የቫቲካን የገና ዛፍ ቅዱስ ጴጥሮስ አደባባይ መድረሱ ተነገረ
አቅራቢ ዘላለም ኃይሉ ፥ አዲስ አበባ
25 ሜትር ቁመት ያለው ቀይ ጥድ በአሁኑ ወቅት በቅዱስ ጴጥሮስ አደባባይ የቆመ ሲሆን፥ ዛፉ የመጣውም በጣሊያን ሰሜናዊ ክፍል ውስጥ በሚገኘው ቦልዛኖ አውራጃ ውስጥ ከሚገኘው ቫል ዲ ኡልቲሞ አካባቢ እንደሆነ እንዲሁም የላጉንዶ እና ቫል ዲ ኡልቲሞ ማዘጋጃ ቤቶች በስጦታ እንዳበረከቱት ተገልጿል።
የቦልዛኖ ግዛት በሐይቆች፣ በጫካዎች፣ በተራሮች እና በሜዳዎች በተሞላ ልዩ ውበቱ የሚታወቅ ሲሆን፥ ዛፉ በደን ጥበቃ አገልግሎት ጥልቅ ምርመራ ከተደረገበት በኋላ መመረጡ ተገልጿል።
እንደ ልማዱ መሰረት ከዋናው ዛፍ በተጨማሪ 40 ትናንሽ ዛፎች ወደ ቫቲካን መጥተው በተለያዩ የቅድስት መንበር ቢሮዎች እና ህንጻዎች እንዲቀመጡ የሚደረግ ሲሆን፥ ተጨማሪ እድሜ ጠገብ የሆኑ ዛፎች እንደ ተፈጥሯዊ እድሳት ሂደት አካል ሆነው ይመረጣሉ ተብሏል።
የቦልዛኖ-ብሬሳኖን ጳጳስ የሆኑት ብፁዕ አቡነ ኢቮ ሙሴር ‘የዛፉ መቆረጥ አክብሮት የጎደለው ተግባር ሳይሆን ጥንቃቄ የተሞላበት የደን አያያዝ ውጤት’ መሆኑን ገልጸው፥ ይህም አንዳንድ ዛፎችን ማስወገድ የጫካውን ጤና የሚያረጋግጥ እና እድገቱን የሚቆጣጠር ንቁ የእንክብካቤ ስልት አካል ነው ሲሉ አብራርተዋል።
ሁለቱ ከተሞች በሚገኙበት በደቡብ ታይሮል አካባቢ የደን መልሶ ማልማት ሥራ ከፕሮጀክትም በላይ ሆኖ የሚታይ ተግባር መሆኑን የገለጹት ጳጳሱ፥ “በእያንዳዱ የተቆረጠ ዛፍ ምትክ አዲስ የሚተከልበት፣ ጤናማና የማይበገር ደኖችን ለመጪው ትውልድ ለማስተላለፍ የሚያረጋግጥ ዘላቂ የደን አስተዳደር የማዕዘን ድንጋይ ነው” በማለት አስረድተዋል።
የዚህ አረንጓዴ እይታ አካል የገና ወቅት መገባደጃን ተከትሎ ተከትሎ ‘ዊልደር ናቱርፕሮዱክቴ’ በተሰኘ የኦስትሪያ ኩባንያ አማካኝነት አስፈላጊ የሆኑ ዘይቶች ከዛፉ ቅርንጫፎች ለማውጣት ዝግጅት መደረጉ የተገለጸ ሲሆን፥ የተቀረው እንጨት የአካባቢ ጥበቃን የመመሪያ መርሆችን በጠበቀ መልኩ ለሌላ አገልግሎት ለበጎ አድራጎት ድርጅት እንደሚለገስ ተገልጿል።
ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዮሐንስ ጳውሎስ ዳግማዊ እ.አ.አ. በ 1982 ዓ.ም. ከፖላንድ ገበሬ በስጦታ የተቀበሉትን የገና ዛፍ ሮም ድረስ ባስመጡበት ወቅት የተጀመረው የቫቲካን የገና ዛፍ ባህል አሁንም ድረስ እንደቀጠለ ይገለፃል።
ከዚያን ጊዜ ጀምሮ የገና ዛፍን ለርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳቱ ማቅረብ እንደ ክብር መግለጫ ሆኖ የሚታይ ሲሆን፥ ቫቲካን በየዓመቱ ከተለያዩ የአውሮፓ ሀገራት ወይም ክልል የተለገሰ ዛፍን ትቀበላለች።