ፈልግ

2024.01.10 croce dietro filo spinato - Kreuz hinter Stacheldraht  © Kirche in Not

ቅድስት መንበር፡- በዓለም አንድ ሦስተኛው የሃይማኖት ነፃነት መብት ተጥሷል ማለቷ ተገለጸ!

በተባበሩት መንግስታት ድርጅት እና ሌሎች አለም አቀፍ ድርጅቶች የቅድስት መንበር ቋሚ ታዛቢ 55ኛው የሰብአዊ መብቶች ጉባኤ ስብሰባ ላይ ባደረጉት ንግግር የሃይማኖት ነፃነትን ጨምሮ እየደረሰ ያለውን የሰብአዊ መብት ጥሰት ለመቅረፍ አዲስ አለም አቀፍ ጥረት እንዲደረግ አሳስበዋል።

የእዚህ ዝግጅት አቅራቢ መብራቱ ኃ/ጊዮርጊስ ቫቲካን

የአስተሳሰብ፣ የኅሊና እና የሃይማኖት ነፃነትን ጨምሮ የሰብዓዊ መብቶች ጥሰት በዓለም ዙሪያ አሳሳቢ ደረጃ ላይ መድረሱን የቅድስት መንበር የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት እና ሌሎች ዓለም አቀፍ ድርጅቶች ቋሚ ታዛቢ በጄኔቫ ረቡዕ የካቲት 20/2016 ዓ.ም ማስታወቃቸው ተገልጿል።

በአማኞች ላይ የሚደርሰው አድሎ እና ስደት እየጨመረ ነው።

በቅድስት መንበር ሥር የሚተዳደረው እና በዓለም ዙሪያ በአስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ የሚገኙ አብያተ ክርስቲያናትን ከሚደግፈው ጳጳሳዊ ድርጅት የተገኘውን መረጃ በመጥቀስ የሃይማኖት ነፃነት በዓለማችን አንድ ሶስተኛ በሚሆኑት አገሮች ውስጥ ሲጣስ 4.9 ቢሊዮን የሚጠጉ ሰዎችን ይጎዳል ሲሉ ተናግረዋል።

በኮንጎ ዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ የቀድሞ የቫቲካን እንድራሴ የነበሩ ሊቀ ጳጳስ ኤቶሬ ባልስትሬሮ ስለ ጉዳዩ ሲናገሩ በተጨማሪም በአንዳንድ ምዕራባውያን አገሮች “‘መቻቻልና መደመር’ በሚል ሽፋን ሃይማኖታዊ መድሎና ሳንሱር ወይም ምርመራ እየተፈጸመ ነው” ሲሉ በምሬት ተናግረዋል።

“የጥላቻ ንግግርን ለመዋጋት የታለመው ሕግ ብዙውን ጊዜ የአስተሳሰብ፣ የሕሊና እና የሃይማኖት ነፃነት መብትን በመቃወም ወደ ሳንሱር እና ወደ ‘አስገዳጅ ንግግር’ ይመራል ሲሉ ተናግረዋል።

የሰውን ልጅ ክብር ለመጠበቅ ዓለም አቀፍ ትብብር

በስብሰባው ላይ የተወያየውን አጠቃላይ ርዕሰ ጉዳይ በተመለከተ ሊቀ ጳጳስ ባሌስትሬሮ እንደተናገሩት ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ዋልታ ረገጥ በሆነው ዓለም ውስጥ ያሉትን ወቅታዊ ፈተናዎች ለመፍታት “ይበልጥ ውጤታማ” ዓለም አቀፍ ትብብርን ለመከተል “በተለይም መሰረታዊ የሚባሉት እና እ.አ.አ በ1948 ዓ.ም የተደነገገውን መሰረታዊ ሰብዓዊ መብቶችን አክብሮት ለማጠናከር በአለም አቀፍ የሰብአዊ መብቶች ድንጋጌ (UDHR) እንደተገለጸው ትኩረቱ የሰው ልጅ ክብር መሆን አለበት፣ ይህም የሰላም መሰረት ነው ሲሉ ተናግረዋል።

የባለብዙ ወገን ዲፕሎማሲውን ለማሻሻል "በሰው ልጅ ክብር ላይ የተመሰረቱ እሴቶችን ማስከበር" አስፈላጊ ነው ብለዋል። ይህ በተራው “የተፈጥሮአችን የጋራ ራዕይ እንደገና መገንባት” ይጠይቃል።

"ጥሩ የሆነውን ከእውነት እና በሰው ተፈጥሮ ውስጥ ስር የሰደዱትን መለየት አንችልም" ሲሉም ሊቀ ጳጳሱ ተናግረዋል።

ሰው ሰራሽ አብርዖት እና መሰረታዊ የሰብአዊ መብቶች ጥበቃ

በተባበሩት መንግስታት ድርጅት እና ሌሎች አለም አቀፍ ድርጅቶች የቅድስት መንበር ቋሚ ታዛቢ ሊቀ ጳጳስ ኤቶሬ ባልስትሬሮ በመቀጠል የሰው ልጅ ክብር በሰው ሰራሽ አብርዖት (AI) ልማት እና አጠቃቀም ላይ መሪ መርህ መሆን አለበት ብለዋል።

"በዚህ መስክ ያሉ እድገቶች መሰረታዊ የሰብአዊ መብቶችን ሊያከብሩ እና ሰብአዊ አቅማችንን መወዳደር ሳይሆን ማገልገል አለባቸው" ብለዋል። "የሰው ሰራሽ አብርዖት እድገት ስኬታማ ሊባል የሚችለው በኃላፊነት ስሜት ከተንቀሳቀስን እና መሰረታዊ የሰው ልጅ እሴቶችን ከጠበቅን ብቻ ነው" ያሉ ሲሆን "የሰው ልጅ ሰብዓዊ መብት ማክበር የሰውን ልጅ ማንነት ለመለየት ወይም ወደ አልጎሪዝም (ስልተ-ቀመር) ወይም የመረጃ ስብስብ ለመቀነስ የሚደረገውን ማንኛውንም አይነት ሙከራ ውድቅ ማድረጋችን እና የተራቀቁ ስርዓቶች የሰውን ልጅ እጣ ፈንታ በራስ ገዝ እንዲወስኑ አንፈቅድም” በማለት ተናግሯል።

ሊቀ ጳጳስ ባሌስትሬሮ በመቀጠል ዛሬ የሚያጋጥሙንን አብዛኞቹ ፈተናዎች “የሰው ልጅ ሰብዓዊ መብት ካለመከበር እና እርስ በርስ መተሳሰራችንን ካለማወቅ የመነጨ ነው” ብለዋል።

"አዲስ መብቶች" የሰውን ክብር እና ወንድማማችነት አደጋ ላይ ይጥላሉ

የእያንዳንዱን ሰው ህይወት ቅድስና የሚጠራጠሩ እና "ለሰው ልጅ በእውነት ከሚጠቅመው ጋር ሁልጊዜ የማይጣጣሙ "አዲስ መብቶች" የሚባሉትን ለማስተዋወቅ የተደረጉ ሙከራዎችን አስታውሰዋል።

እነዚህ “አዲስ መብቶች”፣ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ እንዳሉት ከሆነ የሰውን ልጅ ክብር የሚጎዳ “የርዕዮተ ዓለም ቅኝ ግዛት” ብለው የሰየሙትን፣ እንዲሁም የሰው ልጅ ወንድማማችነትን የሚጎዳ፣ “በባህል፣ በማህበረሰቦች እና በግዛቶች መካከል መከፋፈልን ከመፍጠር ይልቅ፣ አንድነትን እና ሰላምን መፍጠር" አስፈላጊ ነው ሲሉ ሊቀ ጳጳስ ባልስትሬሮ ተናግረዋል።

"የእኛ ማህበረሰቦች "ሁለንተናዊ ወንድማማችነት እና የእያንዳንዱን ሰው ህይወት፣ የእያንዳንዱ ወንድ እና ሴት፣ድሆች፣ አዛውንቶች፣ ህጻናት፣ አቅመ ደካሞች፣ ያልተወለዱ እና በማሕጸን ውስጥ የሚገኙ ሕፃናት ቅድስና መከበር ትክክለኛ ግንዛቤን መሰረት በማድረግ መቀጠል አለባቸው። ሥራ የሌላቸው፣ የተረሱ፣ እንደ ስታስቲክስ አካል ብቻ ስለሚቆጠሩ ሊጣሉ እንደሚችሉ የሚታሰቡ'' ሰዎች ሰብዓዊ ክብር ሊከበር ይገባዋል ማለታቸው ተገልጿል።

በተባበሩት መንግስታት ድርጅት እና ሌሎች አለም አቀፍ ድርጅቶች የቅድስት መንበር ቋሚ ታዛቢ ሊቀ ጳጳስ ኤቶሬ ባልስትሬሮ አሳባቸውን ሲደመድሙ "በአሁኑ ዓለም የሰብአዊ መብቶች ሙሉ በሙሉ እውን እንዲሆኑ ሁለንተናዊ ወንድማማችነት አስፈላጊ ሁኔታ ነው" ያሉ ሲሆን "ሁላችንም የተገናኘን መሆናችንን ሳናውቅ ስንቀር ሁላችንም እንሰቃያለን" ካሉ በኋላ ንግግራቸውን ደምድመዋል።

01 March 2024, 11:45