ፈልግ

በመካከለኛ ምስራቅ በፍልስጤም እና በእስራኤል መካከል እየተካሄደ ያለው ጦርነት በመካከለኛ ምስራቅ በፍልስጤም እና በእስራኤል መካከል እየተካሄደ ያለው ጦርነት  (ANSA) ርዕሰ አንቀጽ

“ጦርነትን በመቃወም ከጦርነት ተጎጂዎች ጋር መቆም ይገባል!”

የቅድስት መንበር መገናኛዎች ርዕሠ አንቀጽ ዝግጅት ክፍል ሃላፊ የሆኑት አቶ አንድሬያ ቶርኔሊ፥ በዓለማችን ውስጥ ከበርካታ ዓመታት ወዲህ ሲካሄዱ በቆዩ ጦርነቶች ላይ ቅድስት መንበር ያላትን አቋም በማስመልከት፥ ጦርነትን በመቃወም ከጦርነት ተጎጂዎች ጋር መቆም ይገባል በማለት የሚከተለውን ርዕሠ አንቀጽ አዘጋጅተዋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

ከአንድ መቶ ለሚበልጡ ዓመታት ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ጦርነትን እንደማይቀበሉ ሲገልጹ ቆይተዋል። ግጭቶች በሚቀሰቀሱበት ጊዜ ሁሉ ቅድስት መንበር ገለልተኛ ሆና አታውቅም። ሁልጊዜም የግጭቱ ሰለባ ለሆኑት፣ በሁለቱም ወገኖች ለሚሰቃዩ እና በግጭቱ መካከል ዋጋን ለሚከፍሉ ሰዎች ቅርብ ለመሆን ትጥራለች።

ቅድስት መንበር ከመቶ ዓመታት በላይ የጦርነት ስጋቶች መባባስ እና የተራቀቁ እና አውዳሚ የጦር መሳሪያዎች ጥቅም ላይ በመዋላቸው ምክንያት፥ ጦርነትን በጽኑ መቃወሟን ስታሳውቅ ቆይታለች። የቀድሞው ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ቤነዲክቶስ 15ኛ፥ ታላቁ ጦርነት የማይጠቅም እና እልቂትን የሚያስከትል ነው በማለት ትንቢታዊ ተማጽኖ ካቀረቡበት ጊዜ ጀምሮ፥ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ባገኙት አጋጣሚ ሁሉ ጦርነት የሰው ልጅ ሽንፈትን የሚያሳይ ነው በማለት  ለሮም ብጹዓን ጳጳሳት በግልጽ ተናግረው፥ የካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን ትምህርተ ክርስቶስ “ፍትሃዊ ጦርነቶች” የሚለው እና እራስን የመከላከል መብትም ቢሆን ተመጣጣኝ መሆን አለበት የሚለውን አስተምህሮ በጥልቀት በመመልከት “ፍትሃዊ ጦርነት” የሚባል ጦርነት ሊኖር እንደማይገባ አሳስበዋል።

ሩሲያ በዩክሬን ላይ ወረራ ካካሄደችበት ጦርነት ጀምሮ እና እንዲሁም ከቅርብ ሳምንታት በፊት የሐማስ ታጣቂዎች በእስራኤል ሲቪሎች ላይ በፈጸሙት ጭካኔ የተሞላበት ጥቃት ተከትሎ የእስራኤል ጦር በመልሶ ማጥቃት ጋዛ ውስጥ የሚገኙ በርካታ ቤቶችን በማፍረስ እንዲሁም በሺዎች የሚቆጠሩ ንጹሃን ፍልስጤማውያንን ሲገድል ከርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ እና ከቅድስት መንበር በኩል ትችት ቀርቧል። አንዳንድ ገለልተኛ ወገኖች ለረጅም ጊዜ ሲያቀርቡት በቆየው የተሳሳተ አስተሳሰብ፥ “ቫቲካን ከዲፕሎማሲዋ መብዛት የተነሳ ወደ ጦርነት ከገቡት ወገኖች መካከል ጥፋተኛውን መለየት አልቻለችም” ሲሉ ይደመጣሉ።

ስለዚህ ቅድስት መንበር በማንኛውም የጦርነት ወቅት ገለልተኛ ሆና እንደማታውቅ በድጋሚ ማስታወሱ ተገቢ ነው። ይልቁንም ሁልጊዜ ገለልተኛ መሆን ማለት በግጭቱ ውስጥ ላለመሳተፍ እና እንደዚሁም ለሁለቱም ወገኖች እኩል ቅርብ ሆኖ መገኘት ማለት ሳይሆን በጦርነቱ ምክንያት ስቃይ ለሚደርስባቸው፥ በጦርነቱ ምክንያት ከፍተኛ መስዋዕትነት ለሚከፍሉ፣ ሕይወታቸውን በከንቱ ለሚያጡ ንጹሃን እና ሰላማዊ ዜጎች፣ ለሚቆስሉት፣ በጦር ሜዳ የወደቁ ወታደሮች እናቶች እና አባቶች፣ የሽብር ሰለባ ለሆኑ ንፁሃን ሰዎች ያላትን ቅርበት የምትገልጽበት መንገድ ነው።

የቫቲካን መገናኛ ይህን ርዕሠ አንቀጽ መስመር ከመከተል በቀር፣ አሁን እየተካሂዱ ያሉ ጦርነቶችን ብቻ ሳይሆን ባጠቃላይ በአሁኑ ጊዜ በምንኖርበት ዓለም ውስጥ የሚታየውን የመከፋፈል ባህሪን ውድቅ አድርገውታል። የተኩስ አቁም ስምምነት ላይ ለመድረስ እና ፍትሃዊ ሰላም እንዲመጣ ለመደራደር ተስፋ በማድረግ ከሁሉም ጋር የውይይት መስመሮችን ክፍት በማድረግ፣ ያሉ ዕድሎችን አለመዝጋት፣ ለንጹሃን ተጎጂዎች መጨነቅ፣ ለግጭቱ ወይም ለጦርነቱ ዋና መንስኤ በሆኑት ምክንያቶች ላይ ማሰላሰል፣ ጥላቻን ይበልጥ የሚያባብሱ ቃላትን ከመጠቀም መቆጠብ ማለት ተበዳይን እና በዳይ መኖሩን መናቅ ማለት አይደለም። ወይም ራስን የመከላከል ሕጋዊነትን ችላ ማለት አይደለም። በተቃራኒው የንጹሃንን እጣ ፈንታ መንከባከብ፣ የሰላሙን የተስፋ ብርሃን በምንም መልኩ እንዳይጠፋ በመጠበቅ፣ ሰላምን ሊያስገኝ የሚችል ማንኛውንም ጠቃሚ ሃስብ ከየትኛውም ቦታ በመውሰድ በዲፕሎማሲ ማመን እና ከምንም በላይ ለተጎጂዎች ማለትም ለአካል ጉዳተኞች እና ለተፈናቃዮች ዕጣ ፈንታ መጨነቅ ማለት ነው። በተጨማሪም ከመከፋፈል አመክንዮ እና ከአንድ ወገን አስተሳሰብ መውጣት ማለት ነው።

የሐማስ ታጣቂዎች በእስራኤል ሲቪሎች ላይ ያደረሱትን ኢ-ሰብአዊ የሽብር ጥቃት ማውገዝ እና እንዲሁም የእስራኤል ጦር በምላሹ ጋዛ ውስጥ በብዙ ሺህዎች ላይ ባደረሰውን የሞት አደጋ ላይ ጥያቄዎችን ማቅረብ ይቻላልን?

ጩኸት እጅግ በጣም ተገቢ ያልሆነባቸው ግጭቶች አሉ። አሁን በመካከለኛው ምሥራቅ እየተካሄደ ባለው ግጭት መካከል ከፍተኛ ጩኸት መኖሩ ግልጽ ነው። ይህም በጣም ውስብስብ በሆነ ሁኔታ ውስጥ ሁለቱም ወገኖች ሃላፊነትን ለመውሰድ እና የትኛው ወገን ትክክል እንደሆነ ለመናገር እርግጠኛ ያልሆኑበት ነው።

እየተካሄዱ ያሉ ጦርነቶችን በመዘገብ እና በማሰላሰል ነጥቦችን ለማቅረብ ስንፈልግ፥ መሪ ብርሃናችን የወቅቱ የቅዱስ ጴጥሮስ ተተኪ የሆኑት ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በትንቢታዊ ንግግራቸው፥ የሰው ልጅ በሙሉ ዓለም አቀፍ ጦርነት እንዳይከሰት እና ራስን በራስ የማጥፋት አደጋ እንዳይከተል ማስጠንቀቃቸውን ቀጥለዋል። እውነታዎችን ከአስተያየቶች እና ከሌሎች ሰዎች አመለካከት በመለየት በትክክለኛ የጋዜጠኝነት ተግባር ለመሳተፍ እየሞከርን እንገኛለን።

የቅርብ ጊዜ ሪፖርቶችን ማቀርብ ወይም ለዜናችን ተስማሚ የሚመስሉ ግለሰቦችን መስማት ማለት አስተያየታቸውን መጋራት ማለት አይደለም። ይልቁንም ይበልጥ ፍትሃዊ እና በጥቂቱ ርዕዮተ ዓለማዊ ድምፆችን በማጉላት ለመረዳት መሞከር ማለት ነው።

 

21 November 2023, 16:48