ፈልግ

ብጹዕ ካርዲናል ፒየትሮ ፓሮሊን ሮም ውስጥ በሚገኝ ሆስፒታል ውስጥ መስዋዕተ ቅዳሴን ሲያቀርቡ ብጹዕ ካርዲናል ፒየትሮ ፓሮሊን ሮም ውስጥ በሚገኝ ሆስፒታል ውስጥ መስዋዕተ ቅዳሴን ሲያቀርቡ 

ብጹዕ ካርዲናል ፓሮሊን፥ “ኢየሱስ በየቀኑ በልባችን ውስጥ እንዲወለድ መፍቀድ አለብን” ሲሉ አሳሰቡ

የቅድስት መንበር ዋና ጸሐፊ ብጹዕ ካርዲናል ፒየትሮ ፓሮሊን በሮም በሚገኝ አንድ ሆስፒታል ውስጥ የተዘጋጀውን መስዋዕተ ቅዳሴን በመሩበት ዕለት ባሰሙት ቃለ-ምዕዳን፥ “ኢየሱስ ክርስቶስ በየቀኑ በልባችን ውስጥ እንዲወለድ መፍቀድ አለብን” ብለዋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

ብጹዕ ካርዲናል ፒየትሮ ፓሮሊን ታኅሳስ 7/2018 ዓ. ም. ጠዋት በሮም የሚገኘውን የቆዳ ሕክምና ተቋምን ጎብኝተው፥ በተቋሙ ጸሎት ቤት የቀረበውን መስዋዕተ ቅዳሴ መርተዋል። ብጹዕነታቸው ከመስዋዕተ ቅዳሴው ሥነ-ሥርዓት በኋላ ለታካሚዎች ሰላምታቸውን አቅርበዋል።

የቅድስት መንበር ዋና ጸሐፊ ብጹዕ ካርዲናል ፒየትሮ ፓሮሊን በቃለ-ምዕዳናቸው፥ “በተስፋ እና በናፍቆት የተሞሉ የብርሃነ ልደቱ በዓል ቀናት የቤተ ክርስቲያን ማኅበረሰብን ወደ አዳኙ የብርሃነ ልደቱ ምስጢር የሚመሩ ናቸው” ብለው፥ በመሆኑም የብርሃነ ልደቱ ሰሞን የኢየሱስ ክርስቶስ ዳግም ምጽዓት ያማከለ ነው” ሲሉ አስረድተዋል።

በዚህ ረገድ የኢየሱስ ክርስቶስን መወለድ በሦስት መንገዶች መመልከት እንደሚገባ፥ የመጀመሪያው ከሁለት ሺህ ዓመታት በፊት በቤተልሔም የተፈጸመ፣ ሁለተኛው በዘመን መጨረሻ የሚመጣ፣ ሦስተኛው በየቀኑ በምዕመናን እና በክርስቲያን ማኅበረሰብ ልብ ውስጥ በቅዱስ ቃል እና በቅዱስ ቁርባን በኩል ሥር የሚሰድድ ነው” ብለዋል።

በሕመም ውስጥ አቅም ማጣት

ብጹዕ ካርዲናል ፓሮሊን በቀጠልም፥ ኢየሱስ ክርስቶስ ስለ ሁለቱ ልጆች ምሳሌ በሚተርክበት በዕለቱ የማቴዎስ ወንጌል ክፍል ላይ በማስተንተን እንደተናገሩት፥ የመጀመሪያው ልጅ በወይን እርሻ ውስጥ ሄዶ ለመሥራት ፈቃደኛ ባይሆንም ነገር ግን በኋላ ንስሐ ገብቶ ለሥራ እንደሄደ፤ ሁለተኛው ልጅ ወደ እርሻው ሄዶ ለመሥራት ቃል ቢገባም ነገር ግን ቃሉን ያልጠበቀ መሆኑን በማስታወስ በእርግጥ የአባቱን ፈቃድ የፈጸመው የመጀመሪያው ልጅ እንደሆነ አስረድተዋል።

“እግዚአብሔር ለተልዕኮው ቅን ልብ ያላቸውን ሰዎች ይፈልጋል” ያሉት ብጹዕ ካርዲናል ፓሮሊን፥ የተቋሙ ተልዕኮ በየቀኑ በሕመም መካከል አቅም የማጣት ስሜትን የሚገለጽ” ነው ብለዋል።

ታካሚዎችን ጎብኝተዋል

ኢየሱስ ክርስቶስ በየቀኑ በልባችሁ ውስጥ ካልተወለደ በቀር በቤተልሔም መወለዱ ፋይዳ የለውም” ብለው፥ ቃለ-ምዕዳናቸውን ያዳመጡት በሙሉ ተቋሙን ኢየሱስ ክርስቶስ የተወለደበት እውነተኛ  ሥፍራ እንዲያደርጉት አሳስበዋል።

ብጹዕነታቸው በመስዋዕተ ቅዳሴው ሥነ-ሥርዓት መደምደሚያ ላይ የሕፃኑ ኢየሱስን ምስል በተቋሙ መግቢያ ላይ በተዘጋጀው የገና ዛፍ ሥር ካስቀመጡ በኋላ ታካሚዎቹን በየክፍሎቻቸው ጎብኝተው  ሰላምታቸውን አቅርበዋል።

17 Dec 2025, 14:16