ፈልግ

የኒካራጓ ፕሬዝዳንት ዳንኤል ኦርቴጋ የኒካራጓ ፕሬዝዳንት ዳንኤል ኦርቴጋ 

ቅድስት መንበር ዲፕሎማሲያዊ ተልዕኮቿን እንድታቋርጥ ኒካራጓ ጠየቀች

የላቲን አሜሪካ አገር ኒካራጓ፣ በውጭ ጉዳይ ሚኒስቴሩ በኩል ባሳለፈችው ውሳኔ፣ ቅድስት መንበር ዲፕሎማሲያዊ ተልዕኮቿን እንድታቋርጥ ጠይቃለች። የማናጓ መንግሥት በአገሪቱ የነበሩ የቅድስት መንበር ሐዋርያዊ እንደራሴን ከአንድ ዓመት በፊት ከአገር ማስወጣቱ ይታወሳል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

የኒካራጓ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር፣ በኒካራጓ እና በቅድስት መንበር መካከል ያለው ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት መቋረጡን አስታውቆ፣ በቅድስት መንበር እና በኒካራጓ የሚገኙ የሁለቱም አገራት የዲፕሎማሲ ሚሲዮኖች እንዲዘጉ ጠይቋል። ይህ ግን ሁለቱ አገራት በመካከላቸው ያለውን ግንኙነት ሙሉ በሙሉ አቋርጠዋል ማለት አለመሆኑን የመገናኛ ብዙኃን ዘግበዋል።

የዛሬ ዓመት መጋቢት 3/2014 ዓ. ም. በማናጓ የሚገኝ የቅድስት መንበር ሐዋርያዊ ጽ/ቤት እንደራሴ ሊቀ ጳጳስ ዋልድማር ስታኒስላው ከአገሪቱ እንዲወጡ መደረጉ ይታወሳል። በወቅቱ ቅድስት መንበር በኒካራጓ መንግሥት ውሳኔ በማዘን ምላሽ መስጠቷም አይዘነጋም። “እርምጃው ለመረዳት አስቸጋሪ ነው” ያለው የቅድስት መንበር መግለጫ፣ ሊቀ ጳጳስ ሶመርታግ በተልዕኮው ሂደት ውስጥ ለቤተ ክርስቲያኗ እና ለኒካራጓ ሕዝብ፣ በተለይም ለችግር የተጋለጡትን ለማበረታታት፣ በሐዋርያዊ መንበር እና በኒካራጓ ባለሥልጣናት መካከል ጥሩ ግንኙነት እንዲኖር ዘወትር በትጋት ይሠሩ እንደነበር ገልጿል።

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ባለፈው የታኅሳስ ወር ከአንድ የስፔን ዕለታዊ ጋዜጣ ጋር ባደረጉት ቃለ ምልልስ፣ ቫቲካን ከኒካራጓ መንግሥት ጋር ያላትን ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት በማስመልከት ለቀረበላቸው ጥያቄ ሲመልሱ፣ ቅድስት መንበር ሁል ጊዜ ሕዝቦችን ለማዳን እንደምትፈልግ እና መሣሪያዋም ውይይት እንደሆነ ገልጸው፣ ቅድስት መንበር ከአንድ አገር እንድትወጣ ካልተጠየቀች በቀር በገዛ ፈቃዷ እንደማትወጣ እና ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነቶችን ለማዳን ብላ በትዕግስት እና በውይይት የሚያድጉ ግንኙነቶችን ለማዳበር ሁልጊዜ እንደምትጥር አስረድተዋል።

የኒካራጓ መንግሥት ከቅርብ ዓመታት ወዲህ በሚወስዳቸው የማሰር፣ የማፈናቀል እና በሰላማዊ ሰልፎች ላይ በሚፈጽማቸው ኃይለኛ እርምጃዎች ምክንያት ማኅበራዊ እና ፖለቲካዊ ሁኔታው እየባሰበት መምጣቱ ታይቷል። የማታጋልፓ ሊቀ ጳጳስ አቡነ ሮላንዶ አልቫሬዝ ካለፈው ነሐሴ ወር ጀምሮ በቁም እስር ከቆዩ በኋላ በዘፈቀደ የ26 ዓመት እስራት ተፈርዶባቸው ዛሬ እስር ቤት ስለሚገኙበት ሁኔታ ምንም ማወቅ አልተቻለም።

 

15 March 2023, 13:23