ካንታላሜሳ፣ ይህን ለማድረግ ብቃት የሌላቸው መሆኑን ተናግረው፣ ይልቁንም ፍላጎታቸው፣ በተገለጸው የነገረ-መለኮት መንገድ አማካይነት የወንጌልን መልዕክት ለዛሬው የሰው ልጅ ጉልህ በሆነ መንገድ ለማቅረብ፣ ለእምነታችን እና ለጸሎታችን የሚያበረክተውን የአዲስ ሕይወት አስተዋጽኦን ለማሳየት መሆኑን አስረድተዋል።

"እግዚአብሔር ይወዳችኋል!"

የሁሉም ሰው ልብ የሚፈልገው እና ቤተ ክርስቲያንም ለዓለም ማወጅ የሚገባት መልካም ዜና “እግዚአብሔር ይወዳችኋል!” የሚል እንደሆነ የተናገሩት ብፁዕ ካርዲናል ካንታላሜሳ፣ ይህም በውስጣችን የያዝነውን እና “እግዚአብሔር ይፈርድብሃል!” የሚለውን የሚተካ መሆኑን አስረድተዋል። “እግዚአብሔር ፍቅር ነው” የሚለው እውነት፣ የፍቅሩ ተግባራዊነት፣ ቅዱስ ወንጌል የሚያሳስበን እና በእያንዳንዱ ክርስቲያን ሊገለጽ የሚገባ መሆኑን አጥብቀው ተናግረዋል።

ብፁዕ ካርዲናል ካንታላሜሳ ስለ እምነት ምስጢራት ባቀረቡት ስብከት፥ ከሥላሴ፣ ከሥጋዌ እና ከሕማማት በስተጀርባ ስላለው ጥልቀት እና ትርጉም አብራርተው፣ በእነዚህ ምስጢራት ላይ ያሰላሰልነው እውነት በሕይወታችን ውስጥ ምን ዓይነት ለውጥን እንደሚያመጣ ማየት አለብን ብለዋል። ቅዱሳት ምሥጢራት በሕይወታችን ላይ በሚያመጧቸው ለውጦች በመታገዝ የክርስትና እምነታችን ውድ ሃብት የሆነውን እና የማይጠፋውን የምሥራች ቃል ለማሳደግ መጣር እንዳለብን አሳስበው፣ በኢየሱስ ክርስቶስ አንድ በመሆናችን በምሥራቹ ቃል በመታገዝ እኛም መልሰን እግዚአብሔርን ማፍቀር እንችላለን ብለዋል።

የተትረፈረፈ መለኮታዊ ፍቅር

"በእኛ ላይ የፈሰሰው ፍቅር፣ እግዚአብሔር አብ ልጁን ኢየሱስ ክርስቶስን ከወደደበት ፍቅር ጋር አንድ ነው” ያሉት ብፁዕ ካርዲናል ካንታላሜሳ፣ “ይህ ፍቅር ቅድስት ሥላሴን ሞልቶ የተትረፈረፈ መለኮታዊ ፍቅር ነው" ብለዋል። የመስቀሉ ቅዱስ ዮሐንስ፥ “እግዚአብሔር ለነፍስ መልዕክቱን ያስተላልፋል” ማለቱን የጠቀሱት ብፁዕ ካርዲናል ካንታላሜሳ፣ ለወልድ በገለጸበት መንገድ ባይሆንም እግዚአብሔር ተመሳሳይ ፍቅሩን ለእኛ ይገልጽልናል ብለው፣ አብን መውደድ የምንችለው ወልድ በወደደው ፍቅር እንደሆነ እና ኢየሱስን መውደድ የምንችለው አብ በወደደው ፍቅር መሆኑን አስረድተዋል።

“ፍቅር ለሆነው ለመንፈስ ቅዱስ ምስጋና ይሁንለት!” ያሉት ካርዲናል ካንታላሜሳ፣ “እግዚአብሔርን ‘እወድሃለሁ!’ ስንል እራሳችንን ለእርሱ እንሰጣለን ወይ?” ብለው ጠይቀው፣ ለእግዚአብሔር የምንሰጠው ፍቅር ከእርሱ የተቀበልነው መሆኑን አስረድተዋል። "ከልባችን አውጥተን ለእግዚአብሔር መልሰን የምንሰጠው ፍቅር፣ የእርሱ ልጆች በመሆናችን በነጻነት የምንሰጠው ምስጋና ነው” ብለዋል።

የእግዚአብሔር ፍቅር በቅዱስ ቁርባን በኩል በምሳሌያዊ መንገድ መፈጸሙን ገልጸው፣ እግዚአብሔር አብ አስቀድሞ የሰጠን ልጁን ኢየሱስ ክርስቶስን “መሥዋዕታችን” አድርገን ለአብ የምንቀርብ መሆኑን ገልጸዋል። በ “አባታችን ሆይ!” ጸሎት፥ “አባት ሆይ! ልጅህን ኢየሱስን በወደድከው ፍቅር እወድሃለሁ! ፣ “ኢየሱስ ሆይ! የሰማዩ አባትህ አንተን በወደደህ ፍቅር እወድሃለሁ! ይህም በምናባዊነት ሳይሆን በእርግጠኝነት መሆኑን ማረጋገጥ እንችላለን” ብለዋል።

20 March 2023, 14:44