ፈልግ

ሊቀ ጳጳስ አቡነ ሚሮስላው ዋክሆቭስኪ ሊቀ ጳጳስ አቡነ ሚሮስላው ዋክሆቭስኪ   (ks. Marek Weresa )

ኢራቅ ውስጥ የክርስቲያኖች ቁጥር እየቀነሰ ቢመጣም ቁልፍ ሚናቸውን መጠበቃቸው ተገለጸ

ሊቀ ጳጳስ አቡነ ሚሮስላው ዋክሆቭስኪ የአገልግሎት ጥሪቸውን፥ በአብርሃም ምድር ያላቸውን ተልዕኮን፣ሰብዓዊ ክብርን እና ሰላምን በማስፈን ረገድ ለቤተ ክርስቲያን የሚሰጡትን ሐዋርያዊ አገልግሎት በማስመልከት ከቫቲካን የዜና አገልግሎት ጋር ቃለ ምልልስ አድርገዋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ አሥራ አራተኛ፥ ሊቀ ጳጳስ አቡነ ሚሮስላው በኢራቅ የቅድስት መንበር ተወካይ በማድረግ መስከረም 8/2018 ዓ. ም. መሾማቸው ይታወሳል። ሊቀ ጳጳስ አቡነ ሚሮስላው ከቫቲካን መገናኛ ጋር ባደረጉት ቃለ ምልልስ የኃላፊነታቸውን ትርጉም በማስመልከት ማብራሪያ ሰጥተዋል።

በአሁኑ ወቅት በቅድስት መንበር የመንግሥታት እና ዓለም አቀፍ ድርጅቶች ግንኙነት ጽሕፈት ቤት ምክትል ጸሐፊ የሆኑት ሊቀ ጳጳስ አቡነ ሚሮስላው፥ ፖላንድ ውስጥ የትውልድ ሥፍራ የሆነች ማሱሪያን እና የልጅነት ጊዜ ጥሪያቸውን በቃለ ምልልሳቸው አስታውሰዋል። ጥልቅ የሆነ የብቃት ማነስ ስሜት በእግዚአብሔር ከመታመን አላገደኝም” ያሉት ሊቀ ጳጳስ አቡነ ሚሮስላው፥ “ከራሴ ውስን ችሎታዎች ይልቅ በእግዚአብሔር ጸጋ በመታመን ምላሽ ሰጥቻለሁ” ብለዋል።

በተሰቃየች አገር ውስጥ የምትገኝ የሰማዕታት ቤተ ክርስቲያን

በጠንካራ የትህትና መንፈስ የተነሳሱት ሊቀ ጳጳስ አቡነ ሚሮስላው፥ አዲሱን ተልዕኮአቸውን የእምነት እና የባሕል አገር በሆነች፥ የእግዚአብሔር ወዳጅ እና የሦስቱ ሃይማኖቶች የእምነት አባት የሆነው አብርሃም በተወለደባት አገር ለማበርከት መሄዳቸውን ገልጸው፥ በሐዋርያት የወንጌል ምስክርነት ወደተሠራች ጥንታዊት ቤተ ክርስቲያን ተልኬያለሁ” ሲሉ ተናግረዋል።

ኢራቅ ውስጥ ያለችው ቤተ ክርስቲያን እምነቷን ጠብቃ ያቆየችው እየለመለመች በነበረችበት ወቅት ብቻ ሳይሆን የሰማዕታት ቤተ ክርስቲያን በሆነችበት እና በስደት ውስጥ በምትገኝበት ጊዜ ጭምር ነው” ሲሉ አስገንዝበዋል። በአገሪቱ ያለው የክርስቲያኖች ቁጥር በከፍተኛ ደረጃ እየቀነሰ ቢመጣም ቁልፍ ሚና የሚጫወቱ መሆናቸውን ገልጸዋል። የአገሪቱ ምዕመናን በባለሥልጣናትም ሆነ በኅብረተሰቡ ዘንድ ከፍተኛ ግምት የሚሰጣቸው እንደሆኑ ገልጸው፥ ብዙውን ጊዜ በልዩነት፣ በክርክርና በግጭት የሚታመሰውን ማኅበረሰብ የሚያረጋጉ መሆናቸውን አስረድተዋል።

ሰላምን እና ሰብአዊ መብቶችን ማሳደግ

ሊቀ ጳጳስ አቡነ ሚሮስላው አዲሱን አገልግሎታቸውን እንደ ዲፕሎማሲያዊ ተግባር ብቻ ሳይሆን ከሁሉም በላይ እንደ መንፈሳዊ ተልዕኮ የሚመለከቱት መሆኑን ገልጸው፥ “እያንዳንዱ የቅድስት መንበር ተወካይ የርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሐዋርያዊ እንደራሴ ነው” ሲሉ አስረድተዋል። አገልግሎታቸውም “በአገሪቱ አብያተ ክርስቲያናት እና በሮም መካከል ያለውን ጥልቅ ግንኙነት ማገልገል ነው” ሲል አጽንዖት ሰጥተዋል።

በቅድስት መንበር ሐዋርያዊ እንደራሴ በኩል የኢራቅ ምዕመናን ከርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ጋር ያላቸው ቅርበት ሊሰማቸው እንደሚችል ገልጸው፥ እንዲሁም “ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት በሐዋርያዊ እንደራሴያቸው አማካይነት የምእመናኑ ደስታ እና ጭንቀት ሊያውቁት ይችላሉ” ሲሉ ተናግረዋል።

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ለምእመናን ቅርብ መሆን፣ ሰላምን እና ሰብዓዊ መብቶችን ማስተዋወቅ አስፈላጊ መሆኑን አበክረው አሳስበዋል። በዚህም ረገድ የቅድስት መንበር ሐዋርያዊ እንደራሴ ሚና ወሳኝ እንደሆነ እና በሲቪል ባለ ሥልጣናት በኩልም የርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ተወካይ ሆኖ የሚገለግል፥ የሰውን ልጅ ክብር፣ ዓለም አቀፍ ሰብዓዊ መብቶችን በማበረታታት ለሰላም የሚሠራ መሆኑን በኢራቅ የቅድስት መንበር ተወካይ ሆነው መስከረም 8/2018 ዓ. ም. የተሾሙት ሊቀ ጳጳስ አቡነ ሚሮስላው ዋክሆቭስኪ ከቫቲካን የዜና አገልግሎት ጋር ባደረጉት ቃለ ምልልስ ተናግረዋል።

22 Sep 2025, 17:11