ፈልግ

በቅዱስ ጴጥሮስ አደባባይ ላይ የተዘጋጀው የኢየሱስ ክርስቶስ ልደት ትዕይንት በቅዱስ ጴጥሮስ አደባባይ ላይ የተዘጋጀው የኢየሱስ ክርስቶስ ልደት ትዕይንት  (@Vatican Media)

በቅዱስ ጴጥሮስ አደባባይ ላይ የተዘጋጀ የኢየሱስ ክርስቶስ ልደት ትዕይንት እና የገና ዛፍ ለሕዝብ ይፋ ሆነ

ቫቲካን በቅዱስ ጴጥሮስ አደባባይ ላይ የተዘጋጀው የኢየሱስ ክርስቶስ ልደት ትዕይንት እና የገና ዛፍ በማስመረቅ ለሕዝብ ይፋ አድርጓል። በቫቲካን ግዛት አስተዳደር ፕሬዝዳንት እህት ራፋኤላ ፔትሪኒ እና ትዕይንቱን ለማዘጋጀት ግብዓት የሚሆኑ ቁሳ ቁሶችን የለገሡ ሀገረ ስብከቶች ተወካዮች እና የመንግሥት ባለሥልጣናት በሥነ-ሥርዓቱ ላይ ተገኝተዋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

በቫቲካን በሚገኘው ቅዱስ ጴጥሮስ አደባባይ ላይ የተዘጋጀው የኢየሱስ ክርስቶስ ልደት ትዕይንት እና የገና ዛፍ በግዛቱ አስተዳደር ፕሬዝደንት በእህት ራፋኤላ ፔትሪኒ ሰኞ ታኅሳስ 6/2018 ዓ. ም. በይፋ ተመርቆ ለሕዝብ ይፋ ሆኗል።

እህት ራፋኤላ ፔትሪኒ በሥነ-ሥርዓት ላይ ባደረጉት ንግግር፥ “ዛሬ ዓለምን በሚያቅፈው በዚህ አደባባይ የኢየሱስን ልደት የሚያስታውስ ትዕይንት እና የገና ዛፍ የብርሃነ ልደቱ በዓል ማስገጫ ብቻ ሳይሆኑ የኅብረት ምልክቶች፣ የሰላም እና የፍጥረት እንክብካቤ ጥሪዎች እና ከሁሉም በላይ ቅዱስ ፍራንችስኮስ ያስቀመጠውን እና የክብሩ መለያ የሆኑ ሁለንተናዊ የወንድማማችነት ጥሪዎች ናቸው” ሲሉ አስረድተው፥ የሚቀጥለው ዓመት የኢየሱስ ክርስቶስ ልደት ትዕይንትን የማዘጋጀት ባሕል እንደ ጎርጎሮሳውያኑ በ1223 ዓ. ም. የጀመረው የአሲሲው ቅዱስ ፍራንችስኮስ ዕረፍት 800ኛ ዓመት መሆኑን አስታውሰዋል።

በምረቃው ሥነ-ሥርዓት ላይ ለትዕይንቱ ዝግጅት ግብዓት የሚሆኑ ቁሳቁሶችን የለገሡ የሀገረ ስብከቶች የሃይማኖት እና የሲቪል ማኅበረሰብ ተወካዮች ተገኝተው ንግግር ያደረጉ ሲሆን፥ ቀደም ብሎም ተወካዮቹ ከርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ ጋር መገናኘታቸው ታውቋል። የቫቲካን ዘብ ጠባቂ ባንድ እና ከሀገረ ስብከቶች የተውጣጡ ልዩ ልዩ መዘምራን እና የሙዚቃ ባንዶች ባሕላዊ የገና መዝሙሮችን እና ውዝዋዜዎችን አቅርበዋል።

የኢየሱስ ክርስቶስ ልደት ምሳሌያዊ ትዕይንት እና የገና ዛፍ እስከ ብርሃነ ልደቱ በዓል ሰሞን መጨረሻ ድረስ ለእይታ ክፍት ሆነው የሚቆዩ ሲሆን፥ ይህም በላቲን የአምልኮ ሥርዓት መሠረት እሁድ ጥር 3/2018 ዓ. ም. የሚከበረው የኢየሱስ ክርስቶስ የጥምቀት በዓል ዕለት እንደሆነ ታውቋል።

አሁን በቅዱስ ጴጥሮስ አደባባይ ላይ የሚገኘውን የኢየሱስ ልደት ምሳሌያዊ ትዕይንት ያዘጋጀው በደቡቡ ጣሊያን የሚገኘው የኖሴራ ኢንፌሪዮር-ሳርኖ ሀገረ ስብከት ሲሆን፥ በሀገረ ስብከቱ ተወክለው ያመጡትም አቡነ ጁሴፔ ጁዲቼ መሆናቸው ታውቋል። ከእህት ራፋኤላ ፔትሪኒ በተጨማሪ የቫቲካን ግዛት አስተዳደር ዋና ጸሐፊዎች ሊቀ ጳጳስ አቡነ ኤሚሊዮ ናፓ እና አቡነ ጁሴፔ ፑሊሲ-አሊብራንዲ በሥነ-ሥርዓት ላይ ተገኝተዋል።

የኢየሱስ ልደት ምሳሌያዊ ትዕይንት

በቅዱስ ጴጥሮስ አደባባይ ላይ የሚገኘው የኢየሱስ ልደት ምሳሌያዊ ትዕይንት 17 በ12 ሜትር ስፋት ባለው ቦታ የተዘጋጀ ሲሆን ቁመቱም 7.70 ሜትር እንደሆነ ታውቋል። ምሳሌያዊ ትዕይንቱ በደቡብ ጣሊያን የአግሮ ኖሴሪኖ-ሳርኔስ አካባቢ በርካታ ባሕላዊ የሥነ-ሕንፃ እና እንዲሁም በአካባቢው የታወቁ ቅዱሳን፥ የእጅግ ቅዱስ ቤዛ ገዳማዊ ማኅበር መሥራች እንደ ቅዱስ አልፎንሰስ ሊጉሪ እና የእግዚአብሔር አገልጋዮች አባ ኤንሪኮ ስማልዶን እና አልፎንሶ ሩሶ ያሉ ቅዱሳን እና የሃይማኖት ሰዎች ምስሎችን የሚያሳይ እንደሆነ ታውቋል።

ትዕይንቱ በተጨማሪም የአካባቢውን የምግብ እና የወይን ተክል ቅርሶችን የሚያጎሉ ምልክቶችን ያካተተ ሲሆን፥ የወለል ንጣፉ በድንጋይ የተሠሩ ጥንታዊ የሮማውያን መንገዶችን እና ትክክለኛ መጠን ያላቸውን እረኞችን እና የእንስሳት ምስሎችን የሚያሳይ እንደሆነ ተመልክቷል።

የገና ዛፍ

በትዕይንቱ መካከል የቆመው 25 ሜትር ቁመት ያለው እና 8000 ኪሎ ግራም የሚመዝነውን የገና ዛፍን በስጦታነት የሰጡት በሰሜን ጣሊያን በቦልዛኖ-ብሬሳኖን ሀገረ ስብከት የሚገኙ የላጉዶ እና ኡልቲሞ ማዘጋጃ ቤቶች እንደሆነ ታውቋል።

ከዋናው ዛፍ በተጨማሪ ወደ ቫቲካን የተላኩ ሌሎች 40 ትናንሽ የዛፍ ችግኞች የቅድስት መንበር ጽሕፈት ቤቶችን፣ የሕዝብ መሰብሰቢያዎችን እና ሕንፃዎችን ለማስዋብ እንደሚያገለግሉ ታውቋል። የብርሃነ ልደቱ በዓል ሲጠናቀቅ ዛፉ የያዛቸው ጠቃሚ ዘይቶች ተጨምቀው ከወጡ በኋላ የተቀረው እንጨት ለፍጥረት እንክብካቤ በሚስማማ መልኩ በማኅበራት ጥረት እንደገና ጥቅም ላይ እንዲውሉ እንደሚደረጉ ተገልጿል።

በቅዱስ ጴጥሮስ አደባባይ ላይ የተዘጋጀ የኢየሱስ ክርስቶስ ልደት ትዕይንት

 

16 Dec 2025, 12:20