ፈልግ

በዮርዳኖስ የሚገኝ የኢየሱስ ክርስቶስ ጥምቀት ቤተ ክርስቲያን በዮርዳኖስ የሚገኝ የኢየሱስ ክርስቶስ ጥምቀት ቤተ ክርስቲያን 

አቡነ ጋላገር በዮርዳኖስ ንጉሥ አብዱላህ ዳግማዊን እና የጋዛ ስደተኞች የዕርዳታ ማዕከልን ጎበኙ

በቫቲካን የመንግሥታት እና ዓለም አቀፍ ድርጅቶች ግንኙነት ጽሕፈት ቤት ዋና ጸሐፊ ሊቀ ጳጳስ አቡነ ፖል ሪቻርድ ጋላገር ለአራት ቀናት የሥራ ጉብኝት ወደ ዮርዳኖስ ተጉዘዋል። ሊቀ ጳጳስ አቡነ ፖል ጋላገር በጉብኝታቸው ወቅት በቅድስት አገር ከሚገኙ የአካባቢው አገራት ብጹዓን ጳጳሳት ጋር ሆነው የመስዋዕተ ቅዳሴ ጸሎትን ያሳርጋሉ። ከዮርዳኖሱ ንጉሥ አብዱላህ ዳግማዊ እና በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ለፍልስጤም ስደተኞች የዕርዳታ ማስተባበሪያ ኤጀንሲ ኮሚሽነር ጋርም ይገናኛሉ።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

ሊቀ ጳጳስ ፖል ሪቻርድ ጋላገር ዮርዳኖስን የሚጎበኙት ከመጋቢት 2-5/2016 ዓ. ም. ሲሆን በዮርዳኖስ እና በቅድስት መንበር መካከል ሙሉ ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት የተመሠረተበትን 30ኛ ዓመት በዓልን ያከብራሉ። ሐዋርያዊ ጽሕፈት ቤቱ ይፋ ባደረገው የጉብኝት መርሃ ግብር መሠረት ሊቀ ጳጳስ ፖል ሪቻርድ ጋላገር ከዮርዳኖስ ንጉሥ አብዱላህ ዳግማዊ ቢን አል ሁሴን ጋር ሰኞ ዕለት እንደሚገናኙ እና ከምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር እና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አቶ አያመን ሳላዲ ጋርም በዕለቱ እንደሚገናኙ ገልጿል።

ሊቀ ጳጳስ አቡነ ፖል ጋላገር ከዮርዳኖስ ወደ ጋዛ ሰርጥ የሚላክ የሰብዓዊ ዕርዳታ ማሰብሰቢያ ማዕከል የሆነው የሐሼማይት በጎ አድራጎት ድርጅትን ጎብኝተው በዚሁ ዕለት የዮርዳኖስ ካቶሊካዊ ማኅበረሰቦች በሚሰበሰቡበት በስዊፋ አማን የናዝሬት እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ቤተ ክርስቲያን ውስጥ ከአካባቢው አገራት ብጹዓን ጳጳሳት ጋር የመስዋዕተ ቅዳሴ ጸሎት እንደሚያሳርጉ ታውቋል።

ኢየሱስ የተጠመቀበት ሥፍራን ይጎበኛሉ

ሊቀ ጳጳስ ፖል ጋላገር ማክሰኞ መጋቢት 3/2016 ዓ. ም. በቅድስት አገር ከሚገኙ ባለስልጣናት ጋር ከተገናኙ በኋላ በማዳባ ከተማ የሚገኘውን እና በ“ካሪታስ” የዕርዳታ ድርጅት የሚመራውን የኢራቅ እና የሶርያ ስደተኞች ማዕከልን ይጎበኛሉ።

በጉብኝታቸው መርሃ ግብር መሠረት ረቡዕ መጋቢት 4/2016 ዓ. ም. የኢየሱስ ክርስቶስ የጥምቀት ሥፍራን፣ የናቦ ተራራ እና የመቃዎስ ቅዱሳን ሥፍራዎችን ከጎበኟቸው በኋላ ከአገሪቱ የቱሪዝም እና የጥንታዊ ቅርሶች ሚኒስትር ከሆኑት ከአቶ ማክራም ሙስጠፋ ኩይሲ ጋር ይገናኛሉ።

በቫቲካን የመንግሥታት እና ዓለም አቀፍ ድርጅቶች ግንኙነት ጽሕፈት ቤት ዋና ጸሐፊ ሊቀ ጳጳስ አቡነ ፖል ሪቻርድ ጋላገር በጉብኝታቸው የመጨረሻ ቀን ሐሙስ መጋቢት 5/2016 ዓ. ም. በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ለፍልስጤም ስደተኞች የዕርዳታ ማስተባበሪያ ኤጀንሲ ኮሚሽነር ከሆኑት ከአቶ ፊሊፕ ላዛሪኒ ጋር ይገናኛሉ።

 

 

 

12 March 2024, 16:00