ፈልግ

ር. ሊ. ጳ. ፍራንችስኮስ ሞንጎሊያን በጎበኙበት ወቅት ር. ሊ. ጳ. ፍራንችስኮስ ሞንጎሊያን በጎበኙበት ወቅት  (VATICAN MEDIA Divisione Foto)

ሰባተኛው የቡዳ እና የክርስትና እምነቶች ውይይት በባንኮክ መጀመሩ ተነገረ

“ካሩና እና አጋፔ የቆሰለውን የሰው ልጅ እና ምድርን ለመፈወስ የሚደረግ ውይይት” በሚል መሪ ርዕሥ ሰባተኛው የቡዳ እና የክርስትና እምነቶች ስብሰባ በታይላንድ መዲና ባንኮክ በሚገኝ አንድ ዩኒቨርሲቲ ውስጥ ከሰኞ ኅዳር 3 እስከ ሐሙስ ኅዳር 6/2016 ዓ. ም. ድረስ በመካሄድ ላይ እንደሚገኝ ታውቋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

ሰባተኛው የቡዳ እና የክርስትና እምነቶች ስብሰባ፥ “ካሩና እና አጋፔ የቆሰለውን የሰው ልጅ እና ምድርን ለመፈወስ” በሚል መሪ ሃሳብ ሰኞ ኅዳር 3/2016 ዓ. ም. በባንኮክ መጀመሩ ታውቋል።

ስብሰባው በታይላንድ መዲና ባንኮክ ውስጥ በሚገኝ አንድ ዩኒቨርሲቲ ውስጥ ከሰኞ ኅዳር 3 እስከ ሐሙስ ኅዳር 6/2016 ዓ. ም. ድረስ እንደሚካሄድ በጳጳሳዊ ምክር ቤት፣ የሐይማኖት ተቋማት የጋራ ውይይት አስተባባሪ ጽሕፈት ቤት ትናንት ሰኞ ባወጣው መግለጫ አስታውቋል።

ስብሰባውን በሕብረት ያዘጋጁት በጳጳሳዊ ምክር ቤት፣ የሐይማኖት ተቋማት የጋራ ውይይት አስተባባሪ ጽሕፈት ቤት እና በባንኮክ ከተማ የሚገኝ በቡዳ እምነት የሚተዳደር ዩኒቨርሲቲ መሆናቸው ታውቋል።

የሐይማኖት ተቋማት የጋራ ውይይት አስተባባሪ ጽሕፈት ቤት በመግለጫ እንደገለጸው፥ “ስብሰባው በዓለም ዙሪያ በተለይም በታይላንድ ውስጥ ከቡዳ እምነት አጋሮች ጋር በመግባባት የተገነባው ጓደኝነትን እና የእርስ በርስ መግባባትን ያረጋግጣል፤ በተጨማሪም የሰውን ልጅ እና የምድሪቱን ቁስል ለመፈወስ የተወሰዱ የጋራ ድርጊቶችን ለይቶ ይመለከታቸዋል" ሲል ገልጿል።

ከካምቦዲያ፣ ከሆንግ ኮንግ፣ ከሕንድ፣ ከጃፓን፣ ከማሌዥያ፣ ከሞንጎሊያ፣ ከምያንማር፣ ከሲንጋፖር፣ ከሲሪላንካ፣ ከደቡብ ኮሪያ፣ ከታይላንድ፣ ከታይዋን እና ዩናይትድ ኪንግደምን ጨምሮ ከተለያዩ አገራት የመጡ ቡዳ እና የክርስትና እምነቶች ተከታዮች ስብሰባውን እንደሚካፈሉት ታውቋል።

በመክፈቻው ሥነ ሥርዓት ላይ የአካባቢው ባለስልጣናት እና በታይላንድ ውስጥ የሚገኙ የሌሎች ሃይማኖቶች ተወካዮች የመልካም ምኞት ሰላምታቸውን ያቀረቡ ሲሆን፣ በዕለቱ የተካሄደው የችግኝ ተከላ ሥነ-ሥርዓ የስብሰባው ተሳታፊዎች ምድሪቱን ለመንከባከብ እና ለመፈወስ ያላቸውን ቁርጠኝነት እንደሚገልጽ ታውቋል።

 

14 November 2023, 16:37