ፈልግ

የብጹ ዓን ካርዲናሎች ጠቅላላ ጉባኤ የብጹ ዓን ካርዲናሎች ጠቅላላ ጉባኤ  (@VATICAN MEDIA)

አዲሱን ር. ሊ. ጳጳሳት ለመምረጥ በሚደረገው ጉባኤ ላይ የሚሳተፉ ሁሉም 133 ብጹአን ካርዲናሎች ወደ ሮም ደርሰዋል

ብጹአን ካርዲናሎቹ ሚያዚያ 29 ቀን 2017 ዓ. ም. የሚካሄደውና “ኮንክሌቭ” ተብሎ ለሚታወቀው የብጹዓን ካርዲናሎች ዝግ ጉባኤ ለመዘጋጀት የሚያስችላቸውን አሥረኛውን ጠቅላላ ጉባኤያቸውን ሰኞ ዕለት ያካሄዱ ሲሆን፥ በዚህም ቤተክርስቲያኒቱ አሁን ስለምትገኝበት ሁኔታ እና ባላቸው የወደፊት ተስፋ ላይ ሲያደርጉት የነበረውን ውይይት ቀጥለው እንደተወያዩ ተነግሯል።

 አቅራቢ ዘላለም ኃይሉ ፥ አዲስ አበባ

የቅድስት መንበር የጋዜጣዊ መግለጫ ጽህፈት ቤት ዳይሬክተር ማትዮ ብሩኒ ትናንት ለጋዜጠኞች በሰጡት መግለጫ በአሥረኛው ጠቅላላ ጉባኤ ላይ 132 መራጭ ካርዲናሎችን ጨምሮ 179 ብፁአን ካርዲናሎች መሳተፋቸውን ገልጸዋል።

ብጹአን ካርዲናሎቹ ከርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ የቀብር ሥነ-ሥርዓት በኋላ ለዘጠኝ ቀናት በሚቆይ ጠቅላላ ስብሰባ፣ አስተንትኖ እና በየዕለቱ መስዋዕተ ቅዳሴ ጸሎት ላይ እንደነበሩም ተመላክቷል።

የካርዲናሎች ዝግ ጉባኤ ላይ የሚሳተፉት 133 መራጭ ካርዲናሎች በአምስቱ አህጉራት ውስጥ ከሚገኙ 71 የተለያዩ ሀገራት የተውጣጡ ሲሆን፥ ሚያዚያ 29 ከሚጀመረው ጉባኤ ቀደም ብለው ሁሉም መራጭ ካርዲናሎች ሮም እንደሚገኙ ጠቁመዋል።

የብጹአን ካርዲናሎች ህብረት መሪ የሆኑት ብፁዕ ካርዲናል ጆቫኒ ባቲስታ ሬ ለጉባኤው እንደተናገሩት፥ ብፁዕ ካርዲናል ካሜር-ሌንጎ ኬቨን ቅዳሜ ከሰዓት በኋላ መራጭ ብጹአን ካርዲናሎቹ የሚያርፉበት ክፍል ምደባ ዕጣ ማውጣታቸውን ገልጸው፥ ሁሉም ተሳታፊዎች በአዲሱ እና በአሮጌው የካሳ ሳንታ ማርታ (የቅድስት ማርታ) የመኖሪያ ህንፃ ክፍሎች ውስጥ እንደሚያርፉ አብራርተዋል።

አቶ ብሩኒ እንዳመለከቱት፥ መራጭ ካርዲናሎቹ ካረፉበት የቅድስት ማርታ መኖሪያ ህንፃ እስከ የምርጫ ሥነ ስርዓቱ ወደ ሚካሄድበት ሲስቲን ጸሎት ቤት ከፍተኛ ጥበቃ በሚደረግበት መተላለፊያ መንገድ ከፈለጉ በእግር መጓዝ እንደሚችሉ ገልጸዋል።

ሰኞ ጠዋት በተካሄደው ጉባኤ ላይ አጠቃላይ ከተነሱት 26 ርዕሰ ጉዳዮች መካከል የቀኖና ሕግ እና የቫቲካን ከተማ ግዛት ሚና፣ የቤተክርስቲያኒቷ ሚስዮናዊ ተፈጥሮ፣ ድሆችን ለመከላከል እና ለመርዳት ካሪታስ ስላለው ሚና፣ ወንጌል በዛሬው ዓለም ውስጥ ለኃላፊነት ጥሪ ትልቅ ትርጉም እንዳለው ማሳያ በሆነው በሥነ ስርዓቱ ስፍራ ላይ ስለሚገኙ በርካታ ጋዜጠኞች ጉዳይ እና በፍርሀት ወቅት እንደ ተከፈተ የተስፋ በር የታየው በኮቪድ ወረርሽኝ ወቅት የተደረገው ጸሎት ያስታወሱ ሲሆን፥ አዲሱን ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት በተመለከተ፡ ብዙዎች ለሕዝቡ ቅርብ የሆነ እረኛ፣ የኅብረት እና አንድነት መግቢያ በር ብሎም ዓለም አቀፋዊ የሥርዓት ቀውስ ውስጥ ባለበት ዓለም ሁሉንም በክርስቶስ ደም አንድ ላይ የሚሰበስቡ እንደሚሆኑ ተስፋ እንደሚያደርጉ ተነስቷል።

ከዚህም በተጨማሪ ወንጌልን በማሰራጨት እና ፍጥረትን ለመንከባከብ በሚደረገው ጥረት ወቅት ስለሚያጋጥሙ ተግዳሮቶች እንዲሁም በጦርነት እና በግጭት የተጎዳችው ዓለምን የመንከባከብ ተግዳሮቶች የተብራሩ ሲሆን፥ በቤተ ክርስቲያኒቷ ውስጥ ስላለው የመከፋፈል ስጋት፣ በሲኖዶሳዊው አውድ ውስጥ ሴቶች ስላላቸው ሚና፣ ስለ መንፈሳዊ ጥሪዎች፣ እንዲሁም ስለ ቤተሰብ እና የህፃናት ትምህርት ጉዳይ ተነስተዋል።

በመጨረሻም ስለ ሁለተኛው የቫቲካን ጉባኤ ሰነዶች በተለይም ‘ዴይ ቨርቡም’ ተብሎ የሚጠራው ሰነድ ተነስቶ፥ የእግዚአብሔር ቃል እንዴት ለእግዚአብሔር ሕዝብ መፈሳዊ ምግብ እንደሚሆን ተመላክቷል።

አቶ ብሩኒ እንደተናገሩት በጠቅላላ ጉባኤው ወቅት ሃሳባቸው መግለጽ የሚፈልጉ ብጹአን ካርዲናሎች በሙሉ እድሉን እንዲያገኙ የተቻለውን ያክል ጥረት የተደረገ መሆኑን ጠቅሰዋል።

የምርጫ ሥነ ስርዓቱ የሚካሄድበት ሲስቲን ጸሎት ቤት እና በሁለቱ የካሳ ሳንታ ማርታ ማረፊያ ቤቶች ላይ ሲደረጉ የነበሩ የዝግጅት ሥራዎች የተጠናቀቁ በመሆኑ መራጭ ካርዲናሎች ከማክሰኞ ጥዋት ጀምሮ መግባት እንደሚችሉ ተገልጿል።

አቶ ብሩኒ በመጨረሻም እንዳስታወቁት፥ ‘ጀንዳርሜሪ’ ተብለው የሚታወቁት የቫቲካን የጥበቃ ሃይሎች ቀድመው ሥፍራውን ስለሚቆጣጠሩ ጋዜጠኞች እና የተለያዩ የሚዲያ ሰዎች የሲስቲን ቻፕልን መጎብኘት አይችሉም ያሉ ሲሆን፥ ሆኖም ግን የተዘጋጀውን የውስጥ ክፍል የሚያሳዩ ምስሎች እንደሚለቀቁ ገልጸዋል።

ሁሉም የምርጫ ሂደቶች የሚከናወኑት በቫቲካን ሐዋርያዊ ሕንጻ ውስጥ በሚገኝ በሲስቲን ጸሎት ቤት ብቻ ሲሆን፥ ምርጫው እስኪጠናቀቅ ድረስ ጸሎት ቤቱ ሙሉ በሙሉ ተዘግቶ ይቆያል ተብሏል።

በምርጫው ሂደት ወቅት መራጭ ካርዲናሎች እጅግ አስቸኳይ ካልሆነ ጉዳይ በስተቀር የስልክ ጥሪዎችን ጨምሮ የጽሑፍ መልዕክቶችን ወይም ደብዳቤዎችን ከመላላክ እና ከውይይት መቆጠብ እንዳለባቸው የተገለጸ ሲሆን፥ ከዚህም ባለፈ ምንም ዓይነት መልዕክት መላክም ሆነ መቀበል፣ ጋዜጦችን ወይም መጽሔቶችን መቀበል፣ የሬዲዮ ወይም የቴሌቪዥን ስርጭቶችን መከታተል አይፈቀድላቸውም ተብሏል።

የመራጭ ካርዲናሎች ዝግ ጉባኤ ሚያዝያ 29 ቀን 2017 ዓ. ም. ከጠዋቱ አራት ሰዓት ተኩል ላይ በቅዱስ ጳውሎስ ጸሎት ቤት በሚቀርብ የጸሎት ሥነ-ሥርዓት በይፋ የሚጀመር ሲሆን፥ ከጸሎት ሥነ-ሥርዓቱ በኋላ መራጭ ካርዲናሎች በጋራ ወደ ሲስቲን ጸሎት ቤት ከማምራታቸው በፊት ወደ ቅዱሳን ዘንድ የሚቀርብ ጸሎት “ሊታኒ” በኅብረት እንደሚደግሙም ጭምር ተገልጿል።
 

06 May 2025, 16:30