ፈልግ

እህት ሔለን አልጎርድ የማኅበራዊ ሳይንስ ጳጳሳዊ አካዳሚ ባዘጋጀው ጉባኤ ላይ ተገኝተው ንግግር ሲያደርጉ እህት ሔለን አልጎርድ የማኅበራዊ ሳይንስ ጳጳሳዊ አካዳሚ ባዘጋጀው ጉባኤ ላይ ተገኝተው ንግግር ሲያደርጉ 

ቫቲካን፥ ሰላም በምድር ላይ በሚል ርዕሥ የተዘጋጀ ጉባኤ ማስተናገዷ ተገለጸ

ቫቲካን፥ የቀድሞው ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ቅዱስ ዮሐንስ 23ኛ “ሰላም በምድር ላይ” በሚለው ሐዋርያዊ ቃለ ምዕዳናቸው ውስጥ ያቀረቡትን ትምህርቶች መሠረት ያደረገ ጉባኤ አስተናገደች። ሐዋርያዊ ቃለ ምዕዳናቸው የታተመበትን ስልሳኛ ዓመት መታሰቢያን ምክንያት በማድረግ በተዘጋጀው ጉባኤ ላይ ልዩ ልዩ ባለሙያዎች ተሳትፈው፥ ጦርነት የማይካሄድበት ዓለምን ለመገንባት በሚደረገው ጥረት ላይ ውይይት አካሂደዋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

የርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ዮሐንስ 23ኛ የታሪክ ማህደር የሆነውን “ሰላም በምድር ላይ” የሚለውን ሐዋርያዊ ቃለ ምዕዳን ከታተሙ እነሆ 60 ዓመታት አልፈዋል። የመታሰቢያ ዓመቱን ምክንያት በማድረግ የቫቲካን የማኅበራዊ ሳይንስ ጳጳሳዊ አካዳሚ ኦስሎ ከተማ ከሚገኝ የሰላም ምርምር ኢንስቲትዩት (PRIO) ጋር በመሆን “ሰላም በምድር ላይ፥ ጦርነት እና ሌሎች እንቅፋቶች” በሚል ርዕሥ ሁለት ቀናት የሚቆይ ጉባኤ አዘጋጅቷል።

ከጉባኤው ጎን ለጎን የቫቲካን ዜና አገልግሎት ባልደረባ አሌሳንድሮ ዲ ቡሶሎ በርካታ የጉባኤውን ታዳሚዎች ያነጋገረ ሲሆን፥ ከእነዚህም መካከል የማኅበራዊ ሳይንስ ጳጳሳዊ አካዳሚ ተጥሪ እህት ሔለን አልፎርድ፣ በኦስሎ ከሚገኝ የሰላም ምርምር ኢንስቲትዩት (PRIO) ከፍተኛ ተመራማሪ ዶክተር ማሪያን ዳህል እና የማኅበራዊ ሳይንስ ጳጳሳዊ አካዳሚ ቻንስለር ብጹዕ ካርዲናል ፒተር ታርክሰን ይገኙበታል።

ጉባኤውን በተመለከተ

ጉባኤውን ለማዘጋጀት ያነሳሱ ሁለት ዋና ዋና ምክንያቶች እንዳሉ የጠቀሱት ብፁዕ ካርዲናል ታርክሰን፥ የመጀመሪያው የሐዋርያዊ ቃለ ምዕዳኑ ስልሳኛ ዓመት መታሰቢያን እና ሁለተኛው ሐዋርያዊ ቃለ ምዕዳኑ እንደገና በግጭት በተሰቃየች ዓለም ውስጥ ያለውን ጠቀሜታ ማደሱን ገልጸው፥ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ የዛሬዎቹ ግጭቶች አልፎ አልፎ የሚካሄዱ “ሦስተኛው የዓለም ጦርነቶ ናቸው” ማለታቸውን ካርዲናሉ አስታውሰዋል።

እህት ሔለን አልፎርድ የጉባኤውን ዋና ጭብጥ በማስፋት ባደረጉት ንግግር፥ “አሁን ያለው ሁኔታ ከ1960ዎቹ ጋር ተመሳሳይ ባይሆንም ነገር ግን በሰው ሠራሽ አስተውሎት የተመሩ የጦር መሣሪያዎች፣ የሳይበር አጠቃቀሞች፣ ራስን በራስ የሚቆጣጠር መሣሪያ መጠቀምን ጨምሮ ብዙ አዳዲስ ስጋቶች ገጥመውናል” ብለዋል። አዲስ ዓይነት የጦር መሣሪያ ሥርዓቶች በትክክል ሊተገበሩ አለበለዚያም ሙሉ በሙሉ ሊወገዱ እንደሚገባም አክለዋል።

የፀረ-ጦርነት እንቅስቃሴ ችግሮች

በኦስሎ የሰላም ምርምር ኢንስቲትዩት (PRIO) ከፍተኛ ተመራማሪ ዶክተር ማሪያን ዳህል በበኩላቸው፥ ለሰላም ሌላ ከባድ እንቅፋት ነው ባሉት ንግግራቸው፥ የፀረ-ጦርነት እንቅስቃሴ ስኬታማነት እያሽቆለቆለ መሄዱን ገልጸው፥ የሰላማዊ ዘመቻዎች መልካም ውጤት ዛሬ ከቀድሞው ያነሰ ነው" ብለዋል።

የችግሩ አንዱ አካል ፀረ-ጦርነት ቡድኖችን ሠርጎ መግባት እንደሆነ የገለጹት ዶክተር ማሪያን ዳህል፥ ጥቂት ፈላጭ ቆራጮች ሰላማዊ እንቅስቃሴዎች ወደ ጭካኔ እንዲለወጡ ለማድረግ ሠርጎ ገቦችን ወደ እንቅስቃሴው እየላኩ መሆኑን ገልጸዋል። ሆኖም ግን ሰላማዊ እንቅስቃሴዎቹ እየተማሩ እና ስልቶቻቸውንም እያራመዱ እንዴት መንቀሳቀስ እንደሚችሉ እየተረዱ መምጣታቸውን ተናግረው፥ ስለሆነም ወደ ወርቃማው የሕዝባዊ ንቅናቄ ዘመን እንመለሳለን ብለን የማናስብበት ምንም ምክንያት የለም ብለዋል።

ዶ/ር ማሪያን ዳህል ጉባኤው ላይ ንግግር ሲያደርጉ
ዶ/ር ማሪያን ዳህል ጉባኤው ላይ ንግግር ሲያደርጉ

ከር. ሊ. ጳ. ቅዱስ ዮሐንስ 23ኛ የተወሰዱ ትምህርቶች

“ዓለም እንዲህ ያሉ ችግሮች ሲያጋጥሙት ምን ምላሽ መስጠት አለበት? ምንስ ሊደረግ ይገባል?” በማለት የጠየቁት እህት ሔለን አልፎርድ፥ “ቢያን ከሁሉ የከፋውን የጦርነት ገጽታ በመገደብ ሰላምን ማሳደግ እና “ሰላም በምድር ላይ” የሚለው ሐዋርያዊ ቃለ ምዕዳን አስቀድሞ ወደ ተመለከተው እና ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ እየገፋፉ ወዳሉበት፥ ጦርነት ወደሌለበት ዓለም ለመጓዝ መሞከር ነው ብለዋል። ብፁዕ ካርዲናል ታርክሰንም እንደዚሁ፥ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ቅዱስ ዮሐንስ 23ኛ የሰላም ባሕልን ለማሳደግ ባቀረቧቸው አምስቱ አምዶች ላይ የተመሠረተ የአዲስ አስተሳሰብ አስፈላጊነትን በማሳሰብ እነሱም፥ ሰብዓዊ ክብርን ማስጠበቅ፣ የጋራ ጥቅም፣ ነፃነት፣ እምነት እና ፍቅር እንደሆኑ አስረድተዋል። ሁለቱም በንግግራቸው፥ “ሰላም በምድር ላይ” በሚል ርዕሥ የተዘጋጀው ጉባኤ ይህንን ዓላማ ለማራመድ አቅም እንዳለው እርግጠኞች መሆናቸውን ገልጸዋል።

እህት ሔለን አልፎርድ ንግግራቸው ሲያጠቃልሉ፥ በጉባኤው ላይ የተገኙት ሰዎች በአዲሶቹ ቴክኖሎጂዎች ላይ ባሏቸው በርካታ ብቃቶች፣ በሥነ-ምግባር እና በቴክኖሎጂዎች ሕጋዊ ደንብ ውስጥ ባሏቸው ብቃቶች በመታገዝ ጥሩ መልስ ለመስጠት በጋራ ሊሠሩ እንደሚችሉ ገልጸው፥ ለወደፊት የተሻሉ ሥርዓቶች ግንባታ የበኩላቸውን አስተዋጽኦ በማበርከት ዓመፅን ለመቆጣጠር እና ሰላምን ማስፈን እንደሚችሉ ተናግረዋል።

“ሰላም በምድር ላይ፥ ጦርነት እና ሌሎች እንቅፋቶች” በሚል ርዕሥ የተዘጋጀ ጉባኤ
“ሰላም በምድር ላይ፥ ጦርነት እና ሌሎች እንቅፋቶች” በሚል ርዕሥ የተዘጋጀ ጉባኤ

 

21 September 2023, 13:01