ፈልግ

እ.አ.አ. በ 2024 በሮም ኦሎምፒክ ስታዲየም የተከበረው የዓለም የህፃናት ቀን እ.አ.አ. በ 2024 በሮም ኦሎምፒክ ስታዲየም የተከበረው የዓለም የህፃናት ቀን   (Vatican Media)

ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ የዓለም የህፃናት ቀን ኮሚቴን ማሰናበታቸው ተነገረ

ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ አሥራ አራተኛ በርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቺስኮስ እ.አ.አ. በ 2024 የተቋቋመውን የዓለም የህፃናት ቀን ጳጳሳዊ ኮሚቴ በይፋ ሥራ ማቆሙን የሚገልጽ ጽሁፍ ማሳተማቸው ተነግሯል።

  አቅራቢ ዘላለም ኃይሉ ፥ አዲስ አበባ

ባለፈው ዓመት ነሐሴ ወር ላይ የዓለም ሕጻናት ቀን ጳጳሳዊ ኮሚቴው በቀጥታ በቅዱስ አባታችን የሚመራ ተቋም ተደርጎ በቅድስት መንበር የምዕመናን፣ ቤተሰብ እና የሕይወት ጉዳዮች ጽህፈት ቤት ሥር እንዲተዳደር ከተደረገ በኋላ፥ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ አሥራ አራተኛ የካቲት 6 ቀን 2018 ዓ.ም. ታትሞ በወጣ ጽሁፍ ኮሚቴው ጊዜውን መጨረሱን አሳውቀው መሰረዛቸው ተገልጿል።

እ.አ.አ. በ 2024 ዓ.ም. በርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቺስኮስ የተቋቋመው ይህ ኮሚቴ ዋና ዓላማው የዓለም የሕፃናት ቀን “ቤተ ክርስቲያናዊ እንቅስቃሴ እና ሃዋሪያዊ ሥራዎችን እንዲመራ ታስቦ የተቋቋመ መሆኑ የተነገረ ሲሆን፥ ይህ በዓል የዓለም ወጣቶች ቀንን ፈለግ የተከተለ እና በሺዎች የሚቆጠሩ ህፃናትን ለሙዚቃ፣ ለእምነት እና ለምስክርነት ከዓለም ዙሪያ ወደ ሮም ያመጣ ክስተት እንደነበር ተገልጿል።

ኃላፊነቱ ለቅድስት መንበር የምዕመናን፣ ቤተሰብ እና ሕይወት ጉዳዮች ጽ/ቤት ተላልፏል
ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ ባለፈው ህዳር ወር ላይ እንዳስታወቁት ሁለተኛው ዙር የዓለም ህፃናት ቀን ከመስከረም 15 እስከ 17 ቀን 2019 ዓ.ም. ድረስ በሮም እንደሚከበር ማሳወቃቸው የሚታወስ ሲሆን፥ የብፁዕነታቸው ደብዳቤ “ቀደም ሲል በጳጳሳዊ ኮሚቴ ሥር የነበሩት ጉዳዮች በሙሉ የቅድስት መንበር የምዕመናን፣ ቤተሰብ እና ሕይወት ጉዳዮች ጽህፈት ቤት ኃላፊነቱን ይወስዳል” በማለት ገልፆ ዝግጅቱን የማደራጀት እና የማስተባበር ሃላፊነት በአሁኑ ወቅት ሙሉ በሙሉ በብፁዕ ካርዲናል ኬቨን ፋሬል ለሚመራው ጽህፈት ቤት መተላለፉ ተነግሯል።

ቅንጅቶችን እና ቅልጥፍናን ማሳደግ
ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ እንዳብራሩት እዚህ ውሳኔ ላይ የተደረሰው በነሃሴ ወር ላይ የተቀመጠውን አቅጣጫ በማስቀጠል “በተገቢው መንገድ ምክክር ከተደረገ በኋላ ይህንን መልካም ተነሳሽነት እውን ለማድረግ ትብብርን እና የበለጠ ውጤታማ ሥራን በተሻለ መንገድ ለማስተዋወቅ ያለመ እንደሆነ ገልጸዋል።

ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ በተጨማሪም ጳጳሳዊ ኮሚቴው የተመሰረተበትን ሰነድ እና ተዛማጅ የሆኑ ህጎችን የሰረዙ ሲሆን፥ በኮሚቴው “ከዚህ ቀደም የወጡ ማናቸውንም ድርጊቶች እና መመሪያዎች” መሻራቸውን ገልጸው፥ በቀኖና እና በፍትሐ ብሔር አሰራሮች ውስጥ ህጋዊ ተጽእኖ ማሳደራቸውን እንደሚያቆሙ እና ከዚህም በተጨማሪ ፕሬዚዳንቱ፣ ምክትል ፕሬዚዳንቱ እና ሌሎች የኮሚቴው አባላት ሥራቸውን እንደሚያቆሙ አሳውቀዋል።

በሰነዱ መሠረት የቅድስት መንበር የምዕመናን፣ ቤተሰብ እና የሕይወት ጉዳዮች ጽህፈት ቤት አስተዳዳሪ “በኮሚቴው ውስጥ ያሉትን ዋና ዋና ጉዳዮች እንደሚገልጽ” እና “የቀረውን የንብረት ክፍፍል በተመለከተ ውሳኔ ለማግኘት ለኢኮኖሚያዊ ጉዳዮች ጽህፈት ቤት የመጨረሻ ደረጃ ሪፖርት እንደሚያቀርብ ተገልጿል።የመጀመርያው የዓለም የህፃናት ቀን ግንቦት 17 ቀን 2016 ዓ.ም. ሮም ውስጥ በሚገኘው የኦሎምፒክ ስታዲየም ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቺስኮስ በተገኙበት እና በጦርነት ከተጎዱ አካባቢዎች የመጡትን ጨምሮ ከ50,000 በላይ ህፃናት እና ታዳጊዎች በተገኙበት መካሄዱ ይታወቃል።

16 Feb 2026, 14:09