ፈልግ

ሊቀ ጳጳስ አቡነ ኢሳኦ ኪኩቺ ከቫቲካን የዜና አገልግሎት ጋር የመጀመሪያ ቃለ ምልልስ ባደረጉበት ወቅት ሊቀ ጳጳስ አቡነ ኢሳኦ ኪኩቺ ከቫቲካን የዜና አገልግሎት ጋር የመጀመሪያ ቃለ ምልልስ ባደረጉበት ወቅት 

ሊቀ ጳጳስ ኪኩቺ፣ የካቶሊክ በጎ አድራጎት ድርጅት የተረሱ ሰዎች ተስፋ እንዲኖራቸው ማገዙን ገለጹ

ዓለም አቀፍ የካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን በጎ አድራጎት ድርጅትን በፕሬዚደንትነት እንዲመሩት የተመረጡት ሊቀ ጳጳስ አቡነ ኢሳኦ ኪኩቺ ከቫቲካን የዜና አገልግሎት ጋር የመጀመሪያቸውን ቃለ ምልልስ አድርገዋል። ሊቀ ጳጳስ አቡነ ኪኩቺ በዚህ ቃለ ምልልሳቸው፣ በየአገራቱ የሚገኙ የድርጅታቸው ሠራተኞች እና በጎ ፈቃደኞች ተባብረው ሰብዓዊ ዕርዳታን በማድረስ ከፍተኛ አገልግሎት ማበርከታቸውን ገልጸው፣ ካቶሊካዊት ቤተ ክርስቲያን በማኅበረሰቡ መካከል የተዘነጉትን በማበረታታት ሐዋርያዊ አገልግሎቷን እንደምታበረክት ገልጸዋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

በጃፓን የቶኪዮ ከተማ ሊቀ ጳጳስ የሆኑት አቡነ ታርሲሲዮ ኢሳኦ ኪኩቺ ከቫቲካን የዜና አገልግሎት ጋር ባደረጉት ቃለ ምልልስ፣ “የበጎ አድራጎት ድርጅቱ ቀዳሚ ተልዕኮ ችግር ውስጥ የሚገኙ ሰዎች የተዘነጉ እንዳይመስላቸው መርዳት ነው” በማለት በ22ኛው የድርጅቱ ጠቅላላ ጉባኤ ላይ ዓለም አቀፍ ድርጅቱን ለአራት ዓመታት እንዲመሩት ለመረጧቸው አራት መቶ ልኡካን ተናግረው፣ አዲሱ ተልዕኮአቸው በችግር ውስጥ ለሚገኙት ሰዎች የሰነቀላቸውን ተስፋ በማብራራት፣ የእግዚአብሔርን ፍቅር በተጨባጭ አገልግሎት በመግለጽ ላይ ለሚገኙ ሥፍር ቁጥር ለሌላቸው በጎ ፈቃደኞች መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል። 

በጎ ተግባር እግዚአብሔር ሕዝቡን እንድሚወድ የሚገልጽበት መንገድ ነው'

ከዓለም አቀፍ ቀይ መስቀል ማኅበር ቀጥሎ የዓለማችን ሁለተኛው ግዙፍ ሰብዓዊ ዕርዳታ አድራጊ ካቶሊካዊ ድርጅት “ካሪታስ”፣ ከበጎ አድራጎት ተግባሩ በላይ ሌሎች አገልግሎቶችንም እንደሚያበረክት የተነገሩት ሊቀ ጳጳስ አቡነ ኪኩቺ፣ “ካሪታስ” ዓለም አቀፍ የበጎ አድራጎት ድርጅት በካቶሊካዊት ቤተ ክርስቲያን ጥላ ሥር ለሚገኙ እና በየአገራቱ ለሚገኙ ካቶሊካዊ የበጎ አድራጎት ድርጅቶች የበላይ እንደመሆኑ፣ እግዚአብሔር ለሕዝቡ ያለውን ፍቅር በተጨባጭ መንገድ ለመመስከር የሚጥር እና ይህንንም የሚያከናውነው የድርጅቱን ባህሪያት በተላበሱ በሁሉም የዓለማችን ክፍሎች በሚገኙ በጎ ፈቃደኞች በኩል መሆኑን ገልጸዋል።

በጎ ፈቃደኞቹ የካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን የበጎ አድራጎት ገጽታን እና በተለይም ግጭቶች በተስፋፉባቸው አካባቢዎች ለሚገኙት እና በተቀረው ዓለም ተረስተው ለቀሩት ሰዎች የዕርዳታ አገልግሎቶችን የሚያበረክቱ መሆናቸውን ሊቀ ጳጳስ አቡነ ኪኩቺ አስረድተው፣ በማከልም ዕርዳታን ከማቅረብ በተጨማሪ ዘወትር ከጎናቸው በመሆን አብረው እንደሚሠሩ፣ እንደሚያስታውሷቸው እና ማንም የተገለለ አለመሆኑን ማረጋገጥ እንደሚፈልጉ ገልጸዋል።

ተስፋን ለመፍጠር በጋራ መጓዝ

“ካሪታስ” ዓለም አቀፍ ካቶሊካዊ ድርጅት የምግብ ዕርዳታን እና ሌሎች ሰብዓዊ ድጋፎችን ለተጎጂዎች እንደሚያቀርብ የተናገሩት አዲሱ ፕሬዝዳንት ሊቀ ጳጳስ አቡነ ኪኩቺ፣ የድርጅታቸው ቀዳሚ ተልዕኮ ተረጂዎቹ ከችግራቸው የሚወጡበት ተስፋ እንዲኖራቸው ማድረግ እና መርዳት እንደሆነ ገልጸው፣ ተስፋውም የትም ሳይሆን በመካከላቸው እንደሚገኝ አስረድተዋል። የበጎ አድራጎት ድርጅቱ ከተቸገሩት ጋር ያለውን ወዳጅነት በማሳደግ አብረው እንደሚጓዝ እና ተስፋቸው ሊሆን እንደሚችል ተናግረዋል።

ሊቀ ጳጳስ አቡነ ኪኩቺ ከቫቲካን የዜና አገልግሎት ጋር ቃለ ምልልስ ሲያደርጉ
ሊቀ ጳጳስ አቡነ ኪኩቺ ከቫቲካን የዜና አገልግሎት ጋር ቃለ ምልልስ ሲያደርጉ

“ካሪታስ ኢንተርናሽናል” ወይም ዓለም አቀፍ የካቶሊክ በጎ አድራጎት ድርጅት ከዓለም አቀፍ ቀይ መስቀል ማኅበር ቀጥሎ ሁለተኛው ግዙፉ የሰብዓዊ ዕርዳታ ድርጅት እንደሆነ፣ በአስቸጋሪ ሁኔታዎች ውስጥ ለሚገኙት ሰዎች ዕርዳታን የሚሰጥ መንግሥታዊ ያልሆነ ድርጅት ቢሆንም፣ መንግሥታዊ ድርጅት አለመሆኑ ብቻ ሳይሆን ከዚያም በላይ የካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን የአገልግሎት ተቋም በመሆኑ  ተልዕኮው ለተራቡት እና ችግር ውስጥ ለወደቁት ምግብን ወይም ሌሎች የዕርዳታ ቁሳቁሶችን ማድረስ ብቻ ሳይሆን ይልቁን የእግዚአብሔርን ፍቅር መመስከር መሆኑን አስረድተዋል።

በካቶሊካዊት ቤተ ክርስቲያን የመለኮታዊ ቃል ሚስዮናውያን ማኅበር አባል መሆናቸውን የገለጹት ሊቀ ጳጳስ አቡነ ኪኩቺ፣ የክኅነት ጸጋን እንደ ጎርጎሮሳውያኑ በ 1986 ዓ. ም. ከተቀበሉበት በኋላ ለሐዋርያዊ አገልግሎት ወደ ምዕራብ አፍሪካ አገር ጋና መላካቸውን ገልጸው፣ በወቅቱ ምዕራፍ አፍሪካን ከፍተኛ ኤኮኖሚያዊ ቀውስ አጋጥሟት እንደነበር በማስታወስ፣ በቂ የሕክምና ዕርዳታን ባለማግኘታቸው የተነሳ በርካታ ሰዎች ሕይወታቸው እንደሚያልፍ እና የኤችአይቪ ኤይድስ ስርጭትም ከፍተኛ እንደነበር ገልጸዋል።

ሊቀ ጳጳስ አቡነ ኪኩቺ በቫቲካን የዜና አገልግሎት ዋና ማዕከል በተገኙበት ወቅት
ሊቀ ጳጳስ አቡነ ኪኩቺ በቫቲካን የዜና አገልግሎት ዋና ማዕከል በተገኙበት ወቅት

የዕርዳታ ምግቦችን እና ቁሳቁሶችን ከውጭ በማስገባት ለተቸገሩት መስጠት እንደሚችሉ የገለጹት አቡነ ኪኩች፣ “ተስፋን ከውጭ ማምጣት እንደማይችሉ፣ ተስፋ በሰዎች ልብ ውስጥ መፈጠር አለበት” ብለዋል። ከተቸገሩት ጋር ወዳጅነትን በመፍጠር አብረው መጓዝ እንደሚችሉ፣ ሰዎች የተረሱ እንዳልሆኑ እርግጠኞች እንዲሆኑ ማድረግ እና በዚህም የመዳን ተስፋን በልባቸው ውስጥ መፍጠር እንደሚችሉ አስረድተዋል።

የካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን በጎ አድራጎት ድርጅት “ካሪታስ” የእግዚአብሔርን ፍቅር በተጨባጭ እንደሚመሰክር የገለጹት ሊቀ ጳጳስ አቡነ ኪኩቺ፣ ድርጅታቸው በከፍተኛ የአስተዳደር እርከኖች ላይ የሚገኙት ሰዎች ስብስብ ብቻ ሳይሆን ከመሠረት የሚገኙ በጎ ፈቃደኞችንም የሚያካትት በመሆኑ እያንዳንዱ የድርጅታቸው በጎ ፈቃደኛ የበጎነት ባህሪያትን መላበስ አስፈላጊ እንደሆነ ገልጸው፣ ከበጎ ፈቃደኞች ጋር በመተባበር የቤተ ክርስቲያኒቱን የበጎ አድራጎት ድርጅት እንደሚፈጥሩ አስረድተዋል።

15 May 2023, 13:44