ፈልግ

በስሪላንካ የረመዳን ጾም  በስሪላንካ የረመዳን ጾም   (AFP or licensors)

ቫቲካን የረመዳን ጾምን በማስመልከት ያወጣው መልዕክት የሰላም ጥረትን እንደሚያበረታታው ተገለጸ

በቫቲካን የሐይማኖት ተቋማት የጋራ ውይይት አስተባባሪ ጳጳሳዊ ጽሕፈት ቤት ዓመታዊ የረመዳን ጾም ወቅት መልዕክቱን ይፋ አድርጓል። ጽሕፈት ቤቱ በመልዕክቱ የሁሉም ሃይማኖቶች ተከታዮች የጥላቻ፣ የአመጽ እና የጦርነት እሳትን በማጥፋት በምትኩ የሰላም ጧፍ እንዲያበሩ አሳስቧል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

በዓለም ላይ በቁጥር እየጨመሩ የመጡት ግጭቶች ጳጳሳዊ ጽሕፈት ቤቱ በረመዳን እና ኢድ አልፈጥር ወቅት ለሙስሊም እህቶች እና ወንድሞች የሚያስተላልፈው ዓመታዊ መልዕክት “ሰላምን መገንባት” በሚል መሪ ሃሳብ ላይ እንዲያተኩር አድርጎታል።

"መቀራረብ እና ወዳጅነት" የሚለው የጳጳሳዊ ጽሕፈት ቤት መልዕክት ይፋ የሆነው ዓርብ መጋቢት 6/2016 ዓ. ም. ሲሆን፥ መልዕክቱ ክርስቲያኖችም ሆነ ሙስሊሞች የጦርነትን እሳትን በማጥፋት በምትኩ የሰላም ጧፍ እንዲያበሩ ጥሪ ያቀረበ እንደሆነ ተመልክቷል።

በዓለማችን ላይ የሚያስደነግጥ ግጭት መጨመሩን በማመልከት የጀመረው ጽሑፉ፥ ከወታደራዊ ውጊያ አንስቶ እስከ ትጥቅ ግጭቶች ድረስ መንግሥታትን፣ የተደራጁ ወንጀለኞችን፣ የታጠቁ ቡድኖች እና ሲቪሎችን የሚያሳትፍ እንደሆነ ገልጿል።

በጦር መሣሪያ ንግድ ላይ የተወሰደ ዕርምጃ ያመጣው ደስታ 

ሥነ-ምግባር የጎደላቸው የግጭት መንስኤዎች፣ ቀጣይነት ያለው የጦር መሣሪያ ምርት እና ግብይት እንደ ሆነ የገለጸው መልዕክቱ፥ ይህም በዘመናት የሰው ልጅ የበላይነት ፍላጎት፣ በጂኦ-ፖለቲካዊ ምኞቶች እና በኢኮኖሚያዊ ጥቅሞች የታጀበ እንደሆነ አስረድቷል።

በሚያስከትላቸው ውድመቶች በእጅጉ የሚሰቃዩ እንዳሉ የገለጸው መልዕክቱ፥ ከዚህ የሥነ ምግባር ብልሹነት እና በጦር መሣሪያ ንግድ በሚያገኙት ከፍተኛ ኢኮኖሚያዊ ትርፍ የሚደሰቱ መኖራቸውን ገልጿል። ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በአንድ ወቅት በመልዕክታቸው፥ “በወንድማችን ደም ውስጥ ቁራሽ እንጀራ መንከር” ሲሉ መናገራቸው መልዕክቱ ጠቅሷል።

በጦርነት ሁሉም ወገን ተሸናፊ ነው

መልዕክቱን በጋራ የፈረሙት በቫቲካን የሐይማኖት ተቋማት የጋራ ውይይት አስተባባሪ ጳጳሳዊ ጽሕፈት ቤት ፕሬዝደንት ብጹዕ ካርዲናል ሚገል አንገል ኣዩሶ እና ዋና ጸሐፊው ሞንሲኞር ኢንዱኒል ኮዲቱዋኩ በሌላ በኩል፥ “የሰላም እና የደኅንነት ፍላጎት በእያንዳንዱ በጎ ፈቃደኛ ሰው ነፍስ ውስጥ ሥር የሰደደ ነው” ሲሉ አጽንዖት ሰጥተዋል።

የመሠረተ ልማት እና የንብረት መውደም ሕይወትን ተስፋ ቢስ እና አስቸጋሪ እንደሚያደርገው ገልጸው፥ በጦርነት ምክንያት ለመፈናቀል እና ለመሰደድ የተገደዱትን አስጨናቂ ሁኔታ አጉልተው፥ “እያንዳንዱ ጦርነት ወንድማማችነት የሚጎዳ፣ ጥቅም የሌለው፣ ትርጉም የለሽ እና ጨለማ ነው" በማለት ገልጸው፥ “በጦርነት ሁሉም ወገን ተሸናፊ ነው” ሲሉ በማያሻማ መልኩ በድጋሚ ገልጸዋል።

ለሕይወት ክብር ለመስጠት ህሊና ሊኖር ይገባል

የሐይማኖት ተቋማት የጋራ ውይይት አስተባባሪ ጳጳሳዊ ጽሕፈት ቤት የረመዳን ጾምን በማስመልከት ባስተላለፈው መልዕክቱ፥ ሁሉም ሃይማኖቶች የሰው ልጅ ሕይወት ቅዱስ እንደሆነ ስለሚያምኑ ክብር እና ጥበቃ እንደሚገባው አስታውሷል። የሞት ቅጣትን የሚበይኑ ክልሎች ቁጥር ከዓመት ዓመት እየቀነሰ መምጣቱን ጳጳሳዊ ጽሕፈት ቤቱ በደስታ ተቀብሎ፥ “መሠረታዊ የሕይወት ስጦታ ክብርን መስጠት ጦርነትን ውድቅ አድርጎ ለሰላም ክብር መስጠት ይገባል ለሚለው አስተዋጽኦ ያደርጋል” ሲል አስገንዝቧል።

መልዕክቱ “የእያንዳንዱን ሰው ሕይወት ፍጹም ዋጋ ያለው እና ደህንነቱን እና መብቱን ለማስከበር ሕሊና ሊኖር ይገባል” በማለት ጥሪ አቅርቧል። ይህም መንገድ ጦርነትን ላለመቀበል እና ማንኛውንም ዓይነት ጦርነት ለመቃወም አስተዋፅኦ እንዳለው ገልጿል።

የጥላቻ እሳት ለማጥፋት መተባበር

መልዕክቱ ሁሉን ቻይ የሆነውን የሰላም አምላክ የሰላም ምንጭ አድርገን እንድንመለከተው በማሳሰብ፥ ሰላም መለኮታዊ ስጦታ ቢሆንም የሰው ልጅ ጥረት ፍሬ እንደሆነ በመግለጽ ሊመሠረት እና ሊጠበቅ እንደሚገባ አሳስቧል።

መልዕክቱ በማከልም፥ “የጥላቻ፣ የአመጽ እና የጦርነት እሳትን በማጥፋት የሰላም ጧፍ በማብራት በሰብዓዊና በሃይማኖታዊ ባህሎቻችን ውስጥ ያሉትን የሰላም እሴቶችን በመያዝ በጋራ እንረባረብ” ሲል አጽንዖት ሰጥቷል።

በቫቲካን የሐይማኖት ተቋማት የጋራ ውይይት አስተባባሪ ጳጳሳዊ ጽሕፈት ቤት በመጨረሻም፥ “የረመዳን ጾም፣ የኢድ አል ፊጥር በዓል እና ሌሎች መልካም ተግባራት፥ የሰላም፣ የተስፋ እና የደስታ ፍሬዎችን ያስገኝላችሁ!” በማለት መልዕክቱን ደምድሟል።

 

18 March 2024, 16:45