ፈልግ

ር. ሊ. ጳ. ፍራንችስኮስ በቅድስት መንበር የጳጳሳት ጠቅላይ ጽሕፈት ቤት ተጠሪን በቫቲካን ሲቀበሉ ር. ሊ. ጳ. ፍራንችስኮስ በቅድስት መንበር የጳጳሳት ጠቅላይ ጽሕፈት ቤት ተጠሪን በቫቲካን ሲቀበሉ   (Vatican Media)

ሊቀ ጳጳስ አቡነ ፕሬቮስት፣ ጳጳስ ለምዕመናኑ የቅርብ ሐዋርያዊ እረኛ መሆኑን ገለጹ

በቅድስት መንበር የጳጳሳት ጠቅላይ ጽሕፈት ቤት ተጠሪ የሆኑት ሊቀ ጳጳስ አቡነ ሮቤርት ፕሬቮስ፣ ከቫቲካን የዜና አገልግሎት ጋር ባደረጉት ቃለ ምልልስ፣ ጳጳስ ሐዋርያዊ እረኛ እንጂ ሥራ አስክያጅ አለመሆኑን ገለጹ። ሊቀ ጳጳስ ፕሬቮስት በዚህ ቃለ ምልልሳቸው፥ "ብዙውን ጊዜ ስለ ቤተ ክርስቲያን አስተምህሮ እንጨነቃለን እንጂ የጳጳሳት የመጀመሪያው ተግባር ኢየሱስ ክርስቶስን የማወቅ ውበት እና ደስታን ለሌሎች ማሳወቅ ነው” በማለት ተናግረዋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

በቅድስት መንበር የብጹዓን ጳጳሳት ጠቅላይ ጽሕፈት ቤትን እንዲመሩ የተሰየሙት ሊቀ ጳጳስ አቡነ ሮቤርት ፕሬቮስት የቅዱስ አጎስጢኖስ ማኅበር አባል መሆናቸው ታውቋል። በሰሜን አሜሪካ ቺካጎ ከተማ የተወለዱት ሊቀ ጳጳስ አቡነ ሮቤርት ፕሬቮስት መጀመሪያ በሚስዮናዊነት በኋላም ካርዲናል ማርክ ኦውሌትን እንዲተኩ በርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ከመመረጣቸው በፊት በላቲን አሜሪካ አገር ፔሩ ውስጥ አገልግለዋል። 

“እራሴን እንደ ሚስዮናዊ እቆጥረዋለሁ” ያሉት ሊቀ ጳጳስ አቡነ ፕሬቮስት፣ ጥሪያቸው ልክ እንደ እያንዳንዱ ክርስቲያን፣ አንድ ሰው ባለበት እንኳ ቢሆን ወንጌልን መስበክ እና የወንጌል ልኡክ መሆን ነው” ብለዋል። ወደ ሮም በመምጣት ቤተ ክርስቲያንን እና ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳትን ለማገልገል ዕድል ማግኘታቸውን ገልጸዋል። ከዚህ በፊቱ ከነበራቸው ተልእኮ የተለየ እንደሆነ የገለጹት አቡነ ፕሬቮስት፣ የተጠየቁበት የቤተ ክርስቲያን አገልግሎት የሕይወታቸውን አቅጣጫ ለመመልከት የሚያስችል አዲስ ዕድል መሆኑን ገልጸው፣ ፔሩን ለስምንት ዓመት ተኩል በጳጳስነት እና ወደ ሃያ ዓመታት ለሚጠጋ ጊዜ በሚሲዮናዊነት ካገለገሉ በኋላ ለአዲስ አገልግሎት ወደ ሮም መምጣታቸውን ለቫቲካን የዜና አገልግሎት ገልጸዋል።

ጳጳስ በመጀመሪያ ደረጃ ካቶሊካዊ አመለካከት ሊኖረው እንደሚገባ የገለጹት አቡነ ፕሬቮርት፣ አንዳንድ ጊዜ ጳጳስ የሚኖርበትን አከባቢ ብቻ ለማትኮር እንደሚጋለጥ፣ ነገር ግን አንድ ጳጳስ ስለ ቤተ ክርስቲያኑ እና ስለ እውነታው ሰፋ ያለ ዕይታ ሊኖረው እንደሚገባ እና የቤተ ክርስቲያኗን ሁለንተናዊነት ሊለማመድ ይገባል ብለዋል። ከዚህም በተጨማሪም ሌላውን የማዳመጥ እና ምክር የመጠየቅ ችሎታ እንዲኖረው፣ እንዲሁም ስነ-ልቦናዊ እና መንፈሳዊ ብስለት ሊኖረው ይገባል ብለዋል።

ጳጳስ ራሱን የሚገልጽበት መሠረታዊ ነገር እንደ አባት እና እንደ ወንድም ከሚመለከታቸው ካህናት ጀምሮ ከመላው ማኅበረሰብ ጋር በመቀራረብ ማንንም ወደ ጎን ሳይል ከሁሉም ጋር አብሮ መኖር ነው ብለዋል። ር. ሊ. ጳ. ፍራንችስኮስ ይህን መቀራረብ በአራት ዓይነት መንገድ እንደተመለከቱት የገለጹት ሊቀ ጳጳስ አቡነ ፕሬቮርት፣ እነርሱም ከእግዚአብሔር ጋር መቀራረብ፣ ወንድም ከሆኑት ጳጳሳት ጋር መቀራረብ፣ ከካህናት ጋር መቀራረብ እና የእግዚአብሔር ሕዝብ ከሆኑት ምዕመናን ጋር መቀራረብ መሆኑን አስታውሰው፣ ጳጳስ እራስን ከሌሎች በመነጠል በተወሰነ ማኅበራዊ ደረጃ ወይም በቤተ ክርስቲያን ውስጥ በተወሰነ ደረጃ ረክቶ ለመኖር በሚገፋፋ ፈተና መሸነፍ የለበትም ብለዋል።

ዛሬ ትርጉም በማይሰጥ የስልጣን ሃሳብ ጀርባ መደበቅ የለብንም ያሉት ሊቀ ጳጳስ አቡነ ፕሬቮርት፣ ሥልጣናችን ሌሎችን ማገልገል፣ ካህናትን መደገፍ፣ የመንጋው እረኛ እና አስተማሪዎች መሆን ነው በማለት አስረድተዋል። ብዙውን ጊዜ በቤተ ክርስቲያን አስተምህሮ ላይ ብቻ በማትኮር እና እምነታችንን የምንገጽበት መንገድ ብቻ በመፈለግ፣ ነገር ግን የመጀመሪያው ሥራችን ኢየሱስ ክርስቶስን ማወቅ ምን ማለት እንደሆነ ማስተማር እና ከእርሱ ጋር ያለንን ግንኙነትን መመስከር መሆኑን ልንዘነጋው እንችላለን ብለው፣ መቅደም ያለበት እምነትን እና ኢየሱስ ክርስቶስን የማወቅ ውበት እና ደስታ ለሌሎች ማሳወቅ ነው ብለዋል። በሲኖዶሳዊ ሂደት ወቅት የምናገኛቸው እና የምንጠቀማቸው ሦስቱ ቃላት ማለትም ተሳትፎ፣ አንድነት እና ተልዕኮ መልሶቻችን ናቸው ያሉት ሊቀ ጳጳስ አቡነ ፕሬቮርት፣ ጳጳስም ለዚህ የተጠራ፣ በኅብረት መንፈስ ለመኖር፣ በቤተ ክርስቲያን ውስጥ አንድነትን ለማሳደግ እና ከርዕሠ ጳጳሳት ጋር አንድነት እንዲኖረው የተጠራ መሆኑን አስረድተዋል።

ይህ ማለት ደግሞ ካቶሊካዊነት መሆን ማለት እንደሆነ፣ ያለ ቅዱስ ጴጥሮስ ቤተ ክርስቲያን መሪ እንደሌላት፣ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስም በመጨረሻው እራት ላይ ‘ሁሉም አንድ እንዲሆኑ’ መጸለዩን አስታውሰው፣ “በቤተ ክርስቲያን ውስጥ ማየት የምንፈልገው ይህ አንድነት ነው” ብለዋል። “የዛሬው ኅብረተሰብ እና ባሕል ከኢየሱስ ክርስቶስ ራዕይ ሊያርቁን እንደሚሞክሩ እና ይህ ደግሞ ብዙ ጉዳትን በማስከለተል፣ በአንድነት እጦት ቤተ ክርስቲያን መጎዳቷ ሕመምን የሚያመጣ ቁስል ነው” ብለዋል።

“ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ባስጀመሩት የቤተ ክርስቲያን ዘላቂ ተሃድሶ ውስጥ ትልቅ ዕድል አለ” ያሉት ሊቀ ጳጳስ አቡነ ፕሬቮርት፣ በእውነት በዚህ ወቅት መንፈስ ቅዱስ በቤተ ክርስቲያን ውስጥ እንዳለ እና ለመታደስ እየረዳ መሆኑን ገልጸው፣ በዚህ ሂደትም አዲስ አመለካከትን ለመያዝ ለከፍተኛ ሃላፊነት ተጠርተናል ብለዋል። ይህም ሂደት ብቻ ሳይሆን፣ አንዳንድ የአሠራር ዘዴዎችን መቀየር ብቻ ሳይሆን ወይም ከፍተኛ ጉባኤዎችን ከማካሄድ በበለጠ በመጀመሪያ ደረጃ መንፈስ ቅዱስን ማዳመጥ መቻል እና እሱ ከቤተ ክርስቲያን የሚጠይቀውን መፈጸም እንደሆነ አስረድተዋል። ይህን ለማድረግ በቤተ ክርስቲያን ውስጥ እውነትን የመሻት መንፈስ ማዳመጥን እና እርስ በርስ መደማመጥን መቻል አለብን ብለዋል።

በቤተ ክርስቲያን ሕይወት ጳጳሳዊ አገልግሎት ጠቃሚ እንደሆነ፣ ነገር ግን በሲኖዶሳዊነት መንፈስ ሁሉን ነገር በኅብረት ማከናወን እንደሚገባ፣ ይህም ማለት ደግሞ ሁላችንም አብረን መመላለስ እና እግዚአብሔር የሚጠይቀንን በጋራ መመለስ ማለት እንደሆነ አስረድተዋል። ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ድሃ እና ለድሆች የምትሆን ቤተ ክርስቲያን እንደምታስፈልግ ነግረውናል ያሉት ሊቀ ጳጳስ አቡነ ፕሬቮርት፣ የቀደሙት አወቃቀሮች እና መሠረተ ልማቶች ከአሁን በኋላ የማይፈለጉ እና ለመንከባከብም አስቸጋሪ የሆኑ ሁኔታዎች መኖራቸውን ገልጸው፣ ከዚሁ ጋር በተያያዘ እርሳቸው በሠሩባቸው ቦታዎች ለሕዝብ መሠረታዊ አገልግሎት የሚሰጡ የትምህርትና የጤና ተቋማትን መንግሥት ለማስተባበር ባለመቻሉ ሃላፊነቱን ቤተ ክርስቲያን መውሰድ አለባት ብለዋል።

ማኅበራዊ ሚዲያዎች በሚሊዮን ለሚቆጠሩ ሰዎች የወንጌል መልዕክት ለማስተላለፍ ጠቃሚ መሣሪያ ሊሆኑ እንደሚችሉ የተነአገሩት ሊቀ ጳጳስ አቡነ ፕሬቮርት፣ ማኅበራዊ ሚዲያን በሚገባ ለመጠቀም እራሳችንን ማዘጋጀት አለብን ብለዋል። በተመሳሳይ መንገድም ያለማቋረጥ እየተለዋወጠ በሚገኝ ዓለማችን፣ ከመናገራችን በፊት ወይም በማኅበራዊ ሚዲያዎች ላይ መልዕክት ከመጻፍ በፊት፣ መልስ ለመስጠት ሆነ ጥያቄዎችን ለማቅረብ ጊዜን ውስደን ማሰብ ያስፈልጋል ብለዋል።

06 May 2023, 16:59