ፈልግ

በዓለም ሰብዓዊ ወንድማማችነት ላይ ያተኮረ ውይይት በዓለም ሰብዓዊ ወንድማማችነት ላይ ያተኮረ ውይይት  

የጥላቻ ቃላትን በማስወገድ ዓለምን የጦር መሣሪያ ትጥቅ ማስፈታት የሚቻል መሆኑ ተገለጸ

“የጂ20 መረጃ” በሚል ርዕሥ በዓለም ሰብዓዊ ወንድማማችነት ላይ ያተኮረ ውይይት በሮም መካሄዱ ተገለጸ። በዓለም አቀፍ ሰብዓዊ ወንድማማችነት ዙሪያ የተካሄደው ሦስተኛ ዙር ውይይት ያተኮረው ግጭቶች እና ጦርነቶች ባሉበት ዓለም በግልጽነት እና በመረጃ ነፃነት ላይ እንደ ነበር ታውቋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

በሮም ከመስከረም 2-3/2018 ዓ. ም. ድረስ በተካሄደው የውይይት መድረክ ላይ ዓለም አቀፍ የመገናኛ፣ የመረጃ፣ የሚዲያ ዋና ሥራ አስፈፃሚዎች እና ተወካዮች የተገኙ ሲሆን፥ መድረኩን ያስተባበሩት የ “ፒያሳ ሳን ፒዬትሮ” መጽሔት ዳይሬክተር አባ ኤንዞ ፎርቱናቶ መሆናቸው ታውቋል።

ተሳታፊዎቹ ለውይይት ካቀረቧቸው ጭብጦች መካከል “በጦርነት እና በግጭት ወቅት ግልጽነት እና የመረጃ ነፃነት ሊኖር ይገባል” የሚሉት እንደሚገኙበት ታውቋል። ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ አሥራ አራተኛው እንደተናገሩት፥ የእውነታዎች እውነት የቃላት ጦርነትን ለማስቆም እና ዓለምን ትጥቅ ለማስፈታት አስፈላጊ እንደሆነ፥ ትክክለኛ ዜና እና መረጃ ሰላምን፣ የጋራ ውይይትን እና ወንድማማችነትን ለማሳደግ እንደሚጠቅም ተገልጿል። የውይይት መድረኩ ተሳታፊዎች በሚዲያው ዓለም የሚሠሩ አካላት ቁጥጥር በማይደረግበት የማኅበራዊ ሚዲያ በኩል የሚሰራጩ የጥላቻ እና የጥቃት ንግግሮችን በመከላከል ጥልቅ እና ትክክለኛ ዘገባን በማቅረብ ተአማኒነትን ለማስተዋወቅ ባላቸው ሃላፊነት ላይም ተወያይተዋል።

እውነት፣ ነፃነት እና ሰብዓዊ ክብር

የ “ፒያሳ ሳን ፒዬትሮ” መጽሔት ዳይሬክተር አባ ኤንዞ ፎርቱናቶ የውይይት መድረኩን ሲከፍቱ ባደረጉት ንግግር፥ የዘመናችንን ብዙሃን መገናኛዎችን የሚያገለግሉ ሦስት ነጥቦች እውነት፣ ነፃነት እና ሰብዓዊ ክብር መሆናቸውን አስረድተዋል። በልዩ ልዩ አገራት እውነት እንደሚዛባ እና ነፃነት እንደሚገፈፍ የገለጹት አባ ኤንዞ፥ በዚህ ምክንያት ጋዜጠኞች እውነትን ማገልገል እንደማይችሉ፣ ለስደት እንደሚዳረጉ ወይም እንደሚገደሉ አስረድተዋል።

አባ ኤንዞ በመቀጠልም፥ “ብዙ ታላላቅ ሰዎች ክብራቸውን እንደሚያጡ እና የጥቃት ኢላማ እንደሚሆኑ፣ ከጥላቻ የተነሳ ስም የማጥፋት ዘመቻ እንደሚካሄድባቸው እና ቃላት ከጦር መሣሪያ በላይ ሊያቆስሉ እንደሚችሉ አስረድተዋል። ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ አሥራ አራተኛ፥ “አማኞች ከመሆናችን በፊት ሰው እንድንሆን ተጠርተናል” ማለታቸውን ያስታወሱት አባ ኤንዞ ፎርቱናቶ፥ “እውነትን፣ ነፃነትን እና ሰብዓዊ ክብርን እንደ የጋራ ሃብት መጠበቅ አለብን” ብለው፥ ይህ ድርጅቶችን ወይም ጥቅሞቻቸውን መከላከል ሳይሆን ነገር ግን  የሥራችን ዋና አካል ነው” ሲሉ ገልጸዋል።

ተስፋ ሰጪ አመለካከቶችን ወደ እያንዳንዱ ትረካ መመለስ

ለመረጃ የሚደረግለትን ጥበቃ እውነተኛ እና ፍሬያማ ማድረግ ለወደፊት ተግባራችን አስፈላጊ ነው” ሲሉ አፅንዖት የሰጡት የቅድስት መንበር የመገናኛ ጽሕፈት ቤት ዋና ተጠሪ ዶ/ር ፓውሎ ሩፊኒ፥ “ሚዲያዎች ጥሩ ጋዜጠኝነትን ከመጥፎ ጋዜጠኝነት መለየት፣ በሃሜት እና በመረጃ ትንታኔ መካከል ያለውን ልዩነት መለየት፣ እውነትን በትዕግስት መፈለግ እና የሐሰት መረጃዎችን በፍጥነት በማሰራጨት መካከል ያለውን ልዩነት መለየት፣ እውነትን በጋራ ላይ በተመሠረተ የግንኙነት ሥርዓት እና በግድየለሽነት ላይ በተመሠረተ የመገናኛ ሥርዓት መካከል ያለውን ድንበር መጠበቅ ያስፈለገበ ለዚህ ነው” ሲሉ አስረድተዋል። ነፍስሔር ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ፥ “ቃላትን ትጥቅ ማስፈታት ማለት እጅ መስጠት ማለት አይደለም” ማለታቸውን ያስታወሱት ዶ/ር ሩፊኒ፥ ማኅበራዊ ግንኙነት ከሁሉም ጭፍን ጥላቻ፣ ከቂም፣ ከጥቃት እና ከአክራሪነት ነጻ መሆን አለበት” ሲሉ አሳስበዋል።

በተመሳሳይም ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ አሥራ አራተኛ፥ “የጥላቻ ቃላትን ካስወገድን ዓለም ከጦርነት ነጻ እንዲሆን በማገዝ ሰላማዊ ዓለም የመመሥረት ዕድልን እንደገና መገንዘብ እንችላለን” ማለታቸውን በመጥቀስ፥ “ይህ ማለት ሃሳብን የመግለጽ መብታችን አደጋ ላይ እንዳይወድቅ፣ ሰዎች በምርጫቸው ብቻ ተገድበው እንዲቆዩ በሚያደርግ የአመለካከት ውጥመድ ውስጥ በመውደቅ መጀመሪያው እና መጨረሻው በማይታወቅ የአልጎሪዝም ሃይልን ለመጋፈጥ ያግዛል” ብለዋል።

“ተግዳሮቱ አዲስ ሰብዓዊነትን መገንባት፣ የግንኙነት ብልሹነትን መቋቋም፣ የመረጃ መሠረትን መመለስ እና ለእያንዳንዱ መረጃ ተስፋ ማድረግ ነው” ብለዋል። የግንኙነት ደንቦችን በተመለከተ፥ “ነፃነት ከሌለ ለእውነት ምንም ዓይነት ዘዴ ሊኖር አይችልም” ሲል አፅንዖት ሰጥተው፥ ተጠቃሚዎችን ወደ ባለድርሻ አካላት ሚና መመለስ እና ጋዜጠኞች ጥራት ያለው መረጃን እንዲያዘጋጁ ማሰልጠን አለብን” ብለው፥ ማርቲን ሉተር ኪንግ “ጨለማን ማሸነፍ የሚችለው ብርሃን ብቻ ነው፤ ጥላቻን ማስወገድ የሚችለው ፍቅር ብቻ ነው” ማለቱን አስታውሰዋል።

ድምጽ ለሌላቸው ድምጽ መስጠት

 “ለጋራ ቃላት እና ተቀባይነት ላላቸው እውነታዎች የጋራ መሠረት መስጠት አስፈላጊ ነው” ያሉት የሌ ሞንዴ ዳይሬክተር ጄሮም ፌኖሊዮ፥ የመደራደር ችሎታ፣ ስምምነት ላይ መድረስ እና ሰላምን ወደ ቦታው መመለስ እንደሚገባ ተናግረዋል። መቀመጫውን በኬንያ ያደረገው ኔሽን ሚዲያ ግሩፕ ዳይሬክተር የሆኑት ጆ አጌዮ በበኩላቸው፣ በጦርነት አሰቃቂነት የተጎዱ በሚሊዮን የሚቆጠሩ የሰው ልጆች ታሪኮችን መናገር አስፈላጊ መሆኑን ጨምረው ገልጸዋል።

በጋዛ የተገደሉ ጋዜጠኞችን በክብር ማስታወስ

የአልጀዚራ ዋና ሥራ አስፈፃሚ ዲማ አል ካቲብ፥ ባለፉት ሁለት ዓመታት የጋዛን ጦርነት ሲዘግቡ የተገደሉት ጋዜጠኞችን በማስታወስ በስሜት ሲናገሩ፥ ሊሞቱ እንደሚችሉ በማወቅ ከወራት በፊት ቤተሰቦቿን ተሰናብታ የወጣችውን እንደ አናስ አል ሸሪፍ ያሉ የሥራ ባልደረቦቻቸውን ፎቶግፎች በማሳየት፥ አል ካቲብ እያለቀሱ “ከሁለት ዓመት ባነሰ ጊዜ ውስጥ በሁለተኛው የዓለም ጦርነት፣ በቬትናም እና በአፍጋኒስታን ከተገደሉት ጋዜጠኞች ጋር ሲወዳደር ብዙ ቁጥር ያላቸው ጋዜጠኞች መገደላቸውን በሐዘን ገልጸው፥ ሆኖም ይህን ዓይነት አረመኔያዊ ድርጊት በመቃወም “የሰው ልጅ አሁንም ለመነሳት እና ለመቃወም የሚያስችል ጥንካሬን ያገኛል” ሲሉ አክለዋል።

ነፃነትን ለመጠበቅ ታሪካዊ እውነቶችን ማክበር

የሮይተርስ ዜና ዋና አዘጋጅ አሌሳንድራ ጋሎኒ በበኩሏ፥ በዘመናችን ውስጥ እውነትን እና የእውነታዎች ወንድማማችነትን ያለማቋረጥ ጥቃት እየደረሰበት ይገኛል” ብላ፥ ነገር ግን ይህ ጉዳዩን ለወደፊቱ እና ለቀጣዩ ትውልድ የበለጠ አስፈላጊ ያደርገዋል ስትል ገልጻለች። የሲቢኤስ ዋና ሥራ አስፈፃሚ ቶም ሲብሮስኪ ጨምረዋል። “ፈተናው እጅግ ትልቅ ነው” የ “ANSA” የጣሊያን የዜና ማሰራጫ ዳይሬክተር ሉዊጂ ኮንቱ፥ የሕዝቡ አስተያየት ግራ የሚያጋባ መሆኑን አስጠንቅቀው፥ በዚህ ትርምስ ውስጥ ሁሉን ነገር መለየት አዳጋች እደሚሆን አስረድተው፥ “ከፕሮፓጋንዳ የተነሳ እውነትን የመናገር ችሎታን እናጣለን” ብለዋል። እንደ ሰው ሠራሽ አስተውሎት ያሉ መሣሪያዎች እውነታውን መጠቀም የሚችሉ ከሆነ እውቀት ያላቸው ዜጎችን የማሳወቅ እና የማስተማር ኃይልን እናጣለን ብለዋል። ተስፋ አስቆራጭ አስተሳሰብን መቃወም እንደሚገባ በማሳሰብ፥ “ከግል ሚዲያዎች ጎን ለጎን የዜና፣ የክርክሮች፣ የባህል እና የታሪክ ይዘቶች በማንነቶች እና የጋራ ልምዶች መካከል ግንዛቤን እና መከባበርን የሚያበረታቱ በቢሊዮኖች የሚቆጠሩ ሰዎች መኖራቸውን አስረድተዋል።

“አገልግሎት” የሚለውን ቃል ማስቀደም

የጣሊያን ሬዲዮ እና ቴሌቪዥን አገልግሎት “RAI” አባል እና የአውሮፓ ብሮድካስቲንግ ዩኒየን (ኢቢዩ) የቦርድ አባል የሆኑት ሲሞና አግነስ፥ በአገልግሎት ሃሳብ ዙሪያ በጋዜጠኝነት ሥራ አስፈላጊነት ላይ አጽንኦት ሰጥተው፥ ይህ ሲሆን የሰውን ልዩ እና የማይደገም ክብርን መገንዘብ እንደሚቻል አስረድተዋል። “በማህበረሰብ አገልግሎት ውስጥ መሆን ማለት እውነታውን በትክክል የሚተረጉሙ መሣሪያዎችን ማቅረብ፣ ብዝሃነትን መወከል፣ እና አቅመ ደካሞችን ከጉዳት በመጠበቅ ወንድማማችነትን በመገንባት እራሳችን የምንገነዘብበት እና የምንቀበልበት ማለት ነው” ብለዋል

በፔሩ ወጣቶችን የመድረስ ውጥኖች

በላቲን አሜሪካ አገር ፔሩ ውስጥ ወጣቶችን የመድረስ ልምድ ቀድሞውኑ መኖሩን የገለጹት በፔሩ የ “ኤል ኮሜርሲዮ” ዋና አዘጋጅ ዩዋን አውሬሊዮ አሬቫሎ፥ ከአምስት ዓመት በፊት በዩኒሴፍ የሕጻናት መርጃ ድርጅት የተጀመረውን ፕሮጀክት በማስታወስ፥ ከ3,000 የሚበልጡ ህጻናትን የሚረዱ ከ24ቱ የአገሪቱ ክልሎች የተወጣጡ 30 ጋዜጠኞች በማኅበረሰባቸው ውስጥ ያሉ ጉዳዮችን እንደሚዘግቡ አስረድተዋል። “ከልጆች፣ ከመምህራኖቻቸው እና ከወላጆቻቸው ጋር በሚገናኙበት ጊዜ የጋዜጠኝነት እሴቶችን እና ኃላፊነቶችን ከልጅነታቸው ጀምሮ እንዲማሩ የማድረግ ዘዴ ነው” ብለው፥  በተጨማሪም፣ “ቮዝ ዩኒቨርሲታሪያ” የተባለ ቦታ የዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች በፔሩ ታላላቅ ተግዳሮቶች ላይ አስተያየቶችን እንዲያካፍሉ እንደሚያስችላቸው ተናግረዋል።

የወደፊት ጊዜያችን በጋራ በምናደርጋቸው ምርጫዎች ይወሰናል

የራፕለር ዋና ሥራ አስፈጻሚ እና የ2021 የኖቤል የሰላም ሽልማት ተሸላሚ ፊሊፒናዊ-አሜሪካዊት ጋዜጠኛ ማርያ ሬሳ፥ “በመረጃው ዓለም ውስጥ እየኖርን ያለነው እውነታዎችን ጥቃት በሚደርስባቸው፣ እውነት እየተገደለ ባለበት እና እምነት እየጠፋ ባለበት ወቅት እንደሆነ ገልጻ፥ ይህም መግባባትን እና አስተዳደርን ወደማይቻል ደረጃ እንደሚያደርሰው ተናግራለች። እንደ ጎርጎሮሳውያን በ 2018 ዓ. ም. የተሰራውን ጥናት በመጥቀስ እንደተናገረችው፥ “ለስልተ-ቀመር ምስጋና ይግባውና ውሸት ከእውነታዎች በላይ በስድስት እጥፍ በፍጥነት ይሰራጫል” ብላለች። ይህ በሚሆንበት ወቅት አቅመ ቢሶች ሳንሆን ነገር ግን ለእውነት፣ ለሰብዓዊነት እና ለወደፊት ወደምንፈልገው ዋና ተልእኳችን በመመለስ የሕዝብን ጥቅም በማገልገል፣ የተግባር ማኅበረሰቦችን በመገንባት እና ቴክኖሎጂን ለሕዝብ ጥቅም አገልግሎት ማዋል እንደሚገባ ገልጻ፥ በመጨረሻም፥ “የወደፊቱ ጊዜ በኮድ የሚጻፈ ሳይሆን ሁላችን አንድ ላይ በምናደርጋቸው ምርጫዎች የሚወሰን ይሆናል” ስትል አስረድታለች።

ወንድማማችነትን መገንባት በሰው ልጅ ውስጥ ማደግ

በመጨረሻም በቫቲካን የቅዱስ ጴጥሮስ ባዚሊካ ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ ካርዲናል ማውሮ ጋምቤቲ፥ “ወንድማማችነትን ስንገነባ እና ራሳችንን እንደ ወንድማማቾች እና እህትማማቾች ስንገነዘብ በሰብዓዊነት ይበልጥ እያደግን እንሄዳለን” ብለው፥ “ወደ ዓለም የሚመጣ እያንዳንዱ ሰው ለዓለም የተሰጠ ስጦታ መሆኑን ማወቅ እንችላለ” በማለት ጠንካራ ማሳሰቢያቸውን ሰጥተዋል።

15 Sep 2025, 16:38