ፈልግ

ር. ሊ. ጳ. ፍራንችስኮስ፥ የጥቃት ሰለባ ሕጻናት መርጃ የማኅበር ተወካዮች በቫቲካን ሲቀበሏቸው ር. ሊ. ጳ. ፍራንችስኮስ፥ የጥቃት ሰለባ ሕጻናት መርጃ የማኅበር ተወካዮች በቫቲካን ሲቀበሏቸው  (Tutela Minorum)

ር. ሊ. ጳ. ፍራንችስኮስ፥ ከወሲባዊ ጥቃት ሰለባ ሕጻናት መርጃ ማኅበር ተወካዮች ጋር መገናኘታቸው ተገለጸ

ለአካለ መጠን ያልደረሱ ሕፃናት ጥበቃ ጳጳሳዊ ምክር ቤት የመጀመሪያውን ዓመታዊ ሪፖርት እያዘጋጀ ባለበት በዚህ ወቅት፥ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ምልአተ ጉባኤውን የተሳተፉ ሁለት የወሲባዊ ጥቃት ሰለባ ሕጻናት መርጃ ማኅበር ተወካዮችን በቫቲካን ተቀብለው ማነጋገራቸው ተገልጿል። ር. ሊ. ጳ. ፍራንችስኮስ፥ ከመስከረም 9-11/2016 ዓ. ም. ድረስ የተካሄደውን የምክር ቤቱን ስብሰባ የተካፈሉ ሁለት ሴት ተወካዮችን በቫቲካን ተቀብለው ባደረጉት ንግግር፥ “ማኅበራቸው የተስፋ ምልክት ነው” ሲሉ ገልጸውታል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

በሮም ከመስከረም 9-11/2016 ዓ. ም. ድረስ የተካሄደው የጳጳሳዊ ምክር ቤት ስብሰባ መንደርደሪያ ሃሳብ፥ ግልጽነት እና ሃላፊነት የሚሉ እንደነበር ታውቋል። ስብሰባውን ምስክርነትን በመስጠት የከፈቱት፥ የወሲባዊ ጥቃት ሰለባ ሕጻናት መርጃ ማኅበር ተወካይ የሆኑት አንቶኒያ ሶቦኪ እና ማጊ ማቴዎስ እንደነበሩ ታውቋል። ሁለቱ የማኅበሩ ተወካይ ሴቶች ቀጥለውም ሐሙስ መስከረም 10/2016 ዓ. ም. በቫቲካን ውስጥ በሚገኘው ቅድስት ማርታ የብጹዓን ጳጳሳት መኖሪያ ቤት ውስጥ ከርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ጋር መገናኘታቸው ታውቋል።

ምልአተ ጉባኤው በመጀመሪያ ቀኑ፥ በቤተ ክርስቲያን ውስጥ ተግባራዊ የሚሆኑ ፖሊሲዎችን እና የተግባር ሂደቶችን እውን በሚያደርግበት መንገድ ላይ ውይይት አድርጓል። ጳጳሳዊ ምክር ቤቱ የመጀመሪያ የተባለውን ይህን ስብሰባ ሲያጠቃልል እንደ ጎርጎሮሳውያኑ በ 2024 ዓ. ም. ጸደይ ወራት ውስጥ በድረ-ገጹ ይፋ የሚያደርገውን ዓመታዊ ሪፖርት ረቂቅ ማጽደቁ ታውቋል። በዚህ ሂደት ውስጥ ምክር ቤቱ የትብብር ስምምነቶችን የመረመረው፥ ከቅድስት መንበር ከፍተኛ ጳጳሳዊ ጽሕፈት ቤቶች እና ከምሥራቅ ካቶሊክ አብያተ ክርስቲያናት ጠቅላይ ጽሕፈት ቤት ከመጡ የበላይ ሃላፊዎች ጋር እንደነበር ታውቋል።

ለአካለ መጠን ያልደረሱ ሕፃናት ጥበቃ ጳጳሳዊ ምክር ቤት

ጳጳስዊ ምክር ቤቱ በዓለም ውስጥ በሚገኙ ካቶሊካዊ ቁምስናዎች ዘንድ የሚደረገውን ክትትል የሚቆጣጠር የአቅም ግንባታ መርሃ ግብርን ለማስፋት የወጣውን እቅድ ገምግሟል። ይህን መርሃ ግብር መደገፍ የሚፈልጉ ለጋሾች 2.5 ሚሊዮን ዶላር የገንዘብ ድጎማ ለማቅረብ ቃል ገብተዋል። የገንዘብ ዕርዳታው ጥቅም ላይ መዋሉን የሚቆጣጠር 'ሜሞራሬ' የተባለ የፋይናንስ ተጠያቂነት ዘዴ መርሃ ግብር በምክር ቤቱ ድረ-ገጽ ላይ ታትሞ ይገኛል።

ጉባኤው ለአፍሪካ አኅጉር ልዩ ትኩረት በመስጠት በየአካባቢያቸው እየታየ ያለውን ለውጥ በተመለከተ ከክልል ቡድኖች የቀረቡ ሪፖርቶችን አድምጧል። በአገራት ውስጥ የሚገኙ 20 ቤተ ክርስቲያናት፣ የብጹዓን ጳጳሳት ጉባኤዎች እና ገዳማት እራሳቸውን በመርሃ ግብሩ ውስጥ ለማካተት ፍላጎት እንዳላቸው ገልጸዋል። በስብሰባው ወቅት የምክር ቤተ ፕሬዝዳንት ብጹዕ ካርዲናል ሾን ፓትሪክ ኦማሌይ፥ በግንቦት ወር 2015 ዓ. ም. ከሩዋንዳ ቤተ ክርስቲያን ጋር ከተፈራረሙት የመግባቢያ ሰነድ በተጨማሪ ሁለተኛውን የመግባቢያ ሠነድ ከመካከለኛው አፍሪካ ሪፐብሊክ ቤተ ክርስቲያን ጋርም ተፈራርመዋል።

በመጨረሻም ሁለተኛውን ዙር የሕፃናት ጥበቃ እና መከላከያ መርሃ ግብርን ተግባራዊ ለማድረግ፥ በዓለም ዙሪያ ካሉ አብያተ ክርስቲያናት የተሰጡ ምላሾችን ለመገምገም የሚያግዝ ጥናት እስከ ግርጎሮሳውያኑ 2024 ዓ. ም. ድረስ እንዲራዘም ተወስኗል። በአንደኛው ዓመት ምክር ቤቱ በመላው ዓለም ከሚገኙ ቤተ ክርስቲያናት ያገኛቸውን አጠቃላይ መመሪያዎችን መሠረት በማድረግ የምክክር ሂደት እንደሚጀምር ብጹዕ ካርዲናል ኦሜሌይ አስታውቀዋል።

የምክር ቤቱ ፕሬዝደንት ብጹዕ ካርዲናል ኦሜሌይ በማከልም፥ ከዓለም ዙሪያ የተውጣጡ የሕጻናት ጥበቃ ባለሙያዎች ላሳዩት ቁርጠኝነት፣ ቤተ ክርስቲያናቸው ሁሉንም ሕዝቦች እና አገራት ያካተተች ትልቅ አካል በመሆኗ ያከናውኑት ተግባር ከባድ ቢሆንም በመልካም ውጤት ለመፈጸም ላሳዩት ቁርጠኝነት ምስጋናቸውን ካቀረቡላቸው በኋላ፥ መላዋን ቤተ ክርስቲያን በተለያዩ የዕድገት ደረጃዎች የሚያካትት ዕቅድ በተግበር መታየት መጀመሩን አስረድተዋል።

26 September 2023, 16:49