ፈልግ

በቅድስት መንበር የስብከተ ወንጌል አገልግሎት ጳጳሳዊ ጽሕፈት ቤት ጋዜጣዊ መግለጫ በቅድስት መንበር የስብከተ ወንጌል አገልግሎት ጳጳሳዊ ጽሕፈት ቤት ጋዜጣዊ መግለጫ  (VATICAN MEDIA Divisione Foto)

ቫቲካን የኢዮቤልዩን የቀን መቁጠሪያ ድረ ገጽ እና መተግበሪያ ይፋ አደረገች

በቅድስት መንበር የስብከተ ወንጌል አገልግሎት ጳጳሳዊ ጽሕፈት ቤት እንደ ጎርጎሮሳውያኑ በ2025 ዓ. ም. ለሚከበረው የኢዮቤልዩ ቅዱስ ዓመት ዝግጅት የሚረዳ የቀን መቁጠሪያ ድረ ገጽ እና መተግበሪያ ይፋ ከማድረግ በተጨማሪ የኢዮቤልዩ መዝሙር ውድድር አሸናፊንም አስታውቋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

በጳጳስዊ ጽሕፈት ቤቱ የበዓሉ አስተባባሪ መምሪያ አባላት ማክሰኞ ግንቦት 1/2015 ዓ. ም. በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ፣ በዓሉን በድምቀት ለማክበር እንዲያስችሉ የታቀዱ በርካታ ፕሮጀክቶችን እና እስካሁን የተካሄዱ የቅድመ ዝግጅት ሥራዎችን በዝርዝር ተናግረዋል። ዝግጅቱን ለማስተባበር የተሰየሙት እና የጳጳስዊ ጽሕፈት ቤቱ ዋና አስተዳዳሪ የሆኑት ሊቀ ጳጳስ አቡነ ሪኖ ፊዚኬላ ዝግጅቱ በፍጥነት እየተካሄደ እንዳለ እና ወደ ከፍተኛ ደረጃ መድረሱን በመግለጫቸው ተናግረዋል።

እንደ ጎርጎሮሳውያኑ በ 2025 ዓ. ም. ወደ ሮም እንደሚመጡ የሚጠበቁ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ምዕመናንን ለመቀበል የሚያስፈልጉ የመሠረተ ልማት አውታሮችን እውን ለማድረግ ከጣሊያን መንግሥት እና የላሲዮ ክፍለ ሀገር ባለ ሥልጣናት እና ከሮማ ከተማ አስተዳደር ጋር ተከታታይ ስብሰባዎችን ከማድረግ በተጨማሪ፣ ባለፈው ዓመት በቅድስት መንበር የስብከተ ወንጌል አገልግሎት ጳጳሳዊ ጽሕፈት ቤት አጠቃላይ መርሃ ግብሩን የሚከታተሉ አራት ኮሚሽኖችን እና የቴክኒክ ኮሚቴዎችን ማቋቋሙ ይታወሳል።

አራት ኮሚሽኖች የትኞቹ ናቸው?

እነዚህም የሐዋርያዊ አገልግሎት ኮሚሽን፣ የእያንዳንዱ የቅድስት መንበር ጳጳሳዊ ጽሕፈት ቤቶች ተወካዮች እና አንዳንድ የቤተ ክርስቲያን አካላት ሐዋርያዊ አገልግሎት የግንኙነት መምሪያ ተወካዮችን ያቀፈ የሥራ ቡድን እና ዓላማው በተለይ በአጥቢያ ቤተ ክርስቲያናት ውስጥ የቅድመ ዝግጅት ሥራዎችን የሚያስተዋውቁትን ያካትታል። ባህላዊ እንቅስቃሴዎችን በማስተዋወቅ ረገድ ኤግዚቢሽኖችን፣ ኮንሴርቶችን እና የተለያዩ ትርዒቶችን የሚያስተባብር የባህል ኮሚሽን የተቋቋመ ሲሆን እነዚህ ኮሚሽኖች በተጨማሪም የንግደትን መንፈሳዊ ልምዶችን የሚያዳብሩ እና የሚያበለጽጉ ናቸው።

የ “ኤል ግሬኮ” ኤግዚቢሽን በቫቲካን

እነዚህ የዝግጅት ተግባራት በመጭው መስከረም ወር በቫቲካን ውስጥ በሚቀርቡ ሦስት የስፔን አርቲስት ኤል ግሬኮ ድንቅ ሥራዎች፥ የኢየሱስን ጥምቀት፣ ኢየሱስ መስቀል መሸከሙን እና የኢየሱስን ቡራኬ በሚያሳይ ኤግዚቢሽን እንደሚጀምሩ ሊቀ ጳጳስ አቡነ ሪኖ ፊዚኬላ ገልጸዋል። የመጀመሪያ ዙር የሆነው ይህ “ምሳሌያዊ ክስተት”፣ ሊቀ ጳጳስ አቡነ ፊዚኬላ እንደተናገሩት ጎብኚዎች “በክርስቶስ ተስፋ” ላይ ለማሰላሰል እንደሚረዳቸው እና የ2025 ዓ. ም. ኢዮቤልዩ ዓመት መሪ ቃል የሆነው “የተስፋ ተጓዦች” የሚለውን ለማስገንዘብ የሚረዳ መሆኑን አስረድተዋል።

"የጉባኤው ማስታወሻ ደብተሮች" ህትመት እና ትርጉም

በር. ሊ. ጳ. ፍራንችስኮስ ጥያቄ መሠረት ለሁለተኛው የቫቲካን ጉባኤ 60ኛ ዓመት መታሰቢያ በዓል የሚሆኑ አራት ሰነዶችን የያዙ 35 መጠነኛ የጉባኤው ማስታወሻ ደብተሮችን ጳጳሳዊ ጽሕፈት ቤቱ አሳትሟል። የማስታወሻ ደብተሩ በስፔን ብጽዓን ጳጳሳት ጉባኤ ትብብር በስፓንኛ ቋንቋ ተተረጉሞ የቀረበ ሲሆን እንደዚሁም ሌሎች የጳጳሳ ጉባኤዎችም የሜክሲኮ፣ የብራዚል፣ የቼክ ብጹዓን ጳጳሳት ጉባኤዎች እና በሕንድም በእንግዚኛ ቋንቋ በመዘጋጀት ላይ እንደሚገኙ ታውቋል።   

የኢዮቤልዩ መዝሙር ውድድር አሸናፊ

ሊቀ ጳጳስ አቡነ ሪኖ ፊዚኬላ በጋዜጣዊ መግለጫቸው እንዳስታወቁት፣ ጳጳስዊ ጽሕፈት ቤታቸው የኢዮቤልዩ መዝሙር ውድድር አሸናፊንም ይፋ ማድረጉን አስታውቀዋል። ውድድሩን ያሸነፈው ጣሊያናዊ የዜማ መምህር ፍራንችስኮስ ሜኔጌሎ ሲሆን ባጋዜጣዊ መግለጫው ወቅት በግንባር ቀደምትነት ከተጠቀሱት ርዕሠ ጉዳዮች መካከል አንዱ የቅዱስ ዓመት የቀን መቁጠሪያ እና የኢዮቤልዩ ድረ ገጽ ዝግጅት ነው። ድረ ገጹ ለጊዜው በኢዮቤልዩ ዓመት ውስጥ የሚከበሩ ትላልቅ በዓላትን፥ የወጣቶችን ኢዮቤልዩ፣ የልዩ ልዩ ማኅበራት ዝግጅቶችን፣ የትምህርተ ክርስቶስ መምህራንን፣ ልዩ ልዩ ሥራዎችን እና ትምህርት ቤቶችን የሚያስተዋውቅ ሲሆን፣ የኢዮቤልዩ ዓመት እስኪደርስ ድረስ እየሰፋ እንደሚሄድ ተመልክቷል። የድረ ገጹ ጎብኚዎች  ወደ ኢዮቤልዩ ማዕከል በመሄድ ሰኔ ወር መጀመሪያ ላይ ተመርቆ ሙሉ አገልግሎቱን ከሚጀምር የመረጃ ቋት ጠቃሚ መረጃዎችን ማግኘት እንደሚችሉ ተነግሯል።

ለነጋዲያን የተዘጋጀ መታወቂያ

ነጋዲያንን በሚመለከት የድረ ገጹ ክፍል ገብተው ከተመዘገቡ በኋላ የሚፈልጉ አገልግሎቶችን ማግኘት እንደሚችሉ ተገልጿል። ጎብኚዎቹ ምዝገባውን ካጠናቀቁ በኋላ በሚሰጣቸው የመታወቂያ ኮድ የተለያዩ በኢዮቤልዩ ዓመት የሚቀርቡ ዝግጅቶችን እና ነጋዲያኑም በኢዮቤልዩ ቅዱስ በር ለማለፍ ዝግጅት ማድረግ እንደሚችሉ ተነግሯል።          

   የኢዮቤልዩ መተግበሪያ

ከመጪው መስከረም ወር ጀምሮ የማኅበራዊ ሚዲያዎች ገጾች እና የኢዮቤልዩ መተግበሪያ በይፋ አገልግሎት መስጠት እንደሚጀምሩ ታውቋል። የኢዮቤልዩ በዓል ዝግጅቶችን እና ዜናዎችን መተግበሪያውን በእጅ ስልኮች ላይ ከጫኑ በኋላ ከዋናው ድረ ገጽ ማግኘት እንደሚቻል እና በተጨማሪም ለኢዮቤልዩ በዓል ዝግጅቶች ከተመዝገቡ ቀላል እና ፈጣን በሆነ መንገድ ግላዊ መረጃዎችንም ለመለዋወጥ አማራጭ እንዳለ ታውቋል።   

 

10 May 2023, 16:30