ፈልግ

የዘር መድልዎ የሚወገድበት ዓለም አቀፍ ቀን መታሰቢያ የዘር መድልዎ የሚወገድበት ዓለም አቀፍ ቀን መታሰቢያ   (Copyright 2011 Brett Jorgensen Photography)

ቅድስት መንበር፣ ዘረኝነት ዛሬም ማኅበረሰባችንን እያስጨነቀ እንደሚገኝ ገለጸች

በተባበሩት መንግሥታት የቫቲካን ታዛቢ የሆኑት ሊቀ ጳጳስ አቡነ ገብርኤል ካቻ፣ የዘር መድልዎ መወገድ እንዳለበት በኒውዮርክ ባደረጉት ንግግር ገልጸው፣ በኅብረተሰባችን ውስጥ የዘለቀው ዘረኝነት፣ እውነተኛ የሕዝቦች ግንኙነት ባሕልን በማስተዋወቅ ሊጠፋ እንደሚችል አስረድተዋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

ቅድስት መንበር፣ ዓለም አቀፍ የዘር መድልዎ የሚወገድበት ቀን ተከብሮ በዋለበት መጋቢት 12፣ ዘረኝነት የአብሮነት ባሕልን እና ትክክለኛ የሰው ልጅ ወንድማማችነትን በማጎልበት ሊገታ እንደሚችል ገልጻ፣ ማንኛውንም ዓይነት ዘረኝነት አጥብቃ የምትቃወመው መሆኑንም አስታውቃለች።

ማክሰኞ መጋቢት 12/2015 ዓ. ም. በኒውዮርክ በተካሄደው የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ጠቅላላ ጉባኤ ላይ ንግግር ያደረጉት የቫቲካን ታዛቢው ሊቀ ጳጳስ አቡነ ገብርኤል ካቻ፣ ዘረኝነት አንድ ሰው ከሌላው ይበልጣል በሚለው “የተዛባ እምነት” ላይ የተመሠረተ ነው ብለው፣ ይህ ደግሞ “የሰው ልጆች በሙሉ በክብር እና በመብት እኩል ሆነው በነጻነት ይወለዳሉ” የሚለውን መሠረታዊ መርህ ፈጽሞ የሚቃረን መሆኑን አስረድተዋል።

ሰብዓዊ ግንኙነትን ያገጠመ ቀውስ

በተባበሩት መንግሥታት የቅድስት መንበር ተወካይ ሊቀ ጳጳስ አቡነ ገብርኤል፣ “ዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ዘረኝነትን ለማጥፋት ቁርጠኝነት ቢኖረውም፣ ዘረኝነት እንደ ወረርሽኝ እንደገና ብቅ ማለቱን ቀጥሏል” ብለው፣ ይህም ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በመልዕክታቸው፥ “ሰብዓዊ ግንኙነትን ያገጠመው ቀውስ” ማለታቸውን በመጥቀስ በቁጭት ተናግረዋል። “ዘረኝነት አሁንም ማኅበረሰባችንን እየጎዳው ይገኛል” ያሉት ሊቀ ጳጳስ አቡነ ገብርኤል፣ “የዘር መድልዎ ብዙውን ጊዜ በግልጽ ተለይቶ የሚታወቅ እና የተወገዘ፣ በግልጽ ባይታይም በኅብረተሰቡ ውስጥ ጠልቆ የገባ የዘር ጭፍን ጥላቻ አሁንም አለ” ብለዋል።

የመገናኘት ባሕልን በማሳደግ ዘረኝነትን መዋጋት

“ማኅበራዊ ግንኙነትን ያጋጠመው ቀውስ ምንጩ ዘረኝነት ነው” ያሉት ሊቀ ጳጳስ አቡነ ገብርኤል፣ ሊወገድ የሚችለውም እርስ በርስ የመገናኘት፣ የመተሳሰብ እና ትክክለኛ የሰው ልጅ ወንድማማችነት ባሕልን በማሳደግ እንደሆነ ገልጸው፣ ይህ ማለት አብሮ መኖር እና መቻቻል ማለት ብቻ እንዳልሆነ አስረድተዋል። 

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ይፋ ባደረጉት እና “ሁላችንም ወንድማማቾች ነን” በሚለው ሐዋርያዊ ቃለ ምዕዳናቸው፣ “ሰዎችን የሚያገናኙ መድረኮችን በመፈለግ፣ የመገናኛ ድልድዮችን በመገንባት፣ ማንንም ወደ ጎን ሳይሉ ሁሉንም የሚያካትት የተግባር መርሃ ግብሮችን ማዘጋጀት እንደሚያስፈልግ ማሳሰባቸውን ጠቅሰዋል። ይህን ባሕል መገንባት የሚቻለው እያንዳንዱ ሰው ለማኅበረተሰቡ ያለውን ልዩ አመለካከት እና የሚያበረክተውን የማይናቅ አስተዋፅዖን ከማወቅ ይመነጫል በማለት የቫቲካን ታዛቢው አክለዋል። “ለሰው ልጅ ሰብዓዊ ክብር እውቅና መስጠት ብቻ የሁሉንም ሰው እና የእያንዳንዱን ማኅበረሰብ የጋራ ዕድገት ሊያመጣ ይችላል” ያሉት አቡነ ገብርኤል፣ የዚህ ዓይነቱን ዕድገት ለማነሳሳት በተለይ ለወንዶች እና ለሴቶች እኩል ዕድሎችን ማረጋገጥ እና በሁሉም የሰው ልጆች መካከል ተጨባጭ እኩልነት ማረጋገጥ አስፈላጊ እንደሆነ ተናግረዋል።

ዘረኝነት በስደተኞች እና ጥገኝነት ጠያቂዎች ላይ አነጣጥሯል

ሊቀ ጳጳስ አቡነ ገብርኤል ንግግራቸውን ሲያጠቃልሉ፣ ቅድስት መንበር በስደተኞች እና ጥገኝነት ጠያቂዎች ላይ እየደረሰ ያለው ዘረኝነት እና ጭፍን ጥላቻ እንዳሳሰባት ተናግረው፣ በዚህ ረገድ "የተሻለ፣ ፍትሃዊ እና ወንድማማችነትን የሚፈጥር ብቸኛው ባሕል" እርስ በርስ መተዋወቅ እንደሆነ ገልጸው፣ ራስን በመከላከል እና በፍርሃት አመለካከት ላይ ለውጥ ማድረግ እንደሚያስፈልግ ጠቁመዋል።

የዘር መድልዎ የሚወገድበት መታሰቢያ ዓለም አቀፍ ቀን

የዘር መድልዎ ዓለም አቀፍ ቀን በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት አስተባባሪነት እንደ ጎርጎሮሳውያኑ በ1966 ዓ. ም. የተቋቋመው ሲሆን፣ በየዓመቱ የሚከበረውም፣ በደቡብ አፍሪካ ሻርፕቪል ከተማ እንደ ጎርጎሮሳውያኑ 1960 ዓ. ም. የአፓርታይድን ሕግ በመቃወም ሰልፍ የወጡ 69 ሰላማዊ ሰዎች የተገደሉበትን ቀን ለማስታወስ መሆኑ ይታወቃል።

የዓለም አብያተ ክርስቲያናት ምክር ቤት ልዩ የጸሎት ሳምንት

የዘር መድልዎ የሚወገድበት መታሰቢያ ዓለም አቀፍ ቀን፣ የዓለም አብያተ ክርስቲያናት ምክር ቤት ከመጋቢት 10 እስከ መጋቢት 16 ያሉት ቀናት ልዩ ጸሎት የሚደረግበት ሳምንት እንዲሆን የወሰነበት፣ በተባበሩት መንግሥታት ድርጅትም የባርነት ሰለባዎች እና አትላንቲክ አቋራጭ የባሪያ ንግድ የሚታወስበት ቀን እንደሆነም ታውቋል።

የዓለም አብያተ ክርስቲያናት ምክር ቤት በእያንዳንዱ የሳምንቱ ቀናት መንፈሳዊ መዝሙሮችን እና በመጽሐፍ ቅዱስ ንባባት ላይ ለማስተንተን የሚያግዙ ጽሑፎችን እንደሚያቀርብ ታውቋል። በጸሎት ሥነ ሥርዓቱ ላይ የሚቀርቡ ጽሑፎች በሙሉ፣ ፍትሃዊ እና ሁሉን አቀፍ ዓለም እንዴት መገንባት እንደሚቻል እና ሁሉም በክብር እና በፍትህ መኖር ሲችሉ ብቻ እንደሆነ የሚያስረዱ እንደሆኑ ታውቋል። በርካታ አገራት ከእነዚህም መካከል ከሕንድ እስከ ጉያና እና በሌሎች አገራት የሚገኙ በርካታ ብሔሮች እና ሕዝቦች፣ ግለሰቦች እና ቡድኖች በጸሎት ሥነ ሥርዓቱ በድምቀት እንደሚሳተፉ ታውቋል። ጸሎቶቹ በተለያዩ ክልሎች የሚገኙ ሕዝቦች እርስ በርስ በጸሎት በመተባበር ዘረኝነትን እና ኢ-ፍትሃዊነት እንዲያወግዙ የሚጋብዙ እንደሆነ ተነግሯል።

23 March 2023, 16:24