ፈልግ

የሩስያ እና የዩክሬይን ጦርነት የሩስያ እና የዩክሬይን ጦርነት  (ANSA)

በዩክሬን ለሁለት ዓመታት የተካሄደው ጦርነት እስከ መቼ ድረስ ይዘልቃል?

በዩክሬን ውስጥ ተቀስቅሶ ለሁለት ዓመታት የቆየው ጦርነት በዜጎች ላይ የሚያስከትለው ጥቃት ቆሞ ፍትሃዊ ሰላም እንዲወርድ ለመወያየት ምን መደረግ እንደሚገባ የቅድስት መንበር መገናኛዎች ርዕሠ ዋና አዘጋጅ አንድሬያ ቶርኔሊ ጠይቋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

ምንም እንኳን በቅርብ ወራት ውስጥ ከቅድስት ሀገር እየወጡ የሚገኙ አስፈሪ ዜናዎች እና የሩስያዊው ተቃዋሚ የናቫልኒ ሞት ከዩክሬን የሚወጡ የጦርነት ዘገባዎችን ቢያጨልመውም ዛሬ ግን ማስታወስ እንፈልጋለን። ዩክሬን ውስጥ በሃያ አራት ወራት ውስጥ የተከሰተውን የሕህዝብ ስቃይ ለመቅረፍ፣ ለጥላቻ ዕድል ለማይሰጡ፣ የሰላም ጸሎታቸውን ለቀጠሉ እና አሁንም እየሠሩ ለሚገኙ የምሥክርነት ድምፅን ለመስጠት ከቅርብ ቀናት ወዲህ ጥረት ስናደርግ ቆይተናል። የቦምብ ጥቃት የተፈጸመባቸው ሰዎች ብዛት ቁጥራቸው እንዲናገሩ ስናደርግ ቆይተናል። ምክንያቱም እየተከሰተ ያለው ተጨባጭ እውነታ ብዙ ጊዜ ከትኩረት የራቀው የዚህን ጦርነት ኢ-ሰብአዊነት ይገልፃል። የጥቂት ኪሎ ሜትሮች መሬትን ለመውረስ ሲባል በአሥር ሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎች ሕይወት ተሰውቷል። በአሥር ሺዎች የሚቆጠሩ ወንዶች፥ ወጣት እና አዛውንት ቆስለዋል ወይም አካለ ጎደሎ ሆነዋል። የዩክሬን ከተሞች በሙሉ ወድመዋል። በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ተፈናቃዮች በውጭ አገራት ይኖራሉ። በሺዎች የሚቆጠሩ ፈንጂዎች የንጹሃንን ሕዝብ የወደፊት ሕይወት ለመናድ ተዘጋጅተዋል...። ወረራዉ እንዲቆም እና በጠረጴዛ ዙሪያ ተቀምጠን ፍትሃዊ ሰላም እንዲወርድ ለመደራደር ምን መደረግ አለበት?

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ የሰዎችን ትኩረት ለመሳብ በጦርነት የተጎዳች ዩክሬንን በማስመልከት ያቀረቡት ሥፍር ቁጥር የሌላቸው የሰላም ጥሪዎች ጆሮ ዳባ ልበስ ተብለዋል። ጦርነት እና አመጽ አለመግባባቶችን የመፍቻ መንገድ ሆነዋል። ወደፊት የሚከሰቱ ጦርነቶችን በማሰብ የሚደረገው የጦር መሣሪያ ውድድር ሊታለፍ የማይገባ ተብሎ ተቀባይነትን አግኝቷል። መዋለ ሕጻናት እና ትምህርት ቤቶችን ለመገንባት፣ በሂደት ላይ የሚገኘውን የጤና አገልግሎት ለመደገፍ፣ ረሃብን ለመዋጋት ወይም የጋራ መኖሪያ ምድራችንን ከጥፋት ለመጠበቅ እና ሥነ-ምህዳራዊ ሽግግርን ለማበረታታት ሊገኝ የማይችል ገንዘብ ለጦር መሣሪያ ግንባታ ዘወትር ቀጥሏል። የዲፕሎማሲ ጥረት በጠብ አጫሪ ጦረኞች ፊት ሰሚ ያጣ ይመስላል። እንደ ሰላም፣ ድርድር፣ እርቅ እና ውይይት የመሳሰሉ ቃላት በጥርጣሬ ይታያሉ። ከጥቂት የአገር መሪዎች ጥረት ባሻገር ከአውሮፓ የሚሰማ ድምጽ በጣም ጥቂት ነው።

ከሁሉ በላይ ለጦርነት አመክንዮ መረታት የሌለብን ጊዜ አሁን ነው። የቅዱስ ጴጥሮስ ተተኪ የሆኑት ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ሳይታክቱ የሰላም ስጦታን ከእግዚአብሔር ዘንድ መለመንን መቀጠል እንደሚገባ ዘወትር ያሳስባሉ። በአዲስ ትንቢታዊ እና ነጻ አመራር ሰላምን ለማምጣት እና በሰው ልጅ የወደፊት ዕጣ ፈንታ ላይ ኃላፊነትን መውሰድ የሚችል ደፋር አመራር እንዲኖር ያስፈልጋል። እራሳችንን ወደ ጥፋት ሊመሩን ለሚችሉ የጦረኞች አመክንዮ የማይገዙት ጠንካራ እና ቆራጥ ሰዎች በሙሉ ድምጻቸውን የሚያሰሙበት በሃላፊነት የተሞላ ቁርጠኝነት ሊኖራቸው ይገባል።

 

 

26 February 2024, 16:06