ፈልግ

የር. ሊ. ጳ ምርጫ አስፈጻሚዎች የምርጫውን ምስጢራዊነት ለመጠበቅ ቃለ መሐላ ፈጸሙ

የመራጭ ካርዲናሎች ዝግ ጉባኤ አስፈጻሚዎች የርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ምርጫ ምስጢራዊነት ለመጠበቅ በቅዱስ ጳውሎስ ጸሎት ቤት ቃለ መሐላቸውን ፈጽመዋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

ረቡዕ ሚያዝያ 29/2017 ዓ. ም. በሚጀምረው የርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ምርጫ ወቅት የሂደቱን ትክክለኛነት የሚያረጋግጡ የምርጫ አስተባባሪዎች ቃለ መሃላ ፈጽመዋል።

የርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ምርጫ አስፈጻሚ አባላት በቅዱስ ጳውሎስ ጸሎት ቤት ውስጥ ሰኞ ሚያዝያ 27/2017 ዓ. ም. ከቀኑ በአሥራ አንድ ሰዓት ተኩል ላይ ቃለ መሐላ የፈጸሙት የቀድሞው ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ቅዱስ ዮሐንስ ጳውሎስ ዳግማዊ፥ “መላው የእግዚአብሔር መንጋ” በማለት እንደ ጎርጎሮሳውያኑ በየካቲት 22/1996 ዓ. ም. በደነገጉት ሕግ መሠረት ነው።

በቅድስት የሮም ቤተ ክርስቲያን የንብረት እና የፋይናንስ አስተዳዳርሪ በሆኑት በብጹዕ ካርዲናል ኬቨን ጆሴፍ ፋሬል ፊት ቀሳውስት እና ምእመናን የፈጸሙት ቃለ መሐላ በሦስቱ ረዳት ካርዲናሎች ተቀባይነትን አግኝቷል።

የርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ምርጫ አስተባባሪዎች ቡድን፥ የብፁዓን ካርዲናሎች ኅብረት ጸሐፊን፣ ጳጳሳዊ የሥርዓተ አምልኮ ዝግጅት አስተባባሪ፣ ሰባት ጳጳሳዊ የሥርዓተ አምልኮ ሊቃውንት፣ የካርዲናሎች ዝግ ጉባኤን እንዲያግዙ በመሪ ካርዲናል የመረጡት የቤተ ክህነት አባላት፣ የመንፈሳዊ አልባሳት እና ቁሳቁስ ክፍል እንዲያተባብሩ የተመደቡ ሁለት የቅዱስ አጎስጢኖስ ማኅበር ገዳማውያን፣ በኑዛዜ መቀበያ ቦታ ላይ የሚሆኑ የልዩ ልዩ ቋንቋ ተናጋሪዎች ሃይማኖታዊ፣ የሕክምና ዶክተሮች እና ነርሶች፣ የጳጳሳዊ ሕንጻዎች ፎቅ መውጫ አገልግሎት ሠራተኞች፣ የጽዳት ሠራተኞች፣ የገበታ ቤት ሠራተኞች፣ መራጭ ካርዲናሎችን ከቅድስት ማርታ ጸሎት ቤት ወደ ሐዋርያዊ ሕንጻዎች የሚያደርሱ የትራንስፖርት አገልግሎት ሰጭዎች፣ በቫቲካን አስተዳደራዊ ክልል የጸጥታ አስከባሪ ዋና አዛዥ፣ ከአንዳንድ የሥራ ተባባሪዎቻቸው ጋር በመሆን በሲስቲን ጸሎት ቤት አቅራቢያ ያለውን የደህንነት ሁኔታ እንዲከታተሉት የተሰየሙት የስዊስ ዘብ ጠባቂዎች በምርጫ አስተባባሪዎች ቡድን ውስጥ የሚገኙ ናቸው።

በሮም ቤተ ክርስቲያን የንብረት እና የፋይናንስ አስተዳዳሪ የሆኑት ብፁዕ ካርዲናል ኬቨን ጆሴፍ ፋሬል ስለ ቃለ መሐላው አስፈላጊነት መመሪያ ከተሰጡ በኋላ እያንዳንዱ የምርጫ አስተባባሪ አባል በብፁዕነታቸው የቀረበውን ሐዋርያዊ ሕግ በቃል እና በፊርማ ሲያረጋግጡ ሁለት የሐዋርያዊ ፍርድ ቤት አባላት ምስክር ሆነዋል።

ቃለ መሐላው የርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ምርጫን በተመለከተ በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ የሚደረጉ ጉዳዮችን በተመለከተ ፍጹም ምስጢራዊነትን ለመጠበቅ ቃል መግባትን ያካትታል። በሐዋርያዊ መንበር በጸደቀው የወንጀለኛ መቅጫ ሕግ መሠረት የድምጽ እና የቪዲዮ መቅረጫ መሣሪያዎች በምርጫ አካባቢ መያዝን ይከለክላል።

ይህ ሥነ-ሥርዓት ሁሉም ረዳት የምርጫ አስተባባሪዎች የምርጫውን ሂደት ምስጢራዊነት እንዲጠብቁ ለማድረግ እና የርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ምርጫ ቅድስናን ለማስከበር ቤተ ክርስቲያን ቁርጠኝነት መሆኗን የሚያመለክት እንደሆነ ታውቋል።

 

 

 

 

 

06 May 2025, 16:38