ፈልግ

ብጹዕ ካርዲናል ማርዮ ግሬች ብጹዕ ወቅዱስ ፓትሪያርክ ታዋድሮስ ዳግማዊን በጽ/ቤታቸው ተቀብለው ብጹዕ ካርዲናል ማርዮ ግሬች ብጹዕ ወቅዱስ ፓትሪያርክ ታዋድሮስ ዳግማዊን በጽ/ቤታቸው ተቀብለው 

ብጹዕ ወቅዱስ ፓትሪያርክ ታዋድሮስ ዳግማዊ ለካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን ሲኖዶሳዊ ጉዞ ቡራኬን ሰጡ

የግብጽ ኮፕት ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን ፓትሪያርክ ብጹዕ ወቅዱስ ታዋድሮስ ዳግማዊ ከከፍተኛ መንፈሳዊ ልኡካን ቡድናቸው ጋር ሆነው በካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን የጳጳሳት ሲኖዶስ ጠቅላይ ጸሐፊ ከሆኑት ብጹዕ ካርዲናል ማርዮ ግሬች ጋር ዓርብ ግንቦት 4/2015 ዓ. ም. ተገናኝተዋል። ብጹዕ ወቅዱስ ፓትሪያርክ ታዋድሮስ ዳግማዊ የብጹዓን ጳጳሳት ሲኖዶስ ጠቅላይ ጽሕፈትን በጎበኙበት ወቅት እንደተናገሩት፣ እንደ ጎርጎሮሳውያኑ በ 2021 ዓ. ም. የተጀመረው ሲኖዶሳዊ ጉዞ "ከምሥራቅ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን ጋር ለመቀራረብ ተጨማሪ እና ጠቃሚ እርምጃ ነው" በማለት ቡራኬአቸውን ሰጥተዋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

የአሌክሳንደሪያው ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት፣ የቅዱስ ማርቆስ መንበረ ፓትርያርክ ሊቃነ ጳጳሳት እና የግብጽ ኮፕት ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን ፓትሪያርክ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ታዋድሮስ ዳግማዊ እና በእርሳቸው የተመራውን ከፍተኛ የልኡካን ቡድንን በጽሕፈት ቤታቸው ተቀብለው ንግግር ያደረጉት የካቶሊክ ጳጳሳት ሲኖዶስ ጠቅላይ ጸሐፊ ብጹዕ ካርዲናል ማርዮ ግሬች፣ "መንፈስ ቅዱስን ማድመጥ እናውቅ ዘንድ ሲኖዶሳዊ ጉዞአችንን ይባርኩልን እርስዎን እና ቤተ ክርስቲያንዎን በትህትና እንጠይቃለን” ብለዋል። 

የካርዲናል ማርዮ ግሬች ንግግር

የጳጳሳት ሲኖዶሱ ሁለት ምክትል ዋና ጸሐፊ ከሆኑት ሞንሲኞር ሉዊስ ማሪን ደ ሳን ማርቲን እና እህት ናታሊ ቤክኳርት ጋር ሆነው ለከፍተኛ መንፈሳዊ የልኡካን ቡድን ንግግር ያደረጉት ብፁዕ ካርዲናል ማርዮ ግሬች በካቶሊካዊት ቤተ ክርስቲያን በመካሄድ ላይ ስለሚገኝ ሲኖዶሳዊ ሂደት በማብራራት፣ ሂደቱ የምሥራቅ ቤተ ክርስቲያን ባሕል መሆኑን በማስታወስ፣ ካቶሊካዊት ቤተ ክርስቲያን በጋራ የቤተ ክርስቲያን ሕይወት ውስጥ ከፍተኛ ትርጉም ያለውን የምእመና ተሳትፎን በተሻለ ሁኔታ ለመግለጽ እንዲረዱ በማለት ጠይቀዋል።

ወደ ምሥራቅ ኦርቶዶክስ ለመቅረብ የተደረገ አዲስ እርምጃ

የምሥራቅ አብያተ ክርስቲያናት መልካም የመንፈሳዊ ሥልጣን ክፍፍልን እንድናበረታታ፣ ክልላዊ እና አውራጃዊ የሲኖዶሳዊነት ደረጃዎችን በተሻለ ሁኔታ በመጠቀም አንድነቷን የጠበቀች ቤተ ክርስቲያንን ለመገንባት እንደሚያበረታቱ ብፁዕ ካርዲናል ማርዮ ግሬች በንግግራቸው ገልጸዋል።

የካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን ጳጳሳት ሲኖዶስ ጠቅላይ ጸሐፊ ብጹዕ ካርዲናል ማሪዮ ግሬች በመጨረሻም “እንደ ጎርጎሮሳውያኑ በ2021 ዓ. ም. በርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮ የተጀመረው ሲኖዶሳዊ ጉዞ ከምሥራቅ ኦርቶዶክሳዊት ቤተ ክርስቲያን ጋር ላለው መቀራረብ ተጨማሪ እና ጠቃሚ እርምጃ ነው" ሲሉ ያላቸውን እምነት ገልጸዋል።

የአሌክሳንደሪያው ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ብፁዕ ወቅዱስ ፓትሪያርክ ታዋድሮስ ዳግማዊ በበኩላቸው የግብጽ ኮፕት ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን ሕይወት መካከል አንዳንድ ገጽታዎችን ያቀረቡ ሲሆን፣ በግብጽ የማዲ እና ኤል ባሳቲን ከተማ ሊቀ ጳጳሳት ብጹዕ አቡነ ዳንኤል ስለ ቤተ ክርስቲያናቸው ሲኖዶሳዊ የሥራ ሂደት አብራርተዋል።

በግብጽ ኮፕት ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን ፓትሪያርክ በብፁዕ ወቅዱስ ፓትሪያርክ ታዋድሮስ ዳግማዊ ከተመራው ከፍተኛ ልኡካን ቡድን ጋር ከአንድ ሰዓት በላይ የፈጀው ስብሰባ በታላቅ መተሳሰብ እና ወንድማማችነት መንፈስ መካሄዱን የሲኖዶሱ ጠቅላይ ጽሕፈት ቤት በመግለጫው አስታውቋል።

13 May 2023, 17:09