ፈልግ

የጀርመን ካቶሊክ ብጹዓን ጳጳሳት በሮም ሐዋርያዊ ጉብኝተ ባደረጉበት ወቅት የጀርመን ካቶሊክ ብጹዓን ጳጳሳት በሮም ሐዋርያዊ ጉብኝተ ባደረጉበት ወቅት  (Dt. Bischofskonferenz)

ቫቲካን ከጀርመን ካቶሊክ ጳጳሳት ጋር በሲኖዶሳዊ ጉዞ ላይ ውይይት ማካሄዷ ተገለጸ

የቫቲካን ባለስልጣናት ከጀርመን ካቶሊክ ብፁዓን ጳጳሳት ጉባኤ ተወካዮች ጋር በጀርመን የሲኖዶስ ሂደት ሠነዶች ላይ በተነሱት በርካታ ሥነ-መለኮታዊ ጥያቄዎች ላይ ተወያይተዋል። የቅድስት መንበር እና የጀርመን ካቶሊክ ብፁዓን ጳጳሳት ጉባኤ፥ በጀርመን በተካሄደው የሲኖዶሳዊ ጉዞ በማስመልከት በቫቲካን ባደረጉት ውይይት ማጠቃለያ ዓርብ መጋቢት 13/2016 ዓ. ም. የጋራ መግለጫ ሰጥተዋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

በመግለጫው መሠረት፥ የሮም ቤተ ክርስቲያን ከፍተኛ ጳጳሳዊ ጽሕፈት ቤቶች ተወካዮች ከበርካታ የጀርመን ካቶሊክ ጳጳሳት ጋር ተገናኝተው የተወያዩ ሲሆን፥ ይህም የጀርመን ካቶሊክ ብጹዓን ጳጳሳት አምና በኅዳር ወር በቫቲካን ሐዋርያዊ ጉብኝት ባደረጉበት ወቅት የጀመሩት ውይይት ቀጣይ እንደሆነ ታውቋል።

ስብሰባው ከዚህ ቀደም እንደ ጎርጎሮሳውያኑ በሐምሌ 26/2023 ዓ. ም. የተካሄደ ስብሰባ ተከታይ ሲሆን፥ በዚህ ስብሰባ ላይ አንዳንድ አዎንታዊ እና ገንቢ ሃሳቦች የቀረቡበት እንደ ነበር ይታወሳል። የስብሰባው ውይይት በጀርመን ካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን ሲኖዶሳዊነት ሠነድ ላይ በተነሱት አንዳንድ ግልጽ ሥነ-መለኮታዊ ጥያቄዎች ላይ ያተኮረ እንደ ነበረም ይታወሳል። በዚያም ወቅት ተወካዮቹ ልዩነቶችን በማስወግድ ወደ ስምምነት ለመድረስ የሚያስችል ቀጣይነት ያለውን ውይይት ለማካሄድ መስማማታቸው ይታወሳል።

በጋራ መግለጫው መሠረት፥ የጀርመን ካቶሊክ ጳጳሳት የጋራ ውይይቱ፥ ሁለተኛው የቫቲካን ጉባኤ የሕገ ቀኖና ድንጋጌዎች እና ውጤቶቹ በዓለማቀፉዊት ቤተ ክርስቲያን መሠረት በጀርመን ለምትገኝ ካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን ተጨባጭ የሆኑ ሲኖዶሳዊ ሥርዓቶችን ለማዘጋጀት እንደሚያገለግል አብራርተው፥ ከዚያም ለቅድስት መንበር ቀርቦ የሚጸድቅ መሆኑን ገልጸዋል።

ቀጣዩ ውይይት ዘንድሮ ከነሐሴ ወር በፊት ይካሄዳል

የሮም ቤተ ክርስቲያን ከፍተኛ ጳጳሳዊ ጽሕፈት ቤቶች ተወካዮች፥ ብፁዕ ካርዲናል ቪክቶር ፈርናንዴዝ፣ ካርዲናል ኩርት ኮክ፣ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ብፁዕ ካርዲናል ፒዬትሮ ፓሮሊን፣ ብፁዕ ካርዲናል ሮበርት ፕሬቮስት፣ ብፁዕ ካርዲናል አርቱር ሮሄ እና ሊቀ ጳጳስ አቡነ ፊሊፖ ያኖኔ እንደሆኑ ታውቋል።  

በጀርመን ካቶሊክ ብፁዓን ጳጳሳት ጉባኤ ተወካዮች፥ ብፁዕ አቡነ ጆርጅ ባትዚንግ፣ ብፁዕ አቡነ ስቴፋን አከርማን፣ ብፁዕ አቡነ ሚካኤል ገርበር፣ ብፁዕ አቡነ ፒተር ኮልግራፍ፣ ብፁዕ አቡነ በርትራም ሜየር እና የጀርመን ካቶሊክ ብፁዓን ጳጳሳት ጉባኤ ሊቀ መንበር እና በጳጳሳቱ ኮሚሽን የሥርዓተ አምልኮ፣ የመንፈሳዊ ጥሪ፣ የሐዋርያዊ አገልግሎቶች ሊቀ መንበር ብፁዕ አቡነ ፍራንዝ-ጆሴፍ ኦቨርቤክ የተገኙ ሲሆን፥ የቤተ ክህነት አገልግሎቶችን፣ ሐዋርያዊ እንክብካቤን፣ ዓለም አቀፍ ቤተ ክርስቲያንን እና የእምነት ጉዳዮች የሚከታተል ክፍል ዋና ጸሃፊ ዶ/ር ቢት ጊልስ እና የጀርመን ብጹዓን ጳጳሳት ጉባኤ ቃል አቀባይ ማቲያስ ኮፕ ተገኝተዋል።

23 March 2024, 16:09