ፈልግ

የቅድስት መንበር ዋና ጸሐፊ ብፁዕ ካርዲናል ፒዬትሮ ፓሮሊን የቅድስት መንበር ዋና ጸሐፊ ብፁዕ ካርዲናል ፒዬትሮ ፓሮሊን   (ANSA)

የቅድስት መንበር እና የቡሩንዲ ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት ስልሳ ዓመታትን ማስቆጠሩ ተነገረ

የቅድስት መንበር ዋና ጸሐፊ ብፁዕ ካርዲናል ፒዬትሮ ፓሮሊን በቅድስት መንበር እና የምሥራቅ አፍሪካ አገር ቡሩንዲ መካከል ላለፉት 60 ዓመታት የቆየውን ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት አስመልክቶ በተዘጋጀው በዓል ላይ ለመገኘት ወደ ቡሩንዲ ተጉዘዋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

ብፁዕ ካርዲናል ፒዬትሮ ፓሮሊን ወደ ቡሩንዲ የተጓዙት በአገሪቱ ከምትገኝ ካቶሊካዊ ቤተ ክርስቲያን እና በቡሩንዲ መንግሥት በቀረበላቸው ግብዣ ሲሆን፥ ብፁዕነታቸው በአገሪቱ ሐዋርያዊ ጉብኝት የሚያደርጉት ከማክሰኞ ነሐሴ 6-12/2017 ዓ. ም. ድረስ እንደሆነ ታውቋል።

የሐዋርያዊ ጉብኝታቸው ምክንያት በቡሩንዲ እና በቅድስት መንበር መካከል የተደረገ የ60 ዓመታት ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት የኢዮቤልዩ ክብረ በዓል መዝጊያ እና እንደ ጎርጎሮሳውያኑ በ2003 ዓ. ም. በቡሩንዲ ለተገደሉት የቀድሞው የቅድስት መንበር ሐዋርያዊ እንደራሴ ሊቀ ጳጳስ አቡነ ሚካኤል አይዳን ኮርትኒ መታሰቢያነት ለሚታነጽ የጤና ጣቢያ የመሠረት ድንጋይ ለማስቀመጥ እንደሆነ ታውቋል።

በወቅት በእርስ በርስ ጦርነት እየተናጠች በነበረች ቡሩንዲ ውስጥ የቅድስት መንበር እንደራሴ ሆነው እንዲያገለግሉ በቀድሞው ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ቅዱስ ዮሐንስ ጳውሎስ ዳግማዊ እንደ ጎርጎሮሳውያን በ 2000 ዓ. ም. የተሾሙት ሊቀ ጳጳስ አቡነ ኮርትኒ፥ በቡሩንዲ መንግሥት እና በሁቱ አማፂያን መካከል እንደ ጎርጎሮሳውያኑ በኅዳር ወር 2003 ዓ. ም. በተደረሰው ስምምነት ላይ ግንባር ቀደም ሚና ተጫውተዋል።

በኩባ በሚገኘው ሐዋርያዊ እንደ ራሴ ውስጥ ሲያገለግሉ የቆዩት አየርላንዳዊው ሊቀ ጳጳስ አቡነ ኮርትኒ፥ በአገሪቱ ውስጥ ሰላም በቅርቡ እንደሚመጣ በማመን በመዲናዋ ቡጁምቡራ ውስጥ ለመቆየት ጠይቀው እንደ ነበር ይታወሳል።

ከቡሩንዲ መዲና ቡጁምቡራ ብዙም ሳይርቅ ሲጓዙ በነበሩበት መኪና ላይ ጥቃት ሲደርስበት የተገደሉት ብቸኛው ሰው ሊቀ ጳጳስ አቡነ ኮርትኒ ሲሆኑ፥ በተወለዱት 58 ዓመታቸው እንደ ጎርጎሮሳውያኑ በታኅሳስ 29’2003 በሆስፒታል ውስጥ ሕይወታቸው ማለፉ ይታወሳል።

ከሞቱ ከሃያ ዓመታት በኋላ ማለትም እንደ ጎርጎሮሳውያኑ በ2023 ዓ. ም. ሊቀ ጳጳስ አቡነ ፖል ሪቻርድ ጋላገር በቫቲካን ውስጥ በሚገኘው የአየርላንድ ጸሎት ቤተ ውስጥ የመታሰቢያ መስዋዕተ ቅዳሴን ማሳረጋቸው ይታወሳል።

ዛሬ የቡሩንዲ ሕዝብ ብጹዕ ካርዲናል ፒየትሮ ፓሮሊን በተገኙበት እና ግድያው በተፈፀመበት ቦታ ላይ የሚገነባ ማዕከል የመሠረት ድንጋይ በማስቀመጥ ሊቀ ጳጳሱን ያስታውሳል። ፕሮጀክቱ ባለፈው ዓመት በቡሩንዲ ፕሬዝዳንት ኢቫሪስቴ ንዳይሺሚዬ ይፋ የተደረገ ሲሆን፥ የመሠረት ድንጋዩ የሚቀመጥበት ቀን ነሐሴ 8/2017 ዓ. ም. እንደሚሆን ታውቋል። ወደ ቡሩንዲ የተጓዙት የቅድስት መንበር ዋና ጸሐፊ ብፁዕ ካርዲናል ፒዬትሮ ፓሮሊን፥ የመታሰቢያ ሐውልት ምረቃ እና የጤና ጣቢያው ሥራ የሚጀምርበትን ሥነ-ሥርዓት ይመራሉ።

የጉብኝታቸው መርሃ ግብር

የብጹዕ ካርዲናል ፒየትሮ ፓሮሊን የሐዋርያዊ ጉዞ ዝርዝር መርሃ-ግብር በቅድስት መንበር ጽሕፈት ቤት @TerzaLoggia ድረ-ገጽ ላይ ታትሟል። ዛሬ ነሐሴ 7/2017 ዓ. ም. ብጹዕ ካርዲናል ፓሮሊን ከቡሩንዲ ብጹዓን ጳጳሳት ጉባኤ ጋር ሆነው መስዋዕተ ቅዳሴን አቅርበዋል።  ከአገሪቱ ፕሬዚዳንት ንዳሺሚዬ ጋር ተገናኝተው በአገሪቱ ብጹዓን ጳጳሳት ጉባኤ እና በመንግሥት መካከል ስምምነቶችን ተፈራርመዋል።

ብጹዕ ካርዲናል ፒየትሮ ፓሮሊን ዓርብ ነሐሴ 9/2017 ዓ. ም. የእመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ቤተ መቅደስ በሚገኝበት ሙገራ ተገኝተው መስዋዕተ ቅዳሴን እንደሚያቀርቡ ይጠበቃል። ብጹዕነታቸው ከዚያም በመቀጠል የፖለቲካ እና የአስተዳደር ዋና ከተማ የሆነችውን ጊቴጋን ይጎበኛሉ።

ብጹዕ ካርዲናል ፒየትሮ ፓሮሊን ቅዳሜ ነሐሴ 10/2017 ዓ. ም. መስዋዕተ ቅዳሴን ካቀረቡ በኋላ ከዘርዓ ክኅነት ትምህርት ቤት ተማሪዎች እንዲሁም ከገዳማውያን እና ገዳማውያት ዋና ዋና መሪዎች ጋር ይገናኛሉ። በኋላም የሊቀ ጳጳስ አቡነ ሚካኤል አይዳን ኮርትኒ የመታሰቢያ በዓል ሥነ-ሥርዓት በሐዋርያዊው እንደራሴ ጽሕፈት ቤት ውስጥ ከተከናወነ በኋላ ከዲፕሎማሲ አባላት ጋር እንደሚገናኙ ታውቋል።

ብፁዕ ካርዲናል ፓሮሊን በመጨረሻም እሑድ ነሐሴ 11/2017 ዓ. ም. በቡሩንዲ እና በቅድስት መንበር መካከል ለ60 ዓመታት የዘለቀውን ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት በማስመልከት የቀድሞው ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ቅዱስ ዮሐንስ ጳውሎስ ዳግማዊ እንደ ጎርጎሮሳውያኑ መስከረም 7/1990 ዓ. ም. መስዋዕተ ቅዳሴን ባሳረጉበት የእመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ቤተ መቅደስ ውስጥ የ60ኛ ዓመት የኢዮቤልዩ መዝጊያ መስዋዕተ ቅዳሴን እንደሚመሩ የሐዋርያዊ ጉብኝታቸው መርሃ-ግብር አመልክቷል።

 

13 Aug 2025, 17:03