ፈልግ

2023.10.30 il vescovo Aliaksandr Jasheuski Bielorussia incontra Papa Francesco durante il Sinodo 2023

16ኛ የካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን መደበኛ ጠቅላላ ሲኖዶስ የሪፖርት ጥንቅር

“ለሲኖዶስዊ ቤተ ክርስቲያን፡ ሕብረት፣ ተሳትፎና ተልእኮ” በሚል መሪ ቃል ከመስከረም 23 እስከ ጥቅምት 18/2016 ዓ.ም በቫቲካን በሚገኘው በጳውሎስ 6ኛ የመሰብሰቢያ አዳራሽ ውስጥ ሲካሄድ የነበረው 16ኛ የካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን መደበኛ ጠቅላላ ሲኖዶስ በጥቅምት 18/2016 ዓ. ም. በቫቲካን በሚገኘው በቅዱስ ጴጥሮስ ባዚሊካ በርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ መሪነት እና በሲኖዶሱ ተሳታፊ ጳጳሳት እና ካህናት በተመራ መስዋዕተ ቅዳሴ መጠናቀቁ ይታወሳል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ መብራቱ ኃ/ጊዮርጊስ ቫቲካን

“እግዚአብሔር በሦስተኛው ሚሌንዬም ውስጥ ከምትገኘው ቤተ ክርስቲያን የሚጠብቀው ይህንን የሲኖዶሳዊ መንገድ ነው” ሲሉ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ እ.አ.አ በጥቅምት 07/2015 ዓ. ም. የብፁዓን ጳጳሳት ሲኖዶስ ተቋም 50ኛ ዓመት የምሥረታ በዓል ላይ ባደረጉት ንግግር ይፋ ማድረጋቸው ይታወሳል። በእርግጥም ሲኖዶሳዊነት “የቤተ ክርስቲያን አስፈላጊ ገጽታ ነው” በማለት አጽንኦት ሰጥተው የተናገሩት  ቅዱስነታቸው፥ “ጌታ እኛን የሚጠይቀን ነገር በተወሰነ መልኩ ‘ሲኖዶስ’ በሚለው ቃል ውስጥ ይገኛል” በማለት አክለው ተናግረው ነበር።

“ሲኖዶስ” የሚለው ቃል በቤተ ክርስቲያን ትውፊት ውስጥ ጥንታዊ እና የተከበረ ቃል ነው፤ ትርጉሙም የራዕይ ጥልቅ ጭብጦችን ይገልጻል፤ ይህም የእግዚአብሔር ሕዝቦች አብረው የሚሄዱበትን መንገድ ያመለክታል። በተመሳሳይ መልኩ ራሱን እንደ “መንገድ፣ እውነትና ሕይወት” አድርጎ የሚያቀርበውን ጌታ ኢየሱስን ያንጸባርቃል (ሐዋ 9:2፣19፤ 9:23፣22፣ 4፣ 24፣ 14:22)።

የሁለተኛው የቫቲካን ጉባኤ ከቤተ ክርስቲያን አስተምህሮ ጋር በተጣጣመ መልኩ የሲኖዶሳዊነት ሥነ-መለኮታዊ መሠረቶችን ይገልጻል። ይህም ከምዕመናን እና ከሚስዮናውያን የእግዚአብሔር ሕዝቦች ዕይታ እና ከቤተ ክርስቲያን ምሥጢራት ጋር በማያያዝ፣ ከቤተ ክርስቲያን ልዩ ባህሪያት ጋር በማገናኘት አንድነት፣ ቅድስና፣ ካቶሊካዊነት እና ሐዋርያዊነት ምን እንደ ሆኑ ያስረዳል። በመጨረሻም ሁሉም የእግዚአብሔር ሕዝቦች በቤተ ክርስቲያኗ ተልዕኮ ውስጥ በሚያደርጉት ተሳትፎ እና በእረኞቻቸው የስልጣን አጠቃቀም መካከል ያለውን ግንኙነት ይመለክታል።

የቤተ ክርስቲያን ሲኖዶሳዊ ሕይወት በቅዱሳት መጻሕፍት እና በትውፊት ውስጥ የሚገኙት መደበኛ ምንጮች እንደሚያሳዩት ከሆነ፥ በእግዚአብሔር የማዳን ዕቅድ ልብ ውስጥ የሰው ዘር በሙሉ ከእግዚአብሔር ጋር አንድነት እንዲኖው እና በእነርሱም በኩል አንድነት እንዲፈጠር በኢየሱስ ክርስቶስ እና በአገልግሎቱ የተገኘውን የቤተ ክርስቲያን ጥሪን የሚያመልክት ነው። የሲኖዶሳዊ ሕይወት፣ አወቃቀሮች፣ ሂደቶቹ እና የሚያካትታቸው ክስተቶችን የሚያንቀሳቅሱትን እና የሚቆጣጠሩትን የሥነ-መለኮት መርሆችን ለመለየት የሚያስፈልገንን መመሪያ ይሰጣሉ።

የሁለተኛው የቫቲካን ጉባኤ፥ “በዛሬ ዘመን የሚኖሩ ሰዎች ደስታና ተስፋ፣ ሐዘን እና መከራ ከሁሉም በላይ ደግሞ ድሆች እና መከራ የሚደርስባቸው ሰዎች ሁሉ፣ ደስታቸው እና ተስፋቸው፣ ሐዘናቸው እና መከራቸው ሁሉ የክርስቶስ ደቀ መዛሙርት የሚጋሩት እና በማንኛውም እውነተኛ በሆነ ሰው ልብ ውስጥ የሚያስተጋቡ ነገሮች ናቸው” በላቲን ቋንቋ (Gaudium et Spece no. 1፣ ደስታ እና ተስፋ) በማለት ቤተ ክርስቲያን የሕዝበ እግዚአብሔር ደስታ ደስታዋ፣ ሐዘናቸው ደግሞ ሐዘኗ እንደ ሆነ አድርጋ በመውሰድ በየጊዜው የዘመኑን ምልክቶች በማየት ሲኖዶሳዊ ጉባኤ በመጥራት የሕዝበ እግዚአብሔርን ችግሮች እና ተግዳሮቶች ለመፍታት፥ ደስታቸውን እና ተስፋዎቻቸውን ለማለምለም፣ እንደ አስፈላጊነቱ በርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሲወሰን የካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን ሲኖዶስ እንደ ምትጠራ ይታወቃል።

እ. አ. አ ከ1962-1965 ዓ. ም. የተካሄደው ሁለተኛው የቫቲካን ጉባኤ ከተጠናቀቀ በኋላ በአጠቃላይ 16 ሠነዶችን ይፋ በማድረግ በሂደት እንደ አስፈላጊነቱ በሚቀጥሉት መቶ ዓመታት ውስጥ የሚተገበር እና እነዚህም ሠነዶች እንደ አስፈላጊነቱ የጊዜውን ምልክት በመመልከት በመጽሐፍ ቅዱስ፣ በቤተ ክርስቲያን ትውፊት እና አስተምህሮ፣ እንዲሁም የነገረ-መለኮት አስተምህሮዎችን ከግንዛቤ ባስገባ መልኩ በመተርጎም ለሕዝበ እግዚአብሔር አገልግሎት እንዲውል በየጊዜው ማሻሻያዎች ማድረግ የሚቻልባቸውን አቅጣጫ አስቀምጧል። እነዚህ ማሻሻያዎች የሚደረጉት ደግሞ የቅዱስ ሲኖዶስ ጉባኤ በሚጠራበት ወቅት ብቻ ነው። በእዚህም መሠረት የሁለተኛው የቫቲካን ጉባኤ ከተካሄደ 58 ዓመታት አልፎታል። በእነዚህ 58 ዓመታት ውስጥ 16 የሲኖዶስ ጉባኤዎች የተከናወኑ ሲሆን የቅዱስ ሲኖዶስ ጉባኤ የሚከናወነው ደግሞ የካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት አስፈላጊነቱን ተመልክተው፣ አስፈላጊውን መስፈርት አሟልተው ጉባኤው እንዲከናወን ጥሪ ስያቀርቡ ብቻ ነው።

የሁለተኛው የቫቲካን ጉባኤ ከተካሄደ ከ58 ዓመት ገደማ በኋላ ባሉት ዓመታት ውስጥ 16 የሲኖዶስ ጉባኤዎች ተከናውነዋል። በእዚህ መሠረት ከላይ እንደተጠቀሰው “ለሲኖዶስዊ ቤተ ክርስቲያን ሕብረት፣ ተሳትፎና ተልእኮ” በሚል መሪ ቃል ከመስከረም 23 እስከ ጥቅምት 18/2016 ዓ. ም. ድረስ በሲኖዶሳዊነት ላይ ሲካሄድ የነበረው 16ኛ የካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን መደበኛ ጠቅላላ የሲኖዶስ ጉባኤ ማብቂያ ላይ ይፋ የሆነው የሪፖርቱ ጥንቅር  በጥቅምት 17/2016 ዓ. ም. ድምጽ ከተሰጠበት በኋላ 40 ገጽ ያሉት የሪፖርቱ ጥንቅር  ይፋ ተደርጓል። እ. ኤ. አ. በ 2024 ዓ. ም. በሲኖዶሳዊነት ላይ የሚከናወነውን ሲኖዶስ ሁለተኛውን ክፍለ ጊዜ በማመላከት አጠቃላይ ሪፖርቱ የሴቶች እና የምእመናን ሚና ፣ የጳጳሳት፣ የካህናት እና የዲያቆናት አገልግሎት፣ የድሆች እና የስደተኞች አስፈላጊነት፣ ዲጂታል ተልዕኮ፣ ክርስቲያናዊ ሕብረት እና ያለ አግባብ የሚፈጸሙ ጥቃቶችን በተመለከተ ቅዱስ ሲኖዶሱ የተወያየባቸውን ፍሬ ሐሳቦች ያካተተ የሪፖርቱ ጥንቅር ይፋ ሆኗል።

ሴቶች እና ምእመናን ፣ ዲያቆናት ፣ አገልግሎት እና የቤተ ክርስቲያን አስተምህሮ፣ ሰላም እና የአየር ንብረት ለውጥ ፣ ድሆች እና ስደተኞች ፣ ክርስቲያናዊ ማኅበራት እና ማንነት ፣ አዲስ ቋንቋዎች እና የታደሱ መዋቅሮች ፣ አሮጌ እና አዲስ ተልእኮዎች (“ዲጂታል” ተልዕኮን ጨምሮ) ሁሉንም ማዳመጥ እና ሁሉንም ነገር መመርመር ይገባል በሚል መሪ ሐሳብ በጥልቀት፣ እንዲሁም በጣም 'አከራካሪ' በሆኑ ጉዳዮች ላይ የተወያየ እና በሲኖዶሳዊነት ላይ የተካሄደ ጉባኤ ነበር። በሲኖዶሳዊነት ላይ የተካሄደው 16ኛ ጠቅላላ ጉባኤ በጥቅምት 17/2016 ዓ. ም. ሲጠናቀቅ ባፀደቀው እና ባሳተመው የሪፖርቱ ጥንቅር፥ ዓለምን እና ቤተ ክርስቲያንን፣ ጥያቄዎቻቸውን በአዲስ መልክ ተመልክቷል። በቫቲካን በሚገኘው በጳውሎስ ስድስተኛ አዳራሽ ውስጥ ከመስከረም 23/2016 ዓ. ም. ጀምሮ  ለአራት ሳምንታት ያህል ከቆየ የሥራ ጊዜ በኋላ አጠቃላይ ጉባኤው የመጀመሪያውን ስብሰባ አጠናቋል። ይህ በ35 ክብ ጠረጴዛ ዙሪያ በሲኖዶሳዊነት ላይ ሲካሄድ የቆየው ጉባኤ ሲጠናቀቅ አርባ ገጾች ያሉት የሪፖርቱ ጥንቅር “ከእዚህ ቀደም የነበሩ ሆነ አዲስ ጦርነቶች በዓለም ላይ ሲቀሰቀሱ፣ ሥፍር ቁጥር በሌላቸው ተጎጂዎች ላይ ከፍተኛ ተጽዕኖ እያሳደረ በነበረበት ጊዜ” የተካሄደ ጉባኤ የሥራ ውጤት ነው። ሪፖርቱ በመቀጠል “የድሆች ጩኸት በመካከላችን እያስተጋባ ይገኛል፤ ለስደት የተገደዱ፣ በዓመፅ የሚሰቃዩ እና የአየር ንብረት ለውጥ ባስከተለው አስከፊ መዘዝ የተነሳ የሚሰቃዩ ብዙ ሕዝቦች አሉ። ጩኸታቸውን የሰማነው በመገናኛ ብዙኃን ብቻ ሳይሆን በቤተሰቦቻቸውም ሆነ በወገኖቻቸው አማካይነት በአሳዛኝ ክስተቶች ውስጥ በተሳተፉት የብዙ ሰዎች ድምጽ ጭምር ነው” በማለት  የሪፖርቱ ጥንቅር አሁን በዓለማችን ላይ በየቦታው ስላሉት ጦርነቶች አሳሳቢነት ይገልጻል።

ለዚህ ፈተና እና ለሌሎች ብዙ ዓለም አቀፋዊው ችግሮች እና ተግዳሮቶች በሲኖዶሱ ላይ የተሳተፉ ሰዎች በጠሬጴዛ ዙሪያ ባቀረቧቸው የተለያዩ አስተያየቶች ዙሪያ ቤተ ክርስቲያን ሐሳብ ለመስጠት ሞክራለች። ሁሉም የውይይት አርእስቶች በሪፖርቱ ጥንቅር ውስጥ ተካተዋል። በመቅድም (የመግቢያ ገጽ) እና በሦስት ክፍሎች የተከፈለ ሲሆን፥ ሁለተኛው ዙር እ. አ. አ በ 2024 ዓ. ም. የሚከናወንበትን መንገድ ይከታተላል።

ከተጎጂዎች ጀምሮ ሁሉንም ማዳመጥ

ለሕዝበ እግዚአብሔር በተጻፈው መልእክት ላይ የሲኖዶሱ ጉባኤው “በቤተ ክርስቲያን ውስጥ በደል የደረሰባቸውን እና የተጎዱትን ጨምሮ ሁሉንም ለመስማት እና ለማጀብ ክፍት” መሆኑን ያረጋግጣል። ይህም “እንዲህ ያለውም በደል ያስከተለውን መዋቅራዊ ሁኔታ የሚፈታው ጉዳዩ በፊታችን እንዳለ ተገንዝበን ተጨባጭ የንስሐ ምልክቶችን ይጠይቃል። እነዚህ እስካሁን እየተደረጉ የሚገኙ ጥረቶች ተጠናክረው መቀጠል ይኖርባቸውል ሲል የሪፖርቱ ጥንቅር በጹሑፍ አስፍሯል።

የሲኖዶስ ቤተ ክርስቲያን ፊት

 

ሲኖዶሳዊነት የመጀመሪያ እርምጃ ነው። የሲኖዶሱ ተሳታፊዎች ራሳቸው እንደሚያምኑት፥ “ለብዙ የእግዚአብሔር ሕዝብ አባላት ያልተለመደ ቃል ነው። ለአንዳንድ ሰዎችን ግራ መጋባትን እና ጭንቀትን ሲፈጥር ቆይቷል።” ከባሕል የመውጣት ፍርሃትን ጨምሮ፣ የቤተ ክርስቲያን የስልጣን ተዋረድ መዋቅርን ዝቅ የሚያደርግ ነው። የቤተ ክርስቲያኗን ተዋረዳዊ ተፈጥሮ (1 g) ፣ በቤተ ክርስቲያን ውስጥ ያለውን ሥልጣን ማጣት ወይም በተቃራኒው የማይንቀሳቀስ እና ለውጥ ለማምጣት ድፍረት ማጣት በሲኖዶሱ ውስጥ የታዩት እውነታዎች ናቸው። “ሲኖዶሳዊ” እና “ሲኖዶሳዊነት” በምትኩ “ኅብረት፣ ተልእኮ እና ተሳትፎን የሚያዋህድ ቤተ ክርስቲያን የመሆን ዘዴን የሚናገሩ” ቃላት ናቸው። ስለዚህ ልዩነቶችን ከግምት ውስጥ በማስገባት የሁሉንም ንቁ ተሳትፎ በማዳበር የቤተ ክርስቲያንን የኑሮ መንገድ ያመለክታል። ይህ የሚጀመረው ከዲያቆናት፣ ከካህናት እና ከጳጳሳት ነው። “የሲኖዶሳዊ ቤተ ክርስቲያን ያለ ድምፃቸው ምንም ማድረግ አትችልም” (1 n)። "አንዳንዶቹ ሲኖዶሳዊነትን የሚቃወሙበትን ምክንያቶች መረዳት ያስፈልገናል" የሚል አድምታ በሲኖዶሱ ወቅት ታይቷል።

ተልዕኮ

የሪፖርቱ ጥንቅር ሲኖዶሳዊነት ከተልዕኮ ጋር አብሮ እንደሚሄድ ያስረዳል። ስለዚህ “የክርስቲያን ማኅበረሰቦች ከሌሎች ሃይማኖቶች፣ እምነቶች እና ባህሎች ጋር ተባብረው በአንድ በኩል ራስን የመግለጽ እና ራስን የመጠበቅ አደጋን በማስወገድ በሌላ በኩል ደግሞ ማንነትን የማጣት አደጋን ማስወገድ አለባቸው” (2 ሠ)። በዚህ አዲስ “የሐዋርያዊ እንክብካቤ ዘይቤ”፣ “የሥርዓተ አምልኮ ቋንቋ ለምእመናን ይበልጥ ተደራሽ እና በባህል ብዝሃነት ውስጥ እንዲካተት” (3 L) ማድረግ ለብዙዎች አስፈላጊ ይመስላል።

የድሆች ማዕከላዊነት

በሪፖርቱ ውስጥ ለድሆች ሰፊ ቦታ ተሰጥቷል። የቤተ ክርስቲያኗን “ፍቅር” ለሚጠይቁ  እንደ “መከባበር፣ መቀበል እና እውቅና” (4 a) መስጠት የመሳሰሉ ሐሳቦች ተካተውበታል። "ለቤተ ክርስቲያኗ የድሆች እና በማኅበረሰቡ በመገለል ወጣ ላሉ ሰዎች ያለው አማራጭ የባህል፣ የማኅበራዊ ሳይንስ፣ የፖለቲካ ወይም የፍልስፍና ፈርጅ ከመሆኑ በፊት ሥነ-መለኮታዊ ፈርጅ ወይም ምድብ ያለው ነው" (4 b)፣ የሪፖርቱ ጥንቅር ድሆችን የሚገልጸው በቁሳዊ ነገሮች እና ችግሮቻቸው ብቻ ሳይሆን እውነተኛውን ሰብዓዊ ማንነታቸውን በማስቀመጥ ድሆች የሚባሉት ቁሳዊ ችግር ያለባቸው ሰዎች ብቻ ሳይሆኑ ነገር ግን ስደተኞች፣ የአገሬው ቀደምት ተወላጆች (indigenous) ላይ የሚደርሰው ጥቃት እና የጥቃት ሰለባዎች በተለይ ሴቶች ወይም የዘረኝነት ሰለባዎች እና ሕገወጥ የሰዎች ዝውውር ተጠቂዎች፣ የሱስ ገፈት ቀማሾች፣ በቁጥር አናሳ (ሕዳጥያን) ላይ የሚደርሰው በደል፣ የተዘነጉ አረጋውያን እና የተበዘበዙ ሠራተኞችን (4 c) ያጠቃልላል። የሪፖርቱ ጥንቅር በመቀጠል፥ “ለአደጋ ተጋላጭ ከሆኑ ሰዎች መካከል የማያቋርጥ ሙግት እና ጥረት ከሚያስፈልጋቸው መካከል ገና ያልተወለዱ በሆድ ውስጥ በጽንስ ደረጃ ያሉ ሕፃናት እና እናቶቻቸው ይገኙበታል” ብሏል። "ጉባዔው በበርካታ አህጉራት በሚገኙ ጦርነቶች እና ሽብርተኝነት የተፈጠሩትን 'የአዲሶቹ ድሆች' ጩኸት ይሰማል። ጉባኤው እንዲህ ያለውን አለመግባባት የሚፈጥሩ ብልሹ የፖለቲካ እና የኢኮኖሚ ስርዓቶችን ያወግዛል"።

“በጦርነቶች ምክንያት የተፈጠሩ 'የአዲሶቹ ድሆች' ጩኸት የሚያውቁት፣ በማህፀን ውስጥ ያሉ ህጻናት እና እናቶቻቸው ናቸው" የሚለው የጉባኤው የሪፖርቱ ጥንቅር ቀጣይነት ያለው ምክር የሚያስፈልጋቸው ለአደጋ ተጋላጭ ከሆኑት መካከል በጣም ተጋላጭ የሆኑት ናቸው። ስለዚህ ማንኛውም ዓይነት ግጭት በቅድሚያ የሚጎዳው ሕጻናትን፣ እናቶችን እና አረጋዊያንን በመሆኑ ለጦርነቶች በሙሉ መፍትሄ ያስፈልጋቸውል የሚል አቋም በሪፖርቱ ጥንቅር ውስጥ ተጠቅሷል። 'በብልሹ የፖለቲካ እና የኢኮኖሚ ሥርዓቶች' የሚፈጠሩ የሽብርተኝነት አደጋዎች መወገድ ይኖርባቸዋል ሲል የሪፖርቱ ጥንቅር አቋሙን ገልጿል።

በፖለቲካው መስክ የምዕመናን ቁርጠኝነት እና ለጋራ ጥቅም መሥራት

ከዚህ አንጻር ቤተ ክርስቲያኗ በግለሰቦች፣ በመንግሥት እና በኩባንያዎች ለሚፈጸሙት "በአደባባይ የፍትሕ መጓደል" ቁርጠኛ እንድትሆን አሳስበዋል። እናም በፖለቲካ፣ በተለያዩ ማኅበራት በተለይም በሠራተኛ ማኅበራት፣ ሕዝባዊ እንቅስቃሴዎች (4f እና 4g) ውስጥ ምዕመናን ንቁ ተሳትፎ ማድረግ ይኖርባቸውል በማለት የሪፖርቱ ጥንቅር ይገልጻል። በተመሳሳይም በትምህርት፣ በጤና እና በማኅበራዊ ዕርዳታ መስኮች የቤተ ክርስቲያኗ የተጠናከረ ተግባር “ያለ አድልዎ ወይም ማንም ሳይገለል” ሊቀጥል የገባል (4 k) ሲል በሲኖዶሳዊነት ላይ የተካሄደው የ16ኛው የካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን መደበኛ ጳጳሳት ሲኖዶስ ጉባኤ ማብቂያ ላይ ይፋ የሆነው ሪፖርት ጥንቅር ይገልጻል።

ስደተኞች

እንዲሁም በስደተኞች እና በጥገኝነት ጠያቂዎች ላይ በ16ኛው የሲኖዶስ ጉባኤ ትኩረት የተሰጠው አንዱ ጉዳይ ሲሆን “አብዛኞቹ ከትውልድ አገራቸው የመነቀል፣ የጦርነት እና የአመጽ ቁስሎችን ይሸከማሉ” በማለት የሪፖርቱ ጥንቅር የገለጸ ሲሆን፥ እነርሱ “ብዙውን ጊዜ ለሚቀበሏቸው ማኅበረሰቦች የእድሳት እና የብልጽግና ምንጭ ይሆናሉ። ከጂኦግራፊያዊ ወይም መልክዓ ምድራዊ ርቀት ካላቸው አብያተ ክርስቲያናት ጋር ቀጥተኛ ግንኙነት ለመመሥረት ዕድል ይሰጣሉ” (5 d) ሲል የሪፖርቱ ጥንቅር ገልጿል። በእነርሱ ላይ ከጊዜ ወደ ጊዜ በሚቃጣው የጥላቻ አመለካከቶችን እየተጋፈጡ ባሉበት ወቅት ጠቅላላ ጉባኤው “ግልፅ የሆነ የስደተኞች አቀባበል እንድንለማመድ ተጠርተናል፣ ለአዲስ ሕይወት ግንባታ አብረናቸው እንድንሄድ እና በሕዝቦች መካከል እውነተኛ የባሕል ትስስር እንድንፈጥር ተጠርተናል” ብሏል። በዚህ ረገድ መሠረታዊው ነገር "የሥርዓተ አምልኮ ወግ እና የስደተኞች ሃይማኖታዊ ተግባራትን ማክበር" እንዲሁም የራሳቸውን ቋንቋ ማክበር ነው። ለምሳሌ እንደ “ተልእኮ” ያለ ቃል “ወንጌልን ማወጅ ከቅኝ ግዛት፣ ከዘር ማጥፋት ጋር በተቆራኘበት አውድ ውስጥ “በሚያሰቃዩ ታሪካዊ ትዝታዎች ዛሬ ኅብረትን ያደናቅፋል” (5 e)። የሪፖርቱ ጥንቅር “በእነዚህ ሁኔታዎች ውስጥ ወንጌላውያን የተደረጉትን ስህተቶች መቀበል፣ ለእነዚህ ጉዳዮች አዲስ ግንዛቤን መማር እንዳለባቸው ይጠይቃል” ይላል።

ዘረኝነትን እና በሌላ አገር ሰዎች ላይ የሚቃጣ ጥላቻን መዋጋት

“በትምህርት፣ በውይይት እና እርስ በእርስ በመገናኘት፣ ዘረኝነትን እና በሌላ አገር ሰዎች ላይ የሚቃጣውን ጥላቻ በመዋጋት በቆራጥነት ለመሳተፍ ከቤተ ክርስቲያን በኩል እኩል ቁርጠኝነት እና እንክብካቤ ያስፈልጋል (5 p)። እንዲሁም “በቤተ ክርስቲያኗ ውስጥ የዘር ኢፍትሃዊነትን የሚፈጥሩ ወይም የሚጠብቁ ሥርዓቶችን” መለየት አስቸኳይ ጉዳይ ነው።

የምሥራቅ አብያተ ክርስቲያናት

በስደት ጉዳይ ላይ ያተኮረው የሪፖርቱ ጥንቅር የምሥራቅ አውሮፓን እና በቅርቡ የተከሰቱትን ግጭቶች በመመልከት በምሥራቅ አውሮፓ የሚገኙ ካቶሊክ የሆኑ የምሥራቃዊያን አብያተ ክርስቲያናት ብዙ ምዕመናን አብላጫ የላቲን ሥርዓት ተከታይ ወደ ሆኑ ግዛቶች እንዲጎርፉ አድርጓል። ጉባኤው “በአገር ውስጥ ላሉ የላቲን-ሥርዓት አብያተ ክርስቲያናት በሲኖዶስ ስም የተሰደዱትን ምሥራቃዊ ምእመናን ማንነታቸውን ጠብቀው እንዲኖሩ እና ልዩ ቅርሶቻቸውን እንዲያሳድጉ መርዳት አስፈላጊ ነው ይላል። የመዋሃድ ሂደቶች ሳይደረግባቸው” (6 c) በማለት አጠቃላይ ሠነዱ ይገልጻል።

ወደ ክርስቲያናዊ አንድነት መንገድ ላይ

ክርስቲያናዊ ኅብረትን በተመለከተ የሪፖርቱ ጥንቅር ስለ "መንፈሳዊ መታደስ" ይናገራል። ይህም "የንስሐ ሂደቶችን እና የማስታወስ ፈውስን" (7c) ይጠይቃል። የርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስን ስለ "የደም ክርስቲያናዊ ኅብረት" የሚለውን አባባል ጠቅሷል። ይህም “በኢየሱስ ክርስቶስ በማመን ሕይወታቸውን የሰጡ የተለያየ ግንኙነት ያላቸው ክርስቲያኖች” (7d)፣ እና ስለ ክርስቲያናዊ ኅብረት ሰማዕታት (7o) የተጠቀሱትን ሐሳቦችን ይጠቅሳል። አጠቃላይ ሪፖርቱ በተጨማሪም "በሁሉም ክርስቲያኖች መካከል ያለው ትብብር" "ቡድኖች፣ ሕዝቦች እና አገራት እርስ በርስ እንዲጋጩ የሚያደርገውን የጥላቻ፣ የመከፋፈል እና የጦርነት ባህልን ለመፈወስ" ምንጭ ነው በማለት ይገልጻል።

ምእመናን እና ቤተሰቦች (ክፍል ሁለት)

“ምእመናን እና ምዕመናት፣ በምንኩስና ሕይወት (በገዳም) ውስጥ ያሉ እና የተቀቡ አገልጋዮች እኩል ክብር አላቸው” (8 b)።  ይህ የእምነት ቃል በሪፖርቱ ጥንቅር  ላይ በአጽኖት ተደጋግሞ ተገልጿል። ይህም ምእመናን እንዴት “በክርስቲያን ማኅበረሰቦች ውስጥ አገልግሎታቸው እየጨመረ መሄዱን እና ንቁ የሆነ አስተዋጾ እያደርጉ እንደ ሆነ” ያስታውሳል። (8 e) የእምነት አስተማሪዎች፣ የነገረ መለኮት ሊቃውንት፣ የሕነጻ ትምህርት ቤት አስተማሪዎች፣ የመንፈሳዊ  እንቅስቃሴ መሪዎች እና ካቴኪስቶች፣ በእምንት ጥበቃ እና በአስተዳደር ውስጥ ንቁ ተሳትፎ ያደርጋሉ። አስተዋጾዎቻቸው “ለቤተ ክርስቲያኗ ተልዕኮ አስፈላጊ ናቸው” (8 f) ሲል አጠቃላይ ሪፖርቱ ገልጿል። ስለዚህ ልዩ ልዩ መክሊቶች “የተጠሩ፣ እውቅና የተሰጣቸው እና ሙሉ በሙሉ አድናቆት ያላቸው” (8 f) መሆን አለባቸው። ችላ ሊባሉ፣ ጥቅም ላይ ሳይውሉ እንዲቀሩ ወይም “የቀሳውስትን የበላይነት” (8 f) የሚያሳዩ መሆን የለባቸው።

ሴቶች በቤተ ክርስቲያኗ ሕይወት እና ተልዕኮ ውስጥ

እንግዲያውስ በሁሉም የሕይወታቸው ዘርፍ፣ ሐዋርያዊ አገልግሎት እና ቅዱሳን ምስጢራትን ጨምሮ ሴቶችን በማጀብ እና አብሮ በመጓዝ እንዲሁም ለመረዳት በቤተ ክርስቲያኗ በኩል ጠንካራ የቁርጠኝነት ጥሪ አለ። ሴቶች “አሁንም በፆታዊ ጥቃት፣ በኢኮኖሚ መበላለጥ እና እነርሱን እንደ ዕቃ የመመልከት ዝንባሌ በሚታይባቸው ማኅበረሰቦች ውስጥ ፍትህን ለማግኘት ይጮኻሉ”(9 c)። “የሐዋርያዊ አገልግሎት እጀባ እና ጠንካራ የሴቶች ቅስቀሳ አብሮ መሄድ አለበት” ብሏል አጠቃላይ ሪፖርቱ።

የቀሳውስት የበላይነት

በሲኖዶሱ ላይ የተገኙ ብዙ ሴቶች “ለካህናት እና ለብጹዓን ጳጳሳት ሥራ ጥልቅ ምስጋናቸውን ገልጸዋል”። ነገር ግን “ስለሚያቆስል ቤተ ክርስቲያንም ተናግሯል።” (9 f) “ቀሳውስት የበላይ ናቸው የሚለው እምነት የጥላቻ አስተሳሰብ እና ተገቢ ያልሆነ የሥልጣን መግለጫ ጠባሳውን ማስቀመጥ ቀጥሏል። የቤተ ክርስቲያን ገጽታ እና ኅብረት ያበላሻል። "ለማንኛውም ውጤታማ መዋቅራዊ ለውጥ መሠረት እንዲሆን ጥልቅ መንፈሳዊ ለውጥ ያስፈልጋል" እናም ጠቅላላ ጉባኤው "ወንዶች እና ሴቶች አብረው የሚነጋገሩባትን ቤተ ክርስቲያን ለማስተዋወቅ እንፈልጋለን… መገለል እና ውድድር” አስፈላጊ አይደለም ብሏል አጠቃላይ ሪፖርቱ።

የድቁና አገልግሎትን ለሴቶች ክፍት ማድረግ ይገባልን?

የድቁና አገልግሎትን ለሴቶች ስለመክፈት የቀረቡ የተለያዩ አስተያየቶች ተቀባይነት አግኝተዋል (9 j)። ለአንዳንዶች "ተቀባይነት የለውም። ምክንያቱም ከወግ ወይም ትውፊት ጋር መቋረጥ አድርገው ስለሚቆጥሩት"። ይህ ሐሳብ ለሌሎች፣ የጥንቷን ቤተ ክርስቲያን ልማድ ይመልሳል የሚል አንድምታ አለው። ሌሎች ደግሞ “ለዘመኑ ምልክቶች ተገቢ እና አስፈላጊ ምላሽ…ይህ በቤተ ክርስቲያኗ ውስጥ አዲስ ጉልበት እና ኃይል በሚፈልጉ በብዙዎች ልብ ውስጥ የሚያስተጋባ” አድርገው ይመለከቱታል። ከዚያም ለሴቶች የድቁና አገልግሎት መከፈቱ “የሚያስጨንቅ የአንትሮፖሎጂ (ሥነ-ስብዓዊ) ውዥንብር የሚፈጥር፣ ይህ የድቁና አገልግሎት ለሴቶች ከተፈቀደ ቤተ ክርስቲያንን ከዘመኑ መንፈስ ጋር ያጋባታል” የሚል ስጋት ያላቸውም አሉ። የሲኖዶሱ አባቶች እና እናቶች በሊቃነ ጳጳሳቱ የተቋቋሙትን ልዩ ኮሚሽኖች ውጤቶች እንዲሁም የነገረ መለኮት፣ ታሪካዊ እና ገላጭ ጥናቶችን በመጠቀም፣ “በሴቶች የድቁና ማዕረግ ተደራሽነት ላይ ያለውን ሥነ-መለኮታዊ እና ሐዋርያዊ አገልግሎት ላይ የሚደርገው ጥናት” እንዲቀጥል የጠየቁም ይገኙበታል። ከተቻለ" ይላሉ "የዚህ ምርምር ውጤቶች በሚቀጥለው የጉባዔው ስብሰባ ላይ መቅረብ አለባቸው" (9 n) ሲል አጠቃላይ ሪፖርቱ ገልጿል።

አድልዎ እና በደል

እስከዚያው ድረስ "ሴቶች በውሳኔ አሰጣጥ ሂደቶች ውስጥ እንዲሳተፉ እና በሐዋርያዊ አገልግሎቶች እንክብካቤ እና አገልግሎት ውስጥ የኃላፊነት ሚና እንዲጫወቱ" የማረጋገጥ አስቸኳይ ጉዳይ በድጋሚ ተነግሯል። ይህም የቀኖና ሕግ (9m) ማስተካከያ መደረግ እንዳለበት አጠቃላይ ሪፖርቱ ይፋ አድርጓል። በቤተ ክርስቲያን ውስጥ የሚገኙ ደናግል ብዙ ጊዜ እንደ “ርካሽ ጉልበት” (9 o) ተደርገው የሚታዩባቸውን ጨምሮ የቅጥር አድልዎ እና ኢ-ፍትሃዊ ክፍያ ጉዳዮች መታረም አለባቸው። በተመሳሳይ የሴቶች የሥነ መለኮት ትምህርት እና የሥልጠና መርሃ ግብሮች ተደራሽነት መስፋፋት አለበት(9 p)። በሥርዓተ አምልኮ ጽሑፎች እና በቤተ ክርስቲያን ሠነዶች (9 q) ማሻሻያ ሊደረግባቸው ይገባል የሚሉ ሐሳቦች እንደ ተነሱ አጠቃላይ ሪፖርቱ ገልጿል።

የተቀደሰ ሕይወት

የተለያዩ የተቀደሰ የሕይወት (ገዳማዊያን/ገዳማዊያት) ዓይነቶችን ብልጽግና እና ልዩነት በመመልከት ሪፖርቱ “የውይይት ቦታ የማይሰጥ የአምባገነን ዘይቤ ጽናት” መወገድ እናዳለበት ያስጠነቅቃል። ሪፖርቱ በተጨማሪም “በሃይማኖታዊ ሕይወት ውስጥ ባሉ ሰዎች እና በምእመናን ማኅበራት በተለይም በሴቶች ላይ የደረሰው የተለያየ ዓይነት በደል የተፈጸመባቸው ጉዳዮች በሥልጣን አጠቃቀም ላይ ችግር እንዳለ የሚጠቁሙና ቆራጥ እና ተገቢ ጣልቃ ገብነትን የሚጠይቁ ናቸው” (10 d) ሲል ገልጿል።

ዲያቆናት እና የዘረዓ ክህነት የሕነጻ ትምህርት ሂደቶች

ጉባኤው በመቀጠል ለተቀቡ አገልጋዮች ምስጋናውን ያቀርባል። “ለሰዎች ቅርብ በሆነ መንፈስ ሁሉንም በመቀበል እና በማዳመጥ ጥልቅ የሆነ ስብዕና እና የጸሎት ሕይወትን እያዳበሩ የእግዚአብሔርን ሕዝብ በማገዝ አገልግሎታቸውን እንዲኖሩ የተጠሩት” ሁሉ በእዚሁ መንገድ መቀጠል ይኖርባቸዋል ሲል አጠቃላይ ሪፖርቱ ያሳስባል። ሪፖርቱ ከሰዎች እና ከተቸገሩ ሰዎች ጋር "የቅርብ ግንኙነት" መፍጠርን በማረጋገጥ "ከመጀመሪያ ደረጃ የዘረዓ ክህነት የሕነጻ ትምህርት አንስቶ በቤተ ክርስቲያን ውስጥ ያላግባብ የቀሳውስትን የበላይነት መንፈስ ማረጋገጥ የሚቃወሙ አስተምሕሮችን ማግኘት ይኖርባቸዋል። በቤተ ክርስቲያን ውስጥ ያለ አግባብ የቀሳውስትን የበላይነት ማረጋገጥ አደገኛ መሆኑን አጠቃላይ ሪፖርቱ ያስጠነቃቃል። ጥያቄው በእነዚህ መስመሮች ውስጥ የዘርዓ ክህነት ተማሪዎች ወይም ሌሎች መንፈሳዊ አገልግሎት መስጠት የሚያስችሉ የሕነጻ እጩ ተማሪዎች የሚሰጡ ትምህርቶች ከማኅበረሰቦች የዕለት ተዕለት ኑሮ ጋር እንዲተሳሰሩ፣ “ወደ ፈላጭ ቆራጭነት የሚወስዱትን መዋቅራዊ እና የአስተሳሰብ አደጋዎችን ለማስወገድ የአመለካከቶች እና የእውነተኛ መንፈሳዊ ጥሪ እድገት እንቅፋት ናቸው" ሲል አጠቃላይ ሪፖርቱ ገልጿል።

በድንግልና መኖር (ባሕታዊነት)

በጉባኤው ላይ የተለያዩ ግምገማዎች የተደረገበት በድንግልና መኖር (ባሕታዊነት) የተመለከቱ ሐሳቦች ተጠቅሰው ነበር። በድንግልና መኖር (ባሕታዊነት) “ዋጋ ያለው ትንቢታዊ እና ስለ ክርስቶስ ጥልቅ ምሥክርነት የሚሰጥ” በመሆነ ሁሉም አድንቀዋል።  ሪፖርቱ እንዳመለከተው አንዳንዶች “ከሥነ-መለኮት አኳያ ለክኅነት አገልግሎት ተገቢነቱ በላቲን ቤተ ክርስቲያን ውስጥ እንደ ሥነ-ሥረዓታዊ ግዴታ ሆኖ መተርጎም አለበት። ከሁሉም በላይ በቤተ ክርስቲያን እና በባሕላዊ አውድ ውስጥ ይበልጥ አስቸጋሪ ያደርገዋል። ይህ ውይይት አዲስ አይደለም ነገር ግን ተጨማሪ ግምገማን ይፈልጋል” ሲል አጠቃላይ ሪፖርቱ ገልጿል።

ጳጳሳት

“የሲኖዶሳዊነት ምሳሌን” (12 c) በመጠቀም “የጋራ ኃላፊነትን” በተግባር በማዋል የተጠሩት የጳጳሱ ምስል እና ሚና ላይ ብዙ አስተንትኖ ተድረጓል። በሀገረ ስብከት ውስጥ ያሉ ሌሎች ተዋናዮች እና የሃይማኖት አባቶች ተልዕኮውን ሊያደናቅፍ የሚችለውን "የአስተዳደር እና ሕጋዊ ግዴታዎች" ሸክም መጋራት አለባቸው።

ከዚህ ጋር ተያይዞ ጳጳስ ሁልጊዜ የሚፈልገውን ሰብዓዊ እና መንፈሳዊ ድጋፍ አያገኝም። "አንድ የተወሰነ የብቸኝነት ስሜት የተለመደ አይደለም" ስለዚህ ሁሉንም ማሳተፍ ይኖርበታል።

ተገቢ ያልሆኑ ጥቃቶች

“ብዙ ጳጳሳት የአባትን ሚና ከዳኝነት ጋር ለማስታረቅ በሚያስቸግር ሁኔታ ውስጥ ያስቀምጣሉ” የሚሉ ጥያቄዎች አሉ። አጠቃላይ ሪፖርቱ “የዳኝነትን ተግባር በሕገ ቀኖና ሊደገፍ ወደሚችል ሌላ አካል የመመደብ ተገቢነት” ይደግፋል።

በዘረዓ ክህነት ውስጥ የሚሰጥ የሕነጻ (Formation) ትምህርት ሂደት (ክፍል 3)

“በግንኙነት እና በጾታዊ ትምህርት ላይ ሥራ እንዲሠራ፣ ወጣቶች በግላቸውና በጾታ ማንነታቸው እስኪበስሉ ድረስ ለማገዝ በሚያስችል መልኩ አብሮ ለመጓዝ እንዲሁም በድንግልና እና በንጽሕና እንዲኖሩ የተጠሩትን ገዳማዊያን/ ገዳማዊያት በሚገባ መልኩ ብስለት ላይ እስኪደርሱ ድረስ አብሮ መጓዝ እና መደገፍ አስፈላጊ እንደ ሆነ እና ይህንን ይበልጥ የሚያጠናክር “ሲኖዶሳዊ አካሄድ” እንዲመሠረት ተጠይቋል።  ሪፖርቱ "በቤተ ክርስቲያኗ ውስጥ አወዛጋቢ የሆኑትን ጉዳዮች በጥንቃቄ መመርመር" ማለትም ከሌሎች ጉዳዮች ጋር "እንደነዚህ ያሉ ጉዳዮች" ጥልቅ በሆነ መልኩ እንዲከናወኑ ለማድረግ "በሰው ልጅ ሳይንስ መካከል ያለውን ውይይት" ማጠናከር አስፈላጊ መሆኑን አጽንዖት ሰጥቶ ተናግሯል። ከማንነት እና ከፆታዊ ግንኙነት፣ ከሕይወት ፍጻሜ፣ ከተወሳሰቡ የጋብቻ ሁኔታዎች እና ሰው ሠራሽ አስተውሎት (አርቴፊሻል ኢንተለጀንስ) ጋር የተያያዙ የሥነ- ምግባር ጉዳዮችን የሚመለከቱ ናቸው። እንደነዚህ ያሉት ጉዳዮች በኅብረተሰብ እና በቤተ ክርስቲያን ውስጥ በትክክል “አዲስ ጥያቄዎችን ስለሚያቀርቡ” አከራካሪ ናቸው። “ግለሰቦችን እና የቤተ ክርስቲያንን አካል የሚጎዱ ቀላል ፍርዶች ሳንሰጥ ለዚህ ነጸብራቅ የሚያስፈልገውን ጊዜ ወስደን የምንችለውን ጉልበት ማውጣታችን አስፈላጊ ነው” ሲል አጠቃላይ ሪፖርቱ የገለጸ ሲሆን፥ የቤተ ክርስቲያን አስተምህሮ እንደሚሰጥ አስታውሷል። በአብዛኛዎቹ ጉዳዮች ላይ የመመሪያ ስሜት፣ ነገር ግን ይህ ትምህርት አሁንም ወደ ሐዋርያዊ አገልግሎት ልምምድ መተርጎምን ይጠይቃል።

ማዳመጥ

በተመሳሳይ ስጋት አጠቃላይ ሪፖርቱ “በጋብቻ ሁኔታቸው፣ በማንነታቸው ወይም በግብረ ሥጋ ግንኙነት ምክንያት ከቤተ ክርስቲያን የተገለሉ ወይም እንዲርቁ የተደረጉ ሰዎችን” ለመስማት እና አብሯቸው ለመጓዝ የቀረበውን ግብዣ ያድሳል። “በቤተ ክርስቲያኗ ለተጎዱ ወይም ችላ ለተባሉ፣ ‘ቤት’ ተብሎ የሚጠራ ቦታ ለሚፈልጉ፣ ደህንነታቸው የሚሰማቸው፣ የሚሰሙበት እና የሚከበሩበት ቦታ ለሚፈልጉ በጉባኤው ውስጥ ጥልቅ የፍቅር፣ የምህረት እና የርህራሄ ስሜት ተሰምቶ ነበር። አጠቃላይ ሪፖርቱ እንደሚለው፥ "ክርስቲያኖች ሁል ጊዜ ለእያንዳንዱ ሰው ክብር አክብሮት ማሳየት አለባቸው" ሲል ጠቅላላ ሪፖርቱ አጽንዖት ሰጥቶ ገልጿል።

ከአንድ ሚስት በላይ ማግባት

በሲኖዶስ አዳራሽ ውስጥ ከአፍሪካ በመጡ አንዳንድ የሲኖዶስ አባላት አማካይነት ከቀረቡት ተሞክሮዎች አንፃር፣ ሴካም (የአፍሪካ እና ማዳጋስካር ጳጳሳት ጉባኤ) ከአንድ በላይ ማግባትን በተመለከተ “ሥነ መለኮታዊ እና በማስተዋል ጥበብ የተደገፈ ሐዋርያዊ አገልግሎት” እንዲበረታታ ጥያቄ መቅረቡን ጠቅላላ ሪፖርቱ አስታውሷል። ከአንድ ሚስት በላይ ያገቡ ሰዎች ወደ እምነት የሚመጡበትን” መንገድ ማበረታታት ይኖርብናል ብለዋል።  

ዲጂታል ባሕል

በመጨረሻም የየሪፖርቱ ጥንቅር ዘገባ ስለ ዲጂታል ምህዳር ይናገራል፡- “ሰዎች በተንቀሳቃሽ ስልኮቻቸው እና በታብሌቶቻቸው የሚገቡባቸውን ቦታዎች ጨምሮ ትርጉም እና ፍቅር በሚፈልጉባቸው ቦታዎች ሁሉ የዛሬውን ባሕሕል ለመድረስ መሞከር የኛ ፋንታ ነው። በይነመረቡ “እንደ ማስፈራራት፣ የሐሰት መረጃ፣ የወሲብ ብዝበዛ እና ሱስን የመሳሰሉ ጉዳቶችን ሊያስከትል እንደሚችል ያስታወሰው አጠቃላይ ሪፖርቱ አክሎም፥ “የክርስቲያን ማኅበረሰብ እንዴት በዲጂታል ምህዳር ላይ ቦታው ደህንነቱ የተጠበቀ ብቻ ሳይሆን መንፈሳዊ ሕይወት ሰጪ መሆኑን ለማረጋገጥ ቤተሰቦችን እንዴት መደገፍ እንደሚችሉ ማጤን ያስፈልጋል” (17 f) ሲል በሲኖዶሳዊነት ላይ ሲካሄድ የቆየው 16ኛው የካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን ጳጳሳት የሲኖዶስ ጉባኤ፥ 40 ገጾች ያሉትን የጠቅላላ ሪፖርት ጥንቅር በማውጣት በጥቅምት 18/2016 ዓ. ም. በቅዱስ ጴጥሮስ ባዚሊካ በተካሄደው መስዋዕተ ቅዳሴ ተጠንቋል።

በዕለቱ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮስ ባሳረጉት መስዋዕተ ቅዳሴ ላይ ባሰሙት ስብከት፥ "ጌታ ይመራናል፤   የበለጠ ሲኖዶሳዊ እና ሚሲዮናዊ ቤተ ክርስቲያን እንድንሆን እርሱ ይደግፈናል፤ እግዚአብሔርን የምታመልክ እና የዘመናችንን ሴቶች እና ወንዶች የምታገለግል፣ ለሁሉም የሚያፅናና የወንጌል ደስታን ለማምጣት የምትወጣ ቤተ ክርስቲያን እንድንሆን” እግዚአብሔር ይረዳናል” ሲሉ ቅዱስነታቸው በስብከታቸው ማጠቃለያ መናገራቸው ይታወሳል።

 

 

 

 

 

10 November 2023, 11:45