ፈልግ

የዓለም አቀፏ ቤተ ክርስቲያን መረጃን የያዘ ዓመታዊ የድረ-ገጽ ላይ መጽሐፍ ይፋ መሆኑ ተነገረ

በዓለም ዙሪያ የሚገኙ የካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን ተቋማት ወቅታዊ መረጃን የያዘ የቅድስት መንበር ዓመታዊ የድረ-ገጽ ላይ መጽሐፍ በበይነ መረብ አማካይነት ይፋ ሆነ።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

በላቲን ሥርዓተ አምልኮ የቀን አቆጣጠር የጽንሰተ ማርያም ዓመታዊ በዓል ከተከበረበት ከሰኞ ኅዳር 29/2018 ዓ. ም. ጀምሮ ዲጂታል ይዘት ያለውን የቅድስት መንበር ዓመታዊ መጽሐፍ በአውታረ መረብ እና በሞባይል መተግበሪያዎች አማካይነት ማግኘት እንደሚቻል ተገልጿል።

አዲሱ ዓመታዊ የዲጂታል መጽሐፍ የቅድስት መንበር ከፍተኛ ጳጳሳዊ ጽሕፈት ቤቶችን ጨምሮ የሀገረ ስብከቶችን፣ የገዳማዊ ተቋማትን እና በየአገራቱ የሚገኙ የቅድስት መንበር እንደራሴዎች ጽሕፈት ቤቶች መረጃን ይፋ የሚያደርግ መሆኑ ተገልጿል።

ፕሮጀክቱን በጋራ በመሥራት በቅርቡ ለርዕሠ ሊቀ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ ያቀረቡት የቅድስት መንበር ጽሕፈት ቤት እና የቢተ ክርስቲያኒቱ መገናኛዎች ጽሕፈት ቤት እንደሆኑ ታውቋል።

በሥነ-ሥርዓቱ ላይ የቅድስት መንበር ጽሕፈት ቤት ምክትል ጸሐፊ ሊቀ ጳጳስ አቡነ ኤጅጋር ፔና ፓራ እና የቅድስት መንበር መገናኛዎች ዋና ጸሐፊ ሞንሲኞር ሉቺዮ አድሪያን ሩይዝ ሲሆኑ፥ አብረዋቸውም የሁለቱ ጽሕፈት ቤቶች ተወካዮች በተገኙበት ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ መተግበሪያውን ለመጀመሪያ ጊዜ በመክፈት አገልግሎት እንዲሰጥ አድርገውታል።

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ በመክፈቻው ላይ ባደረጉት ንግግር፥ “ይህ ሥራ በቤተ ክርስቲያን አገልግሎት ውስጥ ለሚገኙ በርካታ ሰዎች ትልቅ ጥቅም የሚሰጥ በመሆኑ አመሰግናለሁ” ብለው፥ አዘጋጆቹ በዚህ የአገልግሎት መንፈስ እንዲቀጥሉ በማበረታታት “በጥንቃቄ እና በትኩረት የተጠናቀቀው ይህ ሥራ ከጊዜ በኋላ የበለጠ የሚረዳ ይሆናል” ብለዋል።

የርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት የሕይወት ታሪክ ስብስቦችን የያዘውን ዓመታዊ መጽሐፍ ማዘጋጀት የተጀመረው በመካከለኛው ዘመን ሲሆን፥ በሃያኛው ክፍለ ዘመን አጋማሽ ላይ በዓለም ዙሪያ ስለ ካቶሊካዊት ቤተ ክርስቲያን ይፋዊ መረጃን ለሚፈልግ ለማንኛውም ሰው አስፈላጊ ማጣቀሻ ሆኖ እንዲቀርብ መደረጉ ይታወሳል።

ጥንታዊ የቅድስት መንበር መረጃዎችን ዛሬ በአውታረ መረብ አማካይነት ማግኘት የተቻለ ሲሆን፥ ይህም ዓለም አቀፋዊት ቤተ ክርስቲያን የመረጃ መሣሪያዎቿን ለማደስ እና ለማዘመን ትልቅ እርምጃ መውሰዷን የሚያሳይ እንደሆነ ተነግሯል።

የቅድስት መንበር ጽሕፈት ቤት መግለጫ እንዳስታወቀው፥ እርምጃው በማንኛውም የመገናኛ መሣሪያ አሳሽ ወይም መተግበሪያ አማካይነት የቤተ ክርስቲያኒቱን የመረጃ ቋት ማማከር እንዲቻል ማድረጉ ተገልጿል።

ዓመታዊ የዲጂታል መጽሐፉ ለተለያዩ በርካታ ተጠቃሚዎች የአገልግሎት መሣሪያ እንዲሆን የተነደፈ ሲሆን፥ በመጀመሪያ ደረጃ የቅድስት መንበር ከፍተኛ ጳጳሳዊ ጽሕፈት ቤቶች በየጊዜው በሚታደሱ መረጃዎች በመታገዝ ሥራቸውን ተፈጻሚ እንዲያደርጉ ለማስቻል የታሰበ እንደሆነ ተገልጿል።

ይህ በየዓመቱ ይፋ የሚሆን የዲጂታል መጽሐፍ የቅድስት መንበር እንደራሴ ጽሕፈት ቤቶች ለዲፕሎማሲያዊ እና ሐዋርያዊ ሥራቸው ግብዓት የሚሆኑ መረጃዎችን የሚሰጥ ሲሆን፥ እንዲሁም የጳጳሳት ጉባኤዎች በልዩ ልዩ አገራት ውስጥ በሚገኙ የቤተ ክርስቲያን እውነታዎች ላይ ያላቸውን ግንዛቤ እንዲያሰፉ የሚያስችላቸው እንደሚሆን ተገልጿል።

በዚህ መሠረት ገዳማዊ ተቋማት፣ ጳጳሳዊ ዩኒቨርሲቲዎች፣ የምርምር ማዕከላት እና ሌሎች የትምህርት ተቋማት ከቅድስት መንበር ኦፊሴላዊ ግንኙነቶች ጋር የተጣጣሙ መረጃዎችን ማግኘት የሚችሉ መሆናቸው ተነግሯል።

ዓመታዊውን የዲጂታል መጽሐፍ ጋዜጠኞች እና የቤተ ክርስቲያን የመገናኛ ባለሙያዎችም በማጣቀሻነት በመጠቀም የተረጋገጠ ይዘት ያለውን አስተማማኝ መረጃን ሊያገኙ እንደሚችሉ ተገልጿል።

ከቤተ ክርስቲያኒቱ የሚሰጡ አዳዲስ ሹመቶችን፣ የቢሮ ለውጦች እና በልዩ ልዩ መዋቅሮች ላይ የተደረጉ ማሻሻያዎችን በማስመልከት የሚቀርቡ መረጃዎችን ለማግኘት ተጠቃሚዎቹ እስከቀጣዩ አዲስ እትም መጠበቅ እንደሌለባቸው እና አዳዲስ መረጃዎችን በአጭር ጊዜ ውስጥ ከአውታረ መረብ ላይ ሊያገኙ እንደሚችሉ ተገልጿል።

“ሲስተሙ” በተጨማሪም የላቁ የፍለጋ ስልቶች ያሉት ሲሆን ይህም ተጠቃሚዎች መረጃዎችን በስም፣ በሀገረ ስብከት፣ በጽሕፈ ቤት እና ሚናቸው፣ በአገር ወይም ተቋማቱ የሚገኙባቸውን አካባቢዎች እንዲያጣሩ የሚያስችል እንደሆነ ታውቋል።

“የእርስ በርስ ግንኙነት እጅግ ፈጣን እና ዓለም አቀፋዊ በሆነበት በዚህ ዘመን ስለ ቤተ ክርስቲያን ሕይወት ፈጣን እና አስተማማኝ መረጃን መስጠት ቴክኖሎጂን ለቤተ ክርስቲያን ተልዕኮ አገልግሎት ማዋል ማለት ነው” ሲሉ ሊቀ ጳጳስ አቡነ ፔና ፓራ አፅንዖት ገልጸው፥ “ይህም ለካቶሊካዊ ማኅበረሰብ እና በዓለም ዙሪያ የቤተ ክርስቲያኒቱን እውነታ ማወቅ ለሚፈልጉ በሙሉ የትኩረት፣ የግልጽነት እና የኃላፊነት ምልክት ነው” ሲሉ አስረድተዋል።

የቅድስት መንበር መገናኛዎች ጽሕፈት ቤት እና በተለይም የቴክኖሎጂ ጽ/ቤቱ ለዲጂታል መሠረተ ልማት ቴክኒካዊ ልማት፣ የዲጂታል መዋቅርን ለመፍጠር እና በማዕከላዊ የቤተ ክርስቲያን “ስታቲስቲክስ” ጽ/ቤት የተዘጋጀውን መረጃ መደበኛ ለማድረግ የሚረዱ ሂደቶች በሙሉ ኃላፊነት መውሰዱ ታውቋል።

ፕሮጀክቱ በተጨማሪም በአገልግሎት ዲዛይን እና በተጠቃሚ ልምድ የሰለጠኑ ወጣት ባለሙያዎች ያደረጉት አስተዋጽኦ የመድረክ ቴክኒካዊ ጥንካሬ ከአጠቃቀም እና ግልጽነት ጋር እንዲጣጣም አድርጓል።

ወደፊት የሚመጡ እድገቶች ከማህደር እና ከቀደምት እትሞች ታሪካዊ መረጃዎችን መልሶ ማግኘት እና ማዋሃድ እንዲሁም የመድረኩን ተግባራት እና የትንታኔ አቅም በጊዜ ሂደት የሚያሰፉ አዳዲስ ልቀቶችን የሚያካትት እንደሚሆኑ ታውቋል።

በዚህም መሠረት የቅድስት መንበር ጽሕፈት ቤት መድረኩን የሚጠቀሙት በሙሉ አገልግሎቱን ለማሻሻል ምልከታዎችን እና አስተያየቶችን ወደ annuariopontificio@sds.va የተሰኘ አድራሻ በመላክ በማሻሻያው ላይ በንቃት እንዲሳተፉ ጋብዟል። ዋና መድረኩ  https://www.annuariopontificio.catholic/ በሚለው ድረ-ገጽ ላይ እንደሚገኝም ተገልጿል።

እንዲሁም ደረ-ገጹን ለ “iOS” እና ለ “አንድሮይድ” ስልኮች በተዘጋጀ መተግበሪያ በኩል መድረስ የሚቻል ሲሆን ተጠቃሚዎች በድረ-ገጹ ላይ መመዝገብ ወይም መተግበሪያውን ከ “App Store” ወይም “Google Store” ማውረድ እንዳለባቸው ተነግሯል።

ዓመታዊው የዲጂታል መጽሐፍ አገልግሎቱን የሚሰጠው በሁለት ዓይነት የደንበኝነት ምዝገባ ሥርዓት ሲሆን ሁለቱም በቀጣይነት ወደ “ዳታቤዙ” መድረስን እና ዕለታዊ እድሳቶችን የሚያረጋግጡ መሆናቸው ተገልጿል።

 

11 Dec 2025, 14:53