ፈልግ

በቻይና ውስጥ የምትገኝ ካቶሊካዊት ቤተ ክርስቲያን በቻይና ውስጥ የምትገኝ ካቶሊካዊት ቤተ ክርስቲያን 

የክርስትና እምነት ቻይናን እና ቤተ ክርስቲያንን ሊያገናኝ እንደሚችል ተገለጸ

የቫቲካን ሚዲያ ዋና ጽ/ቤት በቻይናዊው ደራሲ ኪያሬቶ ያን የተጻፈውን አዲስ መጽሐፍ ለማስመረቅ መዘጋጀቱ ታውቋል። የመጽሐፍ ርዕሥም “ከክርስትና እምነት ጋር የተደረጉ ውይይቶችን እና ገጠመኞችን የሚገልጽ ቻይናዊ ሕልሜ” የሚል እንደሆነ ተገልጿል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

ቻይናዊው ደራሲ ሕልሙ በክርስትና እምነት እና በቻይና መንግሥት መካከል ድልድይ መሆን እንደሆነ ገልጾ፥ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ ቻይናን እንደሚጎበኙት እና ቻይናም የወንጌልን ብርሃን እንደምትቀበል ተስፋ እንደሚያደርግ የቻይና ፎኮላሬ እንቅስቃሴ አባል ኪያሬቶ ያን ከቫቲካን ሚዲያ ጋር ባደረገው ቃለ ምልልስ ተናግሯል።

ከክርስትና እምነት ጋር የተደረጉ ውይይቶችን እና ገጠመኞችን የሚገልጽ “ቻይናዊ ሕልሜ” በሚል ርዕሥ የተጻፈው አዲሱ መጽሐፍ ቫቲካን ሚዲያ ዋና ጽሕፈት ቤት ውስጥ ታኅሳስ 7/2018 ዓ. ም. በይፋ ተመርቆ ለንባብ መብቃቱ ታውቋል።

ለእውነት፣ ለበጎነት እና ለውበት ያለው ሁለንተናዊ ፍላጎት

ሕልሜ “‘የክርስትና ባሕል ለቻይና ባሕል እንግዳ ሳይሆን የውይይት አጋር ነው’ በሚለው እምነት ላይ የተመሠረተ ነው” ሲል ደራሲ ኪያሬቶ ያን አስረድቷል።

“በእያንዳንዱ የሰው ልጅ ውስጥ ዓለም አቀፋዊ የእውነት፣ የበጎነት፣ የውበት እና የፍቅር ፍላጎት አለ” ያለው ኪያሬቶ ያን፥ “በባሕሎች እና በወጎች ውስጥ የሚገኝ የማያቋርጥ ጥልቅ ፍላጎት በክርስትና እምነት ውስጥ ከእግዚአብሔር ጋር ባለን የግል ግንኙነት አማካይነት ግልጽ ይሆናል” ሲል አስረድቷል።

“በአንድ በኩል የካቶሊክ እምነት ተከታይ ነኝ፤ በሌላ በኩል ቻይናዊ ነኝ” ያለው ደራሲው፥ እግዚአብሔር ለሰው ልጅ ካለው ፍቅር የተነሳ ሥጋን በመልበስ ወደ እኛ እንደመጣ የክርስትና እምነት እንደሚነግረው እና እግዚአብሔር ለሰው ልጅ ያለው ተነሳሽነትም መለኮታዊ መገለጥ እንደሆነ በማስረዳት፥ ሌሎች ባሕሎች እና ሃይማኖቶች የሰው ልጅ እግዚአብሔርን ለመፈለግ የሚያደርገውን ጥረት የሚያሳዩ መሆናቸውን እና እነዚህ ሁለት አቅጣጫዎች የሚገናኙ እንጂ እርስ በርስ የሚጋጩ አለመሆናቸውን ገልጿል።

አምስቱ የምርምር መንገዶች

በዚህ መንፈስ ደራሲው የቻይናን ባሕል እና የክርስትና እምነትን አንድ ላይ ሊያመጡ በሚችሉ አምስት የምርምር ዘርፎች ላይ ማተኮርን እንደመረጠ፥ እነዚህም ፍልስፍና፣ ሥነ-ምህዳር፣ ፖለቲካ፣ ምጣኔ ሃብት እና የባሕል ውይይት መሆናቸውን ገልጿል።

“እነዚህ በሙሉ እጅግ ወቅታዊ ጉዳዮች ናቸው” ያለው ያን፥ “ለመላው የሰው ልጅ የጋራ ፈተና መሆናቸውን “ውዳሴ ላንተ ይሁን” እና “ሁላችንም ወንድማማቾች ነን” በሚሉ የነፍስሔር ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳስት ፍራንችስኮስ ሐዋርያዊ ቃለ-ምዕዳናት እና በዘመናዊው የቻይና መንግሥት የክርክር መድረክ ላይ እናየዋለን” ብሏል።

በምዕራቡ ዓለም “ዲያሌክቲክ” ብዙውን ጊዜ እንደ ቅራኔ ቢታሰብም እንደ ሄግል ያሉ የፍልስፍና ሃሳቦችን በመከተል በ “ታኦይዝም” እምነት መልክ የሚይዝ መሆኑን፥ የዪን እና ያንግ እምነቶችም ቢሆኑ የሚቃረኑ ሳይሆኑ እርስ በርስ የሚደጋገፉ መሆናቸውን አስረድቷል።

በዚህ አመክንዮ መካከል ለክርስትና የሚገባው የፍቅር መግለጫ በተለይም ለሌሎች ቦታን በሚሰጥ እና የአባቱን ፈቃድ ለመፈጸም ራሱን ባዶ በማድረግ በመስቀል ላይ ባለው የክርስቶስ ምስጢር ውስጥ የሚመለከት መሆኑን ኪያሬቶ ያን ገልጿል።

በቻይና ፍልስፍናዊ ቋንቋም ቢሆን በመሆን እና ባለመሆን መካከል ያለውን ስምምነት የሚጠፋ ሳይሆን የሚያሳድግ እንደሆነ፣ ከዚህ ግንኙነት በመነሳት የሚፈጠረው ስምምነት ውይይት የበለጠ ጥልቀት እንዲኖረው እና ንግግርን እውን የሚያደርግ መሆኑን ኪያሬቶ ያን አስረድቷል።

የመጽሐፉ ምረቃ ሥነ-ሥርዓት

የመጽሐፉ የምረቃ ሥነ-ሥርዓት ያተኮረ በውይይት ላይ ሲሆን፥ በውይይቱም በሚላን ከተማ በሚገኘው ልበ ኢየሱስ ካቶሊክ ዩኒቨርሲቲ የዘመናዊ ታሪክ መምህር ፕሮፌሰር አጎስቲኖ ጆቫኞሊ፣ በቫቲካን የጆሴፍ ራትዚንገር (ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት በኔዲክቶስ 16ኛ) ፋውንዴሽን ፕሬዝዳንት አባ ፌዴሪኮ ሎምባርዲ እና በቅድስት መንበር የባህል እና የትምህርት ጳጳሳዊ ጽሕፈት ቤት ረዳት ጸሐፊ ​​አባ አንቶኒዮ ስፓዳሮ የተሳፉ ሲሆን፥ ውይይቱን የመሩት ፊድስ የተሰኘ የቫቲካን ዜና ወኪል ዳይሬክተር ጃኒ ቫለንቴ መሆናቸው ታውቋል።

 

18 Dec 2025, 14:55