ፈልግ

ለኢዮቤልዩ በዓላቸው በሮም የተሰሰቡ የትምህርተ ክርስቶስ መምህራን ለኢዮቤልዩ በዓላቸው በሮም የተሰሰቡ የትምህርተ ክርስቶስ መምህራን  

የትምህርተ ክርስቶስ መምህራን ኢዮቤልዩን ለማክበር የ 115 አገራት ነጋዲያን በሮም እንደሚገኙ ተገለጸ

ዓርብ መስከረም 16/2018 ዓ. ም. በተጀመረው የትምህርተ ክርስቶስ መምህራን ኢዮቤልዩ በዓል የሚሳተፉ ከሃያ ሺህ በላይ ምዕመናን መመዝገባቸው ታውቋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

ከመስከርም 16 – 18/2018 ዓ. ም. ድረስ በሚከበረው የትምህርተ ክርስቶስ መምህራን ኢዮቤልዩ በዓል ለመገኘት ከዓለም ዙሪያ የ 115 አገራት ነጋዲያን በሮም ተሰብስበዋል። ከመቶ በላይ ልዩ ልዩ አገራት የተውጣጡ ከሃያ ሺህ በላይ የትምህርተ ክርስቶስ መምህራን ከመላው ጣሊያን፣ ስፔን፣ ፖርቱጋል፣ ፈረንሳይ፣ ፖላንድ፣ ዩክሬን፣ አሜሪካ፣ አርጀንቲና፣ ብራዚል፣ ፓራጓይ፣ ሜክሲኮ፣ ፔሩ፣ ኮሎምቢያ፣ ፊሊፒንስ፣ ህንድ እና አውስትራሊያ መምጣታቸው ተነግሯል።

የኢዮቤልዩ በዓሉ የተዘጋጀው በየዕለቱ በትምህርተ ክርስቶስ መምህርነት ሥራ ለሚሳተፉት ሲሆን፥ሥራቸውም በሁሉም የዕድሜ ክልል እና የኑሮ ደረጃ ላይ ላሉ ሰዎች እምነትን ማስተማር እንደሆነ ታውቋል። የሚወክሉትም የመጡባቸውን ሀገረ ስብከቶች፣ ብሔራዊ የትምህርተ ክርስቶስ ጽሕፈት ቤቶችን እና የብጹዓን ጳጳሳት ጉባኤዎቻቸውን እንደሆነ ታውቋል።

የትምህርተ ክርስቶስ መምህራን ኢዮቤልዩ በዓል የተጀመረው ዓርብ መስከረም 16/2018 ዓ. ም. ጧት ሲሆን፥ በሥነ-ዓርዓቱ ላይ መምህራኑ ወደ ቅዱስ ጴጥሮስ ባዚሊካ ኡደት በማድረግ የባዚሊካውን ቅዱስ በር ተሻግረዋል። በዚሁ ዕለት ምሽት በቅዱስ ጴጥሮስ ባዚሊካ የተፈጸመውን የዋዜማ የጸሎት ሥነ-ሥርዓት የመሩት ሊቀ ጳጳስ አቡነ ሪኖ ፊዚኬላ፥ በቅድስት መንበር የስብከተ ወንጌል አገልግሎት ጳጳሳዊ ጽሕፈት ቤት ረዳት ሃላፊ እንደሆኑ ታውቋል።

ሊቀ ጳጳስ አቡነ ሪኖ ፊዚኬላ በዕለቱ ከሉቃ. 24:13-33 ተወስዶ በተነበበው እና ወደ ኤማሁስ የሚወስደውን መንገድ በተከተሉ ደቀ መዛሙርት ላይ በማተኮር ያደረጉትን ስብከት መሠረት በማድረግ  ከጣሊያን፣ ከሞዛምቢክ እና ከሜክሲኮ የመጡ ሦስት የትምህርተ ክርስቶስ መምህራን በአካባቢያቸው ማኅበረሰብ ውስጥ ያበረከቱትን የአገልግሎት ታሪካቸውን አካፍለዋል።

ቅዳሜ መስከረም 17/2018 ዓ. ም. የትምህርተ ክርስቶስ መምህራን በቅዱስ ጴጥሮስ አደባባይ ከርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ አሥራ አራተኛ ጋር ይገናኛሉ። ከቀትር በኋላ ከቀኑ ስምንት ሰዓት ላይ የትምህርተ ክርስቶስ መምህራ ቡድን በማዕከላዊ ሮም በሚገኙ ልዩ ልዩ ቤተ ክርስቲያናት ውስጥ በቋንቋቸው ከጳጳሶቻቸው ጋር ተሰብስበዋል። እነዚህ ስብሰባዎች በጣሊያንኛ፣ በእንግሊዘኛ፣ በፖርቱጋልኛ፣ በስፓኒሽ፣ በፈረንሳይኛ እና በፖላንድኛ መካሄዳቸው ታውቋል።

የትምህርተ ክርስቶስ መምህራን የኢዮቤልዩ በዓል ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ አሥራ አራተኛ እሑድ መስከረም 18/2018 ዓ. ም. ከረፋዱ አራት ሰዓት ላይ በቅዱስ ጴጥሮስ አደባባይ በሚመሩት መስዋዕተ ቅዳሴ የሚከበር ሲሆን፥ ቅዱስነታቸው በዚህ ሥነ-ሥርዓት ላይ 39 አዳዲስ መምህራንን የሚሾሙ ሲሆን፥

እያንዳንዱ እጩ መምህር ልዩ ተግባሩን የሚገልጽ ቅዱስ መስቀልን ከርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት እጅ እንደሚቀበል ታውቋል። አዲስ የሚሾሙት የትምህርተ ክርስቶስ መምህራን ከጣሊያን፣ ከስፔን፣ ከእንግሊዝ፣ ከፖርቱጋል፣ ከብራዚል፣ ከሜክሲኮ፣ ከህንድ፣ ከደቡብ ኮሪያ፣ ከኢስት ቲሞር፣ ከተባበሩት አረብ ኤሚሬቶች፣ ከፊሊፒንስ፣ ከአሜሪካ፣ ከሞዛምቢክ፣ ከብራዚል፣ ከፔሩ እና ከዶሚኒካን ሪፐብሊክ የመጡ መሆናቸው ተነግሯል።

 

27 Sep 2025, 13:51