የቫቲካን የሕፃናት ሆስፒታል ከጦርነት ቀጠና የሚመጡ ታካሚዎችን እንደሚቀበል ተነገረ
የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን
እንክብካቤን ማድረግ እና ምርምር ሁለቱም በሕይወት አገልግሎት ውስጥ የተመሳሳይ ጥሪ መንገዶች እንደሆኑ ገልጸው፥ “ይህ ኃላፊነት ለምርምር አዎንታዊ ምላሽን መስጠት ብቻ ሳይሆን በተለይ በድህነት እና በጦርነት ከተጎዱ ሩቅ አካባቢዎች የሚመጡትን ለመቀበል ዘወትር መንገድ የሚከፍት ነው” ሲሉ አስረድተዋል።
የቅድስት መንበር ዋና ጸሐፊ ብጹዕ ካርዲናል ፒዬትሮ ፓሮሊን፥ በሮም የ “ባምቢኖ ጄሱ” የሕፃናት ሆስፒታል ተልዕኮን በዚህ መንገድ በአጭሩ የገለጹት ሆስፒታሉ እንደ ጎርጎሮሳውያኑ በ 1985 ዓ. ም. የምርምር፣ የሆስፒታል ውስጥ ሕክምና እና የጤና አጠባበቅ ሳይንስ ተቋም ሆኖ እውቅና የተሰጠበት 40ኛ ዓመት መታሰቢያን ለማክበር በተዘጋጀው ጉባኤ ላይ ተገኝተው ነው።
ብጹዕ ካርዲናል ፓሮሊን በንግግራቸው፥ “እነዚህ አርባ ዓመታት ሳይንስ እና ሰብዓዊነት ልጆችን እና ወላጆችን በምርምር እና እንክብካቤ፣ በቁርጠኝነት፣ በብልህነት እና ፍቅር ለማገልገል አብረው የተጓዙባቸው ዓመታት ናቸው” ሲሉ ገልጸዋል።
ሕሙማንን በርህራሄ መንከባከብ
ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ በቅርቡ “Dilexi te”፥ “እኔ እንደ ወደድሁህ” (ራእ. 3:9) በሚል ርዕሥ ያካፈሉትን ሐዋርያዊ ምክር ያስታወሱት ብጹዕ ካርዲናል ፒዬትሮ ፓሮሊን፥ የክርስቲያን ርህራሄ የታመሙትን እና የሚሰቃዩትን በመንከባከብ በጊዜ ሂደት የሚገለጽ መሆኑን አስታውሰው፥ የታመሙትን የመጎብኘት እና የመርዳት፣ ህመማቸውን የማስታገስ ባህል የበጎ አድራጎት ምልክት ብቻ ሳይሆን ቤተ ክርስቲያን በታመሙት ውስጥ የኢየሱስ ክርስቶስን የስቃይ አካል የመንካት ተልዕኮ ነው” ብለዋል።
“ባምቢኖ ጄሱ” ሆስፒታልን ጨምሮ በካቶሊክ ሆስፒታሎች ውስጥ እንክብካቤን የመቀጠል ባሕል ለሕመምተኞች ክርስቲያናዊ አለኝታነትን የመግለጽ ረቂቅ ሃሳብ ሳይሆን ተጨባጭ እርምጃ መሆኑን እንደሚያስታውሰን እና ይህ ተልዕኮ በምርምር የሚከናወን መሆኑን አስረተደዋል።
ብጹዕ ካርዲናል ፓሮሊን በዚህ ርዕሥ ላይ፥ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ ባለፈው ሰኔ በቫቲካን የሕዋ ምርምር ማዕከል የበጋ ወራት ትምህርታቸውን ለተከታተሉት ተማሪዎች ባደረጉት ንግግር፥ ዘመናዊ የሳይንስ ምርምር መሠረት የሆነውን እውቀት የማካፈል አስፈላጊነት አስመልክተው የተናገሩትን በመድገም፥ ታላላቅ ስኬቶች የሚመጡት “ከቡድን ሥራ፣ በሥነ-ምግባር ጥቅም ላይ ከዋለ ቴክኖሎጂ እና በዙሪያችን ያለውን የእውቀት ዱካዎች ለሌሎች ከማካፈል እንደሆነ አፅንዖት ሰጥተዋል።
የ “ባምቢኖ ጄሱ” ሆስፒታል ስኬቶች
የ “ባምቢኖ ጄሱ” የሕፃናት ሆስፒታል እንደ ጎርጎሮሳውያኑ በ1986 ዓ. ም. በጣሊያን ከተካሄደው የመጀመሪያው የሕፃናት የልብ ንቅለ ተከላ ጀምሮ እስከ 2018 ዓ. ም. ድረስ ለጠንካራ እጢዎች የሚደረግ የመጀመሪያው የጂን ሕክምና ድረስ በብዙ መስኮች በርካታ ዕድገቶችን ያሳየ እንደሆነ ታውቋል። ይህም ማክሰኞ ጥቅምት 18/2018 ዓ. ም. የተመረቀውን የጂን ሕክምና ላቦራቶሪ የሚያካትት እና ይህም በህፃናት “ኦንኮ-ሄማቶሎጂ” እና በበሽታ መከላከያ ምርምር እና ሕክምና ውስጥ ወደፊት የሚወስድ አስፈላጊ እርምጃ እንደሚሆን ተገልጿል።
ከስኬቶቹ ጀርባ ያሉት ሰዎች
ከእያንዳንዱ ስኬት በስተጀርባ “ሰዎች፣ ታሪኮች፣ አዲስ ተስፋን የሰነቁ ሕጻናት እና ቤተሰቦች፣ መፍትሄዎችን የሚያገኙ ተመራማሪዎች እና ዶክተሮች፣ የሕክምና መንገዶችን የለወጡ የዲሲፕሊን ቡድኖች መኖራቸውን ካርዲናል ፓሮሊን ተናግረው፥ በብቸኝነት ወይም በከባድ ክሊኒካዊ ሁኔታዎች ምክንያት በሚፈጠሩ ችግሮች ለማቃለል ወይም ጥያቄዎችን ለመመለስ ወደኋላ ሳይሉ ነገር ግን በድፍረት እና በጽናት እንዲጥሩ አሳስበዋል።
በቅፍርናሆም ኢየሱስ ክርስቶስን ይፈልግ የነበረ ሽባ ሰው በቤት ጣሪያ በኩል ወርዶ እንደተፈወሰ የሚገልጽ የወንጌል ክፍል ያሳታወሱት ብጹዕ ካርዲና ፓሮሊን፥ ይህ ታሪክ ለሳይንሳዊ ምርምር ምሳሌ ሊሆን እንደሚችል ገልጸው፥ ሳይንሳዊ ምርምር ምንም ተስፋ በሌለበት መላ መፈለግ እና ሌሎች ማግኘት ላልቻሉት መንገድ ማግኘት የሚቻልበት እንደሆነ አስረድተዋል።
ቅዱስ ፒየር ጆርጂዮ ፍራሳቲን መመልከት
ብጹዕ ካርዲናል ፓሮሊን የሕፃናት ሆስፒታሉ ከታማሚ ሕጻናት ጋር ለመሆን ላሳየው ትጋት አመስግነው፥ ሳይንስን እና በጎነትን፣ እምነትን እና ብልህነትን፣ ምርምርን እና እንክብካቤን አንድ ላይ በማጣመር እያንዳንዱ ሕጻን እና መከራ የደረሰበት ሰው፥ አቀባበል ሊደረግለት እና ፍቅር ሊሰጠው የሚገባው የኢየሱስ ክርስቶስ መልክ መሆኑን አንዲመሰክር አደራ ብለዋል።
የቅድስት መንበር ዋና ጸሐፊ ብጹዕ ካርዲናል ፒዬትሮ ፓሮሊን በመጨረሻም፥ ተቋሙን እና አባላቱን እንደ ጎርጎሮሳውያኑ በ1869 ዓ. ም. ሆስፒታሉን ከመሠረተው ከሳልቪያቲ ቤተሰብ ጋር ለተገናኘው የቱሪን ወጣት ቅዱስ ፒየር ጆርጆ ፍራሳቲ አደራ ሰጥተዋል።
ዘላቂነት እና ሁሉን አቀፍነት
የ “ባምቢኖ ጄሱ” ሆስፒታል ፕሬዝዳንት ቲዚያኖ ኦኔስቲ በበኩላቸው፥ ሆስፒታሉ የተጣለትን ሰፊ ኃላፊነት በማስታወስ፥ የአገልግሎት ዘላቂነትን በማስመልከት እንደተናገሩት፥ በሁሉ አቀፍነቱ የሮም ከተማን እና የአገሪቱን መሠረት ሳይዘነጋ እንክብካቤው ለሁሉም ሰው የሚሰጥ መሆኑን ተናግረዋል። ሆስፒታሉ በአሁኑ ጊዜ ለሦስት ወጣት ፍልስጤማውያን የሕክምና አገልግሎት እየሰጠ እንደሚገኝ እና በቅርብ ቀናት ውስጥ ሌሎች ሦስት ታካሚዎች ከፍልስጤም እንደሚመጡ ገልጸው፥ በአጠቃላይ በሆስፒታሉ ውስጥ እንክብካቤ የሚደረግላቸው 31 ታካሚዎች መኖራቸውን የሆስፒታሉ ፕሬዝዳንት አቶ ቲዚያኖ ኦኔስቲ ተናግረዋል።