ፈልግ

በዛፖሪዝሂያ ከተማ የሩሲያ ሰው አልባ አውሮፕላን ጥቃት ካደረሰ በኋላ በዛፖሪዝሂያ ከተማ የሩሲያ ሰው አልባ አውሮፕላን ጥቃት ካደረሰ በኋላ 

ሊቀ ጳጳስ ጋላገር እያንዳንዱ ጦርነት የሞራል እና ሰብዓዊ ውድቀትን እንደሚያደርስ ገለጹ

በቅድስት መንበር የመንግሥታት እና ዓለም አቀፍ ድርጅቶች ግንኙነት ክፍል ዋና ጸሐፊ የሆኑት ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ አቡነ ፖል ሪቻርድ ጋላገር ለአውሮፓ የጸጥታ እና ትብብር ድርጅት ሩሲያ ዩክሬን ላይ ወረራ ያካሄደችበት አራተኛ ዓመትን አስመልክቶ ባዘጋጀው ዝግጅት ላይ ባደረጉት ንግግር ለዩክሬን ፍትሃዊ እና ዘላቂ ሰላም እንዲሰፍን ትክክለኛ የሆኑ መንገዶች እንዲፈለጉ ጥሪ ማቅረባቸው ተነግሯል።

  አቅራቢ ዘላለም ኃይሉ ፥ አዲስ አበባ

ሊቀ ጳጳስ ጋላገር በ1554ኛው የአውሮፓ የጸጥታ እና ትብብር ድርጅት (OCSE) ቋሚ ምክር ቤት የማጠናከሪያ ስብሰባ ላይ ባደረጉት ንግግር ዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ በዩክሬን ሰላም እንዲሰፍን ተጨባጭ እርምጃዎችን እንዲወስድ አሳስበዋል።

የካቲት 17 ቀን 2018 ዓ.ም. ሩሲያ ዩክሬን ላይ ሙሉ ወረራ የፈጸመችበት አራተኛ ዓመት አስመልክቶ በተዘጋጀው ዝግጅት ላይ ባደረጉት ንግግር "ለፍትሃዊ እና ዘላቂ ሰላም ዓላማ ያላቸው ቅን እና ሁሉን አቀፍ የዲፕሎማሲ ሂደቶችን ለመመስረት እና ለማስቀጠል ሁሉም አካላት አስፈላጊውን ፖለቲካዊ ድፍረት እንዲያሳዩ ቅድስት መንበር ታሳስባለች ያሉት ሊቀ ጳጳስ ጋላገር፥ “እያንዳንዱ ጦርነት የሞራል እና ሰብዓዊ ውድቀትን ይወክላል” ብለዋል።

ተጨባጭ እርምጃዎችን መውሰድ ያስፈልጋል
ሊቀ ጳጳስ ጋላገር ሰላም እንዲሰፍን “ተጨባጭ እርምጃዎች መወሰድ እንዳለባቸው” ጠቁመው፥ “ከፍተኛ ህዝባዊ ኃላፊነት የተጣለባቸው ሰዎች በጎ ፈቃድን ወደተረጋገጠና ዘላቂ የሰላም ዝግጅቶች ለመተርጎም ከቀጣይ ዲፕሎማሲያዊ ተሳትፎ ጋር አፋጣኝ ሰብአዊ ድጋፎችን ማስቀደም እንደሚገባ ያሳሰቡ ሲሆን፥ “ውይይት በቅን ልቦና እና ግዴታዎችን በታማኝነት በመወጣት ላይ የተመሰረተ መሆን እንዳለበት” አጥብቀው ገልጸዋል።

በዚህ ረገድ ቅድስት መንበር ውይይቶችን በማመቻቸት፣ በራስ መተማመንን ለማጎልበት እና የጸጥታ ሁኔታን ወደነበረበት ለመመለስ እርምጃዎችን በመተግበር ረገድ የአውሮፓ የጸጥታ እና ትብብር ድርጅት ትልቅ ሚና ሊጫወት እንደሚችል ቅድስት መንበር ያላትን እምነት ጠቁመዋል።

ከዚህም በተጨማሪ ቅድስት መንበር ሰብዓዊነትን እና ስቃይ መቀነስን የጥረታቸው ማዕከል የሚያደርጉትን ማንኛውንም ቅን ዲፕሎማሲያዊ ተነሳሽነት ለመደገፍ ዝግጁ መሆኗን አጽንኦት ሰጥተው ገልጸዋል።

ሊቀ ጳጳስ ጋላገር በመቀጠልም ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ አሥራ አራተኛ ዓለም አቀፍ የሰብአዊ ሕግን የማክበር አስፈላጊነትን በተመለከተ ያላቸውን አቋም በማስተጋባት፥ እነዚህን ህጎች ማክበር በሁኔታዎች ወይም በወታደራዊ እና ስልታዊ ፍላጎቶች ላይ የተመሰረተ መሆን እንደማይገባ አሳስበዋል።

ዓለም አቀፉ የሰብአዊነት ህግ የጦርነትን አስከፊ ተፅእኖዎች ለመቅረፍ እንዲሁም መልሶ ለመገንባት በማሰብ ሁልጊዜ በተፋላሚዎች ፍላጎት ላይ የበላይነት ሊኖረው እንደሚገባ የጠቆሙት ሊቀ ጳጳሱ፥ “የሰው ልጅ ሕይወት እና ክብር የተቀደሰ መሆኑን በምናነሳበት ወቅት ሁሉም አካላት በአስቸኳይ እና በርህራሄ እንዲንቀሳቀሱ እንዲሁም ወደ ሰላም የሚያመሩ መንገዶችን በቅን ልቦና በመፈለግ ውይይት እንዲያደርጉ ቅድስት መንበር ጥሪ ታቀርባለች” ሲሉ ጥር 1 ቀን 2018 ዓ.ም. በቅድስት መንበር እውቅና ለተሰጣቸው የዲፕሎማቲክ አካላት ያደረጉትን ንግግር ጠቅሰዋል።

27 Feb 2026, 13:41