ቅድስት መንበር የቻይና መንግሥት ለአቡነ ዣንግ ዌይዙ እውቅና በመስጠቱ የተሰማትን ደስታ ገለጸች
የቅድስት መንበር የመግለጫ ጽሕፈት ቤት ዳይሬክተር አቶ ማቴዮ ብሩኒ ኅዳር 27/2018 ዓ. ም. በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ፣ የቻይና መንግሥት የዢንዚያንግ ሐዋርያዊ አስተዳደር ለነበሩት አቡነ ዣንግ ዌይዙ የሰጠው እውቅና በቤተ ክርስቲያን የጋራ ጉዞ ውስጥ አስፈላጊ እርምጃ መሆኑን ተናግረዋል።
የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን
አቶ ማቴዮ ብሩኒ በመግለጫቸው፥ “የቻይና መንግሥት በሄናን ውስጥ የዢንዚያንግ ጳጳስ ለነበሩት አቡነ ዮሴፍ ዣንግ ዌይዙ የጵጵስና ማዕረግ እውቅናን በመስጠቱ ቅድስት መንበር የተሰማትን ደስታ ዛሬ ገልጻለች” ብለዋል።
የቅድስት መንበር መግለጫ ክፍል ዳይሬክተር አቶ ማቴዮ ብሩኒ ቅዳሜ ዕለት በሰጡት መግለጫ መሠረት፥ “ይህ እርምጃ በቅድስት መንበር እና በቻይና ባለስልጣናት መካከል የተደረገው ውይይት ውጤት ሲሆን፥ በቤተ ክርስቲያን ጉዳይ በሚያደርጉት የጋራ ጉዞ ውስጥ አዲስ እና አስፈላጊ እርምጃን የሚወክል ነው” ብለዋል።
ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ እንደ ጎርጎሮሳውያኑ ነሐሴ 11/2025 ዓ. ም. በቻይና ሄናን ግዛት የዢንዚያንግ ሐዋርያዊ አስተዳደር ጳጳስ አድርገው የሾሟቸው የአቡነ ፍራንሲስ ሊ ጃንሊን ሲመተ ጵጵስና በዓል ሥነ-ሥርዓት ዓርብ ኅዳር 26/2018 ዓ. ም. መካሄዱ ታውቋል።
ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ ዕጩነታቸው “በቅድስት መንበር እና በቻይና ሕዝባዊ ሪፐብሊክ መካከል በተደረገው ጊዜያዊ ስምምነት ማዕቀፍ ውስጥ” አጽድቀው አቡነ ዮሴፍ ዣንግ ዌይዙ ያቀረቡትን የሐዋርያዊ አስተዳደር የስልጣን መልቀቂያ ጥያቄ ተቀብለዋል።
09 Dec 2025, 17:15