ፈልግ

ሊቀ ጳጳስ ገብርኤል ካቺያ ሊቀ ጳጳስ ገብርኤል ካቺያ 

ቅድስት መንበር የኑክሌር ጦር መሳሪያ ቅነሳ ላይ የሚደረገውን ትብብር እንደምትደግፍ ተገለፀ

በተባበሩት መንግስታት የቅድስት መንበር ቋሚ ታዛቢ የሆኑት ሊቀ ጳጳስ ጋብሪኤሌ ካቺያ የኒውክሌር ጦር መሳሪያ ከሌሎቹ ይልቅ በሴቶች እና ልጃገረዶች ላይ የሚያደርሰውን የከፋ ተፅእኖ በማሳየት፥ በኒውክሌር ጦር መሳሪያ ክልከላ እና በነባር ትጥቅ የማስፈታት እርምጃዎች መካከል ያለውን መመሳሰል አመላክተዋል።

  አቅራቢ ዘላለም ኃይሉ ፥ አዲስ አበባ

የኒውክሌር ጦር መሳሪያዎች አስከፊ ሰብአዊ እና አካባቢያዊ መዘዞች እንዳላቸው፣ አደጋዎችን እንደሚያበዙ እና 'ዘላቂ ያልሆነ ሰላምን' ብቻ እንደሚያመጡ እሙን ነው።

ስለዚህ የኑክሌር ጦር መሣሪያ ክልከላ ስምምነት፥ ከአቶሚክ ጦር መሣሪያ ነፃ የሆነች ዓለም “የሚቻል እና አስፈላጊ እንደሆነ እንዲሁም ይህንን ግብ በውይይት እንድናሳካ የሚያስችል ዘዴ እንደሚሰጠን” ያስታውሰናል።

እንዚህ ከላይ የተጠቀሱት ሃሳቦች በተባበሩት መንግስታት የቅድስት መንበር ቋሚ ታዛቢ የሆኑት ሊቀ ጳጳስ ገብርኤሌ ካቺያ እ.አ.አ. በ2017 የተፈረመው እና በዓለም ዙሪያ በ56 ሀገራት የጸደቀውን ሁለተኛው የስምምነቱ አባል ሀገራት ስብሰባ ላይ ያነሷቸው ነጥቦች ናቸው።

ሊቀ ጳጳሱ በኑክሌር የጦር መሣሪያ ክልከላ ላይ የተፈረመውን ስምምነት መሠረታዊ ጉዳዮችን በሚመለከቱ ሁለት ነጥቦች ላይ ትኩረት አድርገው አንስተዋል። የመጀመሪያው “የስምምነቱ የሥርዓተ-ፆታ ድንጋጌዎችን መተግበር” ሲሆን፥ ሁለተኛው “ስምምነቱ አሁን ካለው የኒውክሌር ጦር መሳሪያ ቅነሳ ሂደት ጋር ያለውን ትሥሥር እና በፍጥነት ያለመተግበር ሁኔታ” የሚሉት ናቸው።

የፆታ ልዩነት

የሥርዓተ-ፆታ ልዩነትን አስመልክቶ ሊቀ ጳጳስ ካቺያ እንደተናገሩት ለረጅም ጊዜ የኒውክሌር ጦር መሳሪያዎች ለፍንዳታ፣ ለሙቀት እና ለጨረር የተጋለጡትን ሰዎች እኩል ይጎዳሉ ተብሎ ይታመን ነበር። ይሁን እንጂ አዳዲስ ሳይንሳዊ መረጃዎች እንደሚያሳዩት ይህ እንዳልሆነ እና በኒውክሌር ጦር መሳሪያ ፍንዳታ አማካይነት የሚከሰተው ጨረር በሴቶች እና ልጃገረዶች ላይ ከባድ የሆነ ተጽእኖ እንደሚያሳድር ተናግረዋል።

ሊቀ ጳጳስ ካቺያ ስምምነቱ ይህንን በትክክል እንደተገነዘበ እና “ለተጎጂዎች የሚሰጠው የእርዳታ አቅርቦት የእያንዳንዱን ግለሰብ ፍላጎት ግምት ውስጥ በማስገባት እንዲሰጥ ይጠይቃል” ብለዋል።

በሴቶች ላይ ያለው ተጽእኖ

ጥናቶች እንደሚያሳዩት ከተወለዱበት ጊዜ አንስቶ እስከ አምስት ዓመት ዕድሜ ድረስ ያሉ ለጨረር የተጋለጡ ልጃገረዶች ከሌሎቹ አውሮፓውያን ወንዶች ጋር ሲነፃፀሩ በካንሰር የመያዝ ዕድላቸው በአሥር እጥፍ እንደሚበልጥ ነው። ይህ በሴቶች እና ህጻናት ላይ የበለጠ ተፅእኖ እንዲፈጠር ምክንያት የሆኑትን ነገሮች ለማወቅ በእናቶች እና በፅንስ ጤና ክትትል ላይ ባሉት ተጨማሪ ጥናቶች እንደሚያስፈልጉ ሊቀ ጳጳስ ካሲያ ገልፀዋል። በማከልም በዚህ ጥናት የሚገኝ ግንዛቤ “ለአዮናይዚንግ ለተባለው ጨረር የተጋለጡ ሴቶች የራሳቸውን እና የልጆቻቸውን ጤና ለመጠበቅ በቂ እንክብካቤ እንዲያገኙ ለማድረግ” ወሳኝ ነው ብለዋል።

ሊቀ ጳጳሱ በመቀጠል “ጠንካራ ሳይንሳዊ መሠረት አለመኖሩ አገሮች በተለይም ሴቶችን እና ልጃገረዶችን በሚመለከቱ ጉዳዮች ላይ የስምምነቱ አወንታዊ ግዴታዎች ውጤታማ በሆነ መንገድ እንዳይተገበሩ እንቅፋት ይሆናል” ሲሉ አጽንኦት በመስጠት ተናግረዋል።

የቋንቋ አጠቃቀም

እነዚህ ፆታን በተመለከተ ግልጽ ያልሆነ የቋንቋ አጠቃቀሞች ሲሆኑ፥ ለተጎጂዎች እገዛ ለማድረግ በሚደረጉ ውይይቶች መሃል ህጋዊ ያልሆኑ ቃላትን መጠቀም፣ የሕክምና እንክብካቤን በሚመለከት ከፋፋይ ቋንቋዎች መጠቀም፣ እና ስምምነት ላይ ያልተደረሱባቸውን የተባበሩት መንግስታት ጽሑፎችን መጥቀስ ናቸው። በነዚህ ጉዳዮች ምክንያት “ቅድስት መንበር በሪፖርቱ ውስጥ የተዘረዘሩትን ምክሮች መደገፍ አትችልም” ብለዋል ሊቀ ጳጳስ ካቺያ።

በስምምነቱ ውስጥ የሥርዓተ-ፆታ ድንጋጌዎችን አተገባበር አስመልክቶ ንግግራቸውን ሲያጠቃልሉ ሊቀ ጳጳስ ካቺያ አጽንኦት ሰጥተው እንዳስታወቁት፥ በእነዚህ ጉልህ ሥጋቶች ምክንያት “የሥርዓተ-ፆታ የትኩረት ነጥብ ማካተት በስምምነቱ መካከል ባለው መዋቅር ውስጥ ወደፊት እንደገና መታየት እንደሚያስፈልግ ቅድስት መንበር ትገነዘባለች” ብለዋል።

በስምምነቱ እና በነባሩ የኑክሌር መስፋፋት ቁጥጥር ሥርዓት መካከል ያለው ግንኙነት

በስምምነቱ እና በነባር የኒውክሌር ትጥቅ ማስፈታት እንዲሁም መስፋፋት ቁጥጥር ሥርዓት መካከል ያለውን ግንኙነት በተመለከተ ሊቀ ጳጳስ ካቺያ እንዳስታወቁት የኑክሌር ጦር መሳሪያዎች ክልከላ ተጨማሪ ፕሮቶኮልን በማስፈጸም እና የኑክሌር ጦር መሳሪያ መከላከል ውል አንቀጽ 6ን እንደሚያጠናክር ጠቁመዋል። “የኒውክሌር መስፋፋት ቁጥጥር የትግበራ ጥረቶች በተለይም በመሳሪያ ማስፈታት ዘውግ ውስጥ ቢኖሩም፥ ትጥቅ የማስፈታት እና ቁጥጥር ስርዓት የማዕዘን ድንጋይ ሆኖ ይቆያል” ብለዋል።

ሁሉም ስምምነቶች አንድ ላይ

ሊቀ ጳጳስ ካቺያ ንግግራቸውን በመቀጠል በ ‘ጠቅላላ የኑክሌር ሙከራ ክልከላ ስምምነት’ (CTBT) እና በኑክሌር ጦር መሳሪያዎች ክልከላ ስምምነት (TPNW) መካከል ያለውን እምቅ ውህደት አጽንዖት ሰጥተው ተናግረዋል።

ከዓለም አቀፍ የክትትል ስርዓት የተገኘውን መረጃ የኑክሌር ጦር መሳሪያዎች ክልከላ ስምምነት ግዴታዎችን ለመደገፍ ጥቅም ላይ ማዋል አስፈላጊ መሆኑን ገልፀው፥ በኑክሌር ጦር መሳሪያዎች ክልከላ ስምምነት ፈራሚ ሃገራት እና ጠቅላላ የኑክሌር ሙከራ ክልከላ ስምምነት ፈራሚዎች መካከል ትብብር እንዲኖር አሳስበዋል። ይህንንም በማስመልከት እንደተናገሩት “የኑክሌር ጦር መሳሪያዎች ክልከላ ስምምነት እና የጠቅላላ የኑክሌር ሙከራ ክልከላ ስምምነት ግብ እና ዓላማዎች እርስ በርስ የሚደጋገፉ እና የሚያራምዱ በመሆናቸው በትይዩ ተደጋግፈው መሄድ አለባቸው” ሲሉ አብራርተዋል።

ሊቀ ጳጳስ ካቺያ “በኒውክሌር ጦር መሣሪያ እንቅስቃሴዎች የሚደርሰውን ሰብዓዊና አካባቢያዊ ጉዳቶችን ግንዛቤ ማሳደግ ስለሚችል እና እንደዚህ አይነት ጉዳቶችን ለመፍታት ለሚደረገው ጥረት አስተዋፅዖ ስለሚያደርግ፥ ቅድስት መንበር በኑክሌር ጦር መሳሪያዎች ክልከላ ስምምነት ፈራሚ ሃገራት እና በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የአቶሚክ ጨረራ ውጤቶች ሳይንሳዊ ኮሚቴ (UNSCEAR) መካከል ከዚህ የበለጠ ትብብር እንዲኖር ትደግፋለች” በማለት አስረድተዋል።
 

04 December 2023, 13:32