ፈልግ

የቅዱስ ሲኖዶስ ጠቅላላ ጉባኤ የቅዱስ ሲኖዶስ ጠቅላላ ጉባኤ   (Vatican Media)

የቅዱስ ሲኖዶስ ጠቅላላ ጉባኤ ቅድመ ዝግጅትን የሚያስተባብር ምክር ቤት ተቋቋመ

በካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን የቅዱስ ሲኖዶስ ዋና ጸሐፊ ብጹዕ ካርዲናል ማሪዮ ግሬች፣ የሲኖዶሱን ጠቅላላ ጉባኤ ዝግጅት የሚመሩ አባላትን መጋቢት 6/2015 ዓ. ም. መርጠዋል። በተመረጡት አባላት መካከል የቅዱስ ሲኖዶስ ጠቅላላ ጉባኤ ሰብሳቢ ብጹዕ ካርዲናል ዣን ክሎድ ሆለሪች ይገኙበታል። የሲኖዶሱ ጠቅላይ ጽሕፈት ቤት ዋና ጸሐፊው እንደዚሁም ለጠቅላላ ጉባኤው ዝግጅት ግንቦት 23/2015 ዓ. ም. ወደ እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም የዋዜማ ጸሎት የሚቀርብበት ቤተ መቅደስን እንዲመርጡ በማለት ለአገራቱ ብጹዓን ጳጳሳት ጉባኤዎች እና በምሥራቅ አብያተ ክርስቲያናት መሪዎችን ጥሪ አድርገዋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

የብጹዓን ጳጳሳት ኅብረት በተሰኘው ሐዋርያዊ ደንብ አንቀጽ 10፣ ቁ. 1 እና 2 መሠረት የተመረጡት የቅዱስ ሲኖዶስ መደበኛ ጠቅላላ ጉባኤ ዝግጅት አስተባባሪ ኮሚቴ አባላት ቁጥር ሰባት ሲሆን፣ የኮሚቴው ምክር ቤት በዋና ጸሐፊው በብፁዕ ካርዲናል ማሪዮ ግሬች የሚመራ መሆኑ ታውቋል።

የኮሚቴው አባላት

የምክር ቤቱ አባላትም፣ የኢየሱሳውያን ማኅበር አባል አባ ጃኮሞ ኮስታ የምክር ቤቱ አስተባባሪ፣ ሊቀ ጳጳስ አቡነ ጢሞቴዎስ ጆን ኮስቴሎ፣ አቡነ ዳንኤል ፍሎሬስ፣ እህት ሺዙ ሂሮታ፣ አቡነ ሉሲዮ ሟንዱላ፣ ፕሮፌሰር ዳሪዮ ቪታሊ ሲሆኑ፣ ዋና ጸሐፊው አቡነ ቶማስ ትራፍኒ ሆነው ተመርጠዋል። በምክር ቤቱ ሥራ ውስጥ የቅዱስ ሲኖዶስ ጠቅላይ ጽሕፈት ቤት ዋና ተጠሪ፣ ብፁዕ ካርዲናል ዣን ክላውድ ሆሌሪች ተሳታፊ እንደሚሆኑ ታውቋል።

የቅድመ ዝግጅት ምክር ቤቱ በተቋቋመበት ወቅት፣ የጠቅላይ ሲኖዶሱ ዋና ጸሐፊ ብጹዕ ካርዲናል ግሬች፣ እንደ ጎርጎሮሳውያኑ አቆጣጠር ወደ እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ጸሎት በሚቀርብበት የግንቦት ወር መጨረሻ፣ ለ16ኛው የቅዱስ ሲኖዶስ ጠቅላላ መደበኛ ጉባኤ ዝግጅት እንዲሆን በዓለም አቀፍ ደረጃ ጸሎት የሚቀርብ መሆኑን አስታውቀዋል። የጸሎት ሥነ ሥርዓቱ ዋና ዓላማ፣ መላው የእግዚአብሔር ሕዝብ በመከናወን ላይ የሚገኝ የሲኖዶሳዊነት ሂደት አስፈላጊነት እንዲገነዘብ እና በጸሎትም እንዲደግፈው ለማድረግ፣ የእመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ልዩ ጥበቃ በመላው የሲኖዶሳዊነት ሂደት በተለይም በካቶሊክ ብጹዓን ጳጳሳት ጠቅላላ ጉባኤ ተግባር ላይ እንዲሆን ለመለመን እንደሆነ ተገልጿል።

የጥልቅ ጸሎት ጊዜ ነው

በብፁዕ ካርዲናል ግሬች ስም ለምሥራቅ ካቶሊክ አብያተ ክርስቲያናት መሪዎች እና ለብጹዓን ጳጳሳት ጉባኤዎች ፕሬዚዳንቶች  የቀረበው ይህ ጥሪ፣ በእያንዳንዱ አገር በሚገኙ የብጹዓን ጳጳሳት ጉባኤዎች በሚመረጡ የእመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ቤተ መቅደሶች ዙሪያ ያለውን መንፈሳዊነት ጥልቅ ጸሎት በማቅረብ ለመግለጽ እንደሆነ ታውቋል። የጸሎት ሥነ ሥርዓቱ በቤተ ክርስቲያን የታቀፉ የተለያዩ መንፈሳዊ ማኅበራትን፣ የምዕመናን፣ የካኅናት፣ የገዳማውያን እና ገዳማውያት ማኅበራትን የሚያሳትፍ እንደሚሆን ታውቋል። ከዚህም በተጨማሪ፣ የቁምስና ማኅበረሰብ አባላትም ከሀገረ ስብከታቸው ጳጳስ ጋር በመስማማት ለቅዱስ ሲኖዶስ ጠቅላላ መደበኛ ጉባኤ ስኬታማነት የአፍታ ጸሎት እንዲያደርጉ ተጋብዘዋል።

16 March 2023, 15:48