ፈልግ

በአሜሪካ የናሳ የጠፈር ምርምር ዕቅድ በአሜሪካ የናሳ የጠፈር ምርምር ዕቅድ  (ANSA)

“የጠፈር ኤኮኖሚ እጣ ፈንታ እና ትርጉሙ” በሚል ርዕሥ ስብሰባ መካሄዱ ተገለጸ

የተቀናጀ የሰው ልጅ ልማትን ለማበረታታት እና አዳዲስ ቴክኖሎጂዎች በጠረፍ ኢኮኖሚ ላይ በሚያሳድሩት ማኅበራዊ እና ፖለቲካዊ ተግዳሮቶች የተመለከተ ስብሰባ መካሄዱ ተገለጸ። በቅድስት መንበር የሰው ልጅ ሁለንተናዊ ዕድገት አገልግሎት ጳጳሳዊ ጽሕፈት ቤት ሐምሌ 14/2015 ዓ. ም. ባዘጋጀው ስብስባ ላይ ዓለም አቀፍ ባለሙያዎች እና ባለ ድርሻ አካላት መገኘታቸው ታውቋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

በጳጳሳዊ ጽሕፈት ቤት አስተባባሪነት ቫቲካን ውስጥ የተካሄደው ስብሰባው አዳዲስ ቴክኖሎጂዎች በጠፈር ኤኮኖሚ መስክ ላይ ከሚያሳድሩት ተጽእኖ ጋር የተያያዙ አዳዲስ ማኅበራዊ እና ፖለቲካዊ ተግዳሮቶችን ወደ አዲስ አጠቃላይ የሰው ልጅ ልማት እና ሰላም ለማምጣት ያለመ እንደነበር ታውቋል። ዕውቅና ያላቸው ዓለም አቀፍ ባለሙያዎች እና ባለ ድርሻ አካላት ሳይንሳዊ፣ ማኅበራዊ እና ፖለቲካዊ ትንታኔዎችን በማቅረብ አዳዲስ ቴክኖሎጂዎችን ለሰው ልጅ ልማት እንዴት መጠቀም እንደሚቻል የሚያሳዩ ጥናታዊ ጽሑፎቻቸውን አቅርበዋል።

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ “ውዳሴ ላንተ ይሁን” በሚለው ሐዋርያዊ ቃለ ምዕዳናቸው ቁ. 112 ላይ “ራዕያችንን እንደገና በማሳደግ ቴክኖሎጂን ለመገደብ እና ለመምራት ባለን ነፃነት ጤናማ፣ የበለጠ ሰብዓዊ እና ማኅበራዊ የዕድገት አገልግሎቶችን ማቅረብ እንችላለን” በማለት ያቀረቡትን ራዕይ መሠረት በማድረግ፥ በስብሰባው ላይ የህዋ ቴክኖሎጂዎች በማኅበራዊ ልማት እና በጋራ መኖሪያ ምድራችን ላይ ያላቸውን ተፅእኖ እና የሚሰጡ ጥቅሞችን የተመለከቱ ወሳኝ ጥያቄዎች ቀርበዋል።

የቀድሞ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ቅዱስ ጳውሎስ 6ኛ እንደ ጎርጎሮሳውያኑ ሐምሌ 21/1969 ዓ. ም. ለጠረፍ ተመራማሪዎች ባስተላለፉት ሐዋርያዊ መልዕክት፥ "የዲጂታል ዘመን የቦታ፣ የጊዜ እና የአካል ግንዛቤን በመለወጥ የሰው ልጅ ሕልውና ድንበር ሳይሆን ወሰን የሌለው የጠፈር ስፋት ለአዳዲስ አጠቃላይ የሰው ልጅ ልማት እና ሰላም ክፍት ነው” ማለታቸውም በስብሰባው ላይ ተጠቅሷል።

“ከአሁን በኋላ ወጥነት ያለው ዓለም የለም”

የፋይናንስ ቀውሶች፣ ወረርሽኞች እና ጦርነቶች በአጠቃላይ የሰው ልጅ እንቅስቃሴ ላይ ተጽዕኖ ማሳደራቸውን እና በዓለም የመተዳደሪያ ደንቦች እና ክስተቶች ላይ ጫናዎችን መፍጠሩን ስብሰባው ገልጾ፥   በራዕያዊ አነጋገር ከአሁን በኋላ ወጥ በሆነ ዓለም ውስጥ መኖር እንደማይቻል ገልጿል። ወጥነት አብረው መቆየት በሚችሉ ሃሳቦች መካከል እንደሚገኝ የገለጸው ስብሰባው፥ አንድነትን ማምጣት የሚቻለው በነጠላ ስሜት ብቻ ሳይሆን፥ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ እንደ ጎርጎሮሳውያኑ መጋቢት 27/2020 ዓ. ም. ከቅዱስ ጴጥሮስ ባዚሊካ ለመላው ዓለም እና ለሮም ከተማ ሕዝብ ባስተላለፉት መልዕክት፥ “አንድነትን የሚፈጥር ቃል በተቃራኒ ሃሳቦች ላይ በነፃነት በአሁኑ ወቅት ሊከሰቱ የሚችሉ ችግሮችን ሁሉ ለመቀበል ድፍረት ይሰጠናል” ማለታቸውን ጠቅሶ፥ "ለምን ትፈራላችሁ? እምነት የላችሁምን? ጌታ ሆይ! ቃልህ ዛሬ ማታ የሁላችንንም ልብ ይነካል” ማለታቸውን አስታውሷል።

ከመላው ዓለም የመጡ ባለሙያዎች

በቅድስት መንበር የሰው ልጅ ሁለንተናዊ ዕድገት አገልግሎት ጳጳሳዊ ጽሕፈት አስተባባሪነት ሐምሌ 14/2015 ዓ. ም. የተካሄደውን ስብስባ በንግግር የከፈቱት የቀድሞ የናሳ የጠፈር ምርምር ዋና የመረጃ ኦፊሰር የነበሩት ወ/ሮ ሬኒ ዊን፥ "የህዋ ኤኮኖሚ አዳዲስ ዕድሎች እና ትርጉም" በሚለው ርዕስ በኩል ጠቅላላ ማብራሪያ ሰጥተዋል። በናሳ የጠፈር ምርምር የቀድሞ የመረጃ ኦፊሴር የነበሩት አቶ ስቲፌን ኦርሊዬን ኮቫችም በበኩላቸው፥ "ለድህረ-ኳንተም ዓለም መዘጋጀት" በሚል ርዕሥ ጥናታዊ ጽሑፋቸውን አቅርበዋል። በጣሊያን በሚገኝ ቦኮኒ ትምህርት ቤት ውስጥ የአስተዳደር ትምህርት፣ የህዋ ፊዚክስ ጥናት እና ኤኮኖሚ መምህር እንዲሁም በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የህዋ ሳይንስ ጉዳዮች ጽሕፈት ቤት ተጠሪ የነበሩት ወ/ሮ ሲሞኔታ ዲ ፒፖ፥ የህዋ ኤኮኖሚ ለማኅበራዊ እና ኤኮኖሚያዊ ዘላቂ ልማት የሚያበረክተውን አስተዋጽኦ በማስመልከት ለስብሰባው ተካፋዮች ንግግር አድርገዋል። በመጨረሻም የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት እስከ 2030 ዓ. ም. ተግባራዊ ለማድረግ ያቀደውን የዘላቂ ልማት ግቦች ለማሳክት በዲጅታል ዓለም የትምህርት አስፈላጊነት በማስመልከት በዓረቡ ዓለም “SEEDS” የተባለ ድርጅት መስራች የሆኑት ዶ/ር ሂንድ አቡ ናስር ካሲር የቪዲዮ ቅንብር አሳይተዋል።

በቅድስት መንበር የሰው ልጅ ሁለንተናዊ ዕድገት አገልግሎት ጳጳሳዊ ጽሕፈት አስተባባሪነት ሐምሌ 14/2015 ዓ. ም. የተካሄደውን ስብስባ በንግግር የከፈቱት የጳጳስዊ ጽሕፈት ቤቱ ምክትል ዋና ጸሐፊ አቡነ አንቶኒ ኦኚየሙኬ ኤክፖ ሲሆኑ ስብሰባውን የመሩት አቶ አሌሲዮ ፔኮራሪዮ እንደነበሩ ታውቋል።ለስብሰባው ዝግጅት ድጋፋቸውን ለገለጹት፥ የ “ሁላችንም ወንድማማቾች ነን” ፋውንዴሽን እና "ባንካ ኢንተዛ ሳን ፓውሎ" ለተባለ የጣሊያን ባንክ ምስጋና ቀርቦላቸዋል። 

24 July 2023, 15:00