ፈልግ

በፖቱጋል መዲና ሊዝበን በተከበረው የዓለም ወጣቶች ቀን የተሳተፉ በጎ ፈቃደኞች በፖቱጋል መዲና ሊዝበን በተከበረው የዓለም ወጣቶች ቀን የተሳተፉ በጎ ፈቃደኞች  

በመጭው የኢዮቤልዩ በዓል ወቅት የሚከበረው የዓለም ወጣቶች ቀን የተስፋ ጥሪ በዓል መሆኑ ተገለጸ

የክርስቲያናዊ ተስፋ ትርጉም በማጠናከር ኢየሱስ ክርስቶስ ሕያው መሆኑን በደስታ መመስከር እንደሚገባ፥ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ፥ እንደ ጎርጎርሳውያን በ2023 እና በ2024 ዓ. ም. በሀገረ ስብከት ደረጃ ለሚከበሩ ሁለት የወጣቶች ቀን በዓላት ያቀረቡት የተስፋ ጥሪ መሆኑን፥ በቅድስት መንበር የምእመናንና የቤተሰብ ሕይወት መምሪያ ጳጳሳዊ ጽሕፈት ቤት በመግለጫው አስታውቋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

እንደ ጎርጎሮሳውያኑ በ2025 ዓ. ም. የሚከበረውን የወጣቶች ኢዮቤልዩ በዓል ለማክበር ዝግጅት እየተደረገ ባላበት በዚህ ወቅት፥ “የተስፋ ነጋዲያን” የሚለው መሪ ሃሳብ፥ በሀገረ ስብከት ደረጃ እንደ ጎርጎሮሳውያኑ በ 2023 እና በ 2024 ዓ. ም. ለሚከበሩ የዓለም ወጣቶች በዓላትም ተስፋ እንደሚሆናቸው ታውቋል።

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ለሁለቱም በዓላት ዝግጅቶች የሚሆኑ መሪ ጥቅሶችን መምረጣቸውን የቫቲካን ጋዜጣዊ መግለጫ ክፍል ዛሬ ማክሰኞ መስከረም 15/2016 ዓ. ም. ጠዋት ላይ በሰጠው መግለጫ አስታውቋል። 38ኛው የዓለም ወጣቶች ቀን መሪ ጥቅስ ከወደ ሮሜ ሰዎች ምዕ. 12:12 ላይ የተወሰደ እና “በተስፋ ደስ ይበላችሁ” የሚል ሲሆን፥ የቀጣዩ የወጣቶች ቀን መሪ ጥቅስም ከትንቢተ ኢሳ. 40:31 የተወሰደ እና “ጌታን በመተማመን የሚጠባበቁ ግን ኃይላቸውን ያድሳሉ፤ እንደ ንስር በክንፍ ይወጣሉ፤ ይሮጣሉ፤ አይታክቱም፤ ይሄዳሉ፤ አይደክሙም” የሚል እንደሆነ ታውቋል።

በዓለም ዙሪያ ተስፋን በድጋሚ ማቀጣጠል

እንደ ጎርጎሮሳውያኑ በ2023 እና በ 2024 ዓ. ም. የሚከበሩ የዓለም ወጣቶች ቀናት በኢየሱስ ክርስቶስ ንጉሥ ክብረ በዓል ዕለት ማለትም እሑድ ኅዳር 26 እና እሑድ ኅዳር 24 ቀን በቅደም ተከተል የሚውሉ እና በልዩ ቤተ ክርስቲያናት ዘንድ እንደሚከበሩ ታውቋል። እንደ ጎርጎሮሳውያን በ1965 ዓ. ም. ይፋ የሆነው እና “ደስታ እና ተስፋ” በሚለው ሐዋርያዊ ቃለ ምዕዳን፥ “በአሁኑ ጊዜ የሰዎች ደስታና ተስፋ፣ ሐዘንና ጭንቀት፣ ከሁሉም በላይ የድሆችና የሚሠቃዩ ሰዎች ደስታና ተስፋ፣ ሐዘንና ጭንቀት” እንደሆነ ይገልጻል። ሐዋርያዊ ቃለ ምዕዳኑ በመቀጠልም፥ የክርስቶስ ደቀ መዛሙርት ጭንቀት፥ በዛሬው አስቸጋሪ ጊዜያት ቤተ ክርስቲያን በዓለም ላይ ተስፋዋን ለማደስ እንደምትፈልግ እና ይህንን እውን ለማድረግ በተለይ የታሪክ ዋና ተዋናዮች በሆኑ ወጣቶች የደስታ ልኡካን ላይ የምትመካ መሆኑን ይገልጻል።

ክርስቶስ ሕያው መሆኑን መመስከር

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ፥ “ክርስቶስ ሕያው ነው” በሚለው የድህረ ሲኖዶስ ሐዋርያዊ ማሳሰቢያቸው ላይ፥ “ተስፋችን እና የዚህ ዓለም ብርቱ ወጣቶች” ማለታቸውን በቅድስት መንበር የምእመናንና የቤተሰብ ሕይወት መምሪያ ጳጳሳዊ ጽሕፈት ቤት ገልጾ፥ በሁለቱም ቀጣይ የዓለም ወጣቶች ቀን መሪ ሃሳቦችን  ወጣቶች በጥልቀት እንዲመለከቷቸው፥ የክርስቲያናዊ ተስፋን ትርጉም ጠንቅቀው በማወቅ እና ክርስቶስ ሕያው እንደሆነ በደስታ መመስከር እንደሚገባ ቅዱስነታቸው መጋበዛቸውን አስታውቋል።

 

 

26 September 2023, 16:57