ፈልግ

በቅድስት መንበር የሰው ልጅ ሁለንተናዊ ዕድገት አገልግሎት ጽሕፈት ቤት የአመራር አባላት በቅድስት መንበር የሰው ልጅ ሁለንተናዊ ዕድገት አገልግሎት ጽሕፈት ቤት የአመራር አባላት 

የተቀናጀ የሰው ልጅ ልማትን ለማስተዋወቅ የሚያግዝ የአንድ ሳምንት ስብሰባ መካሄዱ ተገለጸ

በቅድስት መንበር የሰው ልጅ ሁለንተናዊ ዕድገት አገልግሎት ጽሕፈት ቤት ውስጥ የሚሠሩትን ጨምሮ በውጭ አገራት የሚገኙ ተባባሪዎችን እና በጎ ፈቃደኞችን ያሳተፈ የአንድ ሳምንት ስብሰባ መካሄዱ ታውቋል። አባላቱ በሮም የተሰበሰቡት ተነሳሽነቶቻቸውን ለማቅረብ እና ለመጋራት እንደሆነ ታውቋል። የጳጳሳዊ ጽሕፈት ቤቱ ሃላፊ ብጹዕ ካርዲናል ሚካኤል ቼርኒ የስብሰባውን ዓላማ ሲያብራሩት፥ የርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳትን እና በዓለም ዙሪያ የሚገኙ ብጹዓን ጳጳሳት ተልዕኮ መደገፍ” ነው ሲሉ ገልጸዋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

የቅድስት መንበር የሰው ልጅ ሁለንተናዊ ዕድገት አገልግሎት ጽሕፈት ቤት ሠራተኞች፣ በውጭ አገራትም ሆነ በአገር ውስጥ የሚገኙ ተባባሪዎች እና በጎ ፈቃደኞች ከሚያዝያ 15-22/2018 ዓ. ም. ድረስ በቅዱስ ካሊስቶ ሕንጻ ውስጥ በሚገኘው የጽሕፈት ቤቱ ዋና መሥሪያ ቤት መሰብሰባቸው ታውቋል።

ስብሰባው ከሮም ውጭ የሚሠሩ ከዳያስፖራ የተውጣጡ ተባባሪ አባላትን ጨምሮ ለሁሉም ሰው የሚሆኑ ልዩ ልዩ አሳታፊ ዝግጅቶች የቀረቡበት ሲሆን፥ እነዚህም የቫቲካን ሙዚየሞችን እና “የውዳሴ ላንተ ይሁን” መንደርን መጎብኘት እንዲሁም በቅዱስ ጴጥሮስ አደባባይ በመገኘት ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ በሚመሩት “የእመቤታችን ማርያም የሰማይ ንግሥት” ጸሎት መሳተፍን ያካተተ እንደ ነበር ታውቋል።

የስብሰባው ተካፋዮች
የስብሰባው ተካፋዮች

ጭብጦችን ከማሸከም ይልቅ ማዳመጥ

የሳምንቱ ዝግጅት የተጀመረው እንደ ጎርጎሮሳውያኑ በ2023 ዓ. ም. ሲሆን፥ በሚቀጥሉት ዓመታትም ተጠናክሮ እንደሚቀጥ ተገልጿል። በቅድስት መንበር የሰው ልጅ ሁለንተናዊ ዕድገት አገልግሎት ጽሕፈት ቤት ሃላፊ ብጹዕ ካርዲናል ሚካኤል ቼርኒ፥ በአሁኑ ጊዜ የጽሕፈት ቤቱን ተልዕኮ እንደገና መመልከት እንደሚያስፈልግ ገልጸው፥ ቀልጣፋ አሠራርን ለማሳደግ የውስጥ ግንኙነትን ማጠናከር እንደሚገባ፣ በዋና መሥሪያ ቤት በሚሠሩት እና በዳያስፖራው ውስጥ ባሉት ሰዎች መካከል ያለውን ግንኙነት ማጠናከር እና የጽሕፈት ቤቱ አገልግሎት ጥራትን ማሳደግ እንደሆነ አስረድተዋል።

ብጹዕ ካርዲናል ሚካኤል ቼርኒ በስብሰባው ወቅት “ዶግማ” ብለው የጠሩትን ቃል በመጥቀስ ስለጭብጦች ሲናገሩ፥ ጽሕፈት ቤቱ በከፍታ ላይ ላስቀመጣቸው ነጥቦች ቅድሚያ እንደማይሰጥ ገልጸው፥ ይልቁንም በየአካባቢው የሚገኙ ቤተ ክርስቲያናትን በማዳመጥ፥ በልዩ አውዶች ውስጥ የሰው ልጅ ዕድገትን የሚያደናቅፉ ነገሮች ለመፍታት የሚያደርጉትን ጥረት ማገዝ እንደ ሆነ ተናግረዋል።

የጳጳሳዊ ጽሕፈት ቤቱ ዋና ጸሐፊ እህት አሌሳንድራ ስመሪሊ ይህን አመለካከት በመደገፍ እንደተናገሩት፥ ሳምንቱ ሌሎች ዕለታዊ እንቅስቃሴዎችን በመተው ኃይልን ጨምረው የተወያዩበት ጊዜ እንደ ነበር ገልጸው፥ እንደ ዋና መሪ አድርገው ያቀረቡት ቁልፍ ቃል “እውቀት” የሚል እንደ ነበር አስረድተዋል።

እንደ ጎርጎሮሳውያኑ ከ 2025 ዓ. ም. ጀምሮ በቅድስት መንበር ጽሕፈት ቤት የጠቅላላ ጉዳዮች አዲስ አማካሪ ሆነው የተሾሙት ምክትል ፀሐፊ ሞንሲኞር ጆዜፍ ባርላሽ፥ ዲያስፖራው የሎጂስቲክስ ጉዳዮችን የሚመለከት ብቻ ሳይሆን በዓለም ዙሪያ በሁሉም አቅጣጫ የሚገኝ የቤተ ክርስቲያን ምስል እንደሆነ አፅንዖት ሰጥተዋል።

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳትን እና ጳጳሳትን መርዳት'

በአዳራሹ ውስጥ ከተለያዩ ቦታዎች፣ የዕድሜ ክልሎች፣ ቋንቋዎች እና ሚናዎች የመጡት የሳተፉበት ስብሰባው የደመቀ እና በሕያው ድባብ ውስጥ የተካሄደ ሲሆን፥ ብጹዕ ካርዲናል ቼርኒ በስብሰባው ማጠቃለያ ለሁሉም የጽሕፈት ቤቱ መምሪያዎች እና ዘርፎች፣ በማዳመጥ እና በውይይት፣ በምርምር እና በአስተንትኖ፣ በመገናኛ፣ በጸሐፊነት፣ በአገልግሎቶች፣ በአስተዳደር እና በእቅድ ሥራ ለተባበሩት ምስጋናቸውን አቅርበዋል።

በስልጠናው መካከል ምክትል ጸሐፊው ብጹዕ ካርዲናል ፋቢዮ ባጆ የመሩት ተከታታይ የድጋፍ ሂደት፥ አንዱ የስልጠናው ግብ ዝግጅቶችን ማደራጀት ሳይሆን ሂደቶችን ማጀብ እና ተነሳሽነቶችን መደገፍ እንደ ነበር ገልጸው፥ እነዚህ ተጨባጭ የሐዋርያዊ አገልግሎት ውጤቶችን ለማሳካት የታለሙ እና በአካባቢው በሚገኙ ቤተ ክርስቲያናት ውስጥ ዘላቂ ምልክቶችን የመተው አቅም ያላቸው መንገዶች እንደሆኑ አስረድተዋል።

ብጹዕ ካርዲናል ሚካኤል ቼርኒ (መሃል) ለስብሰባው ተሳታፊዎች ንግግር ሲያደርጉ
ብጹዕ ካርዲናል ሚካኤል ቼርኒ (መሃል) ለስብሰባው ተሳታፊዎች ንግግር ሲያደርጉ

የውስጥ ግንኙነት መመርመር

በሳምንቱ ውስጥ መላው የጽሕፈት ቤቱ ሠራተኞች እንደ ጎርጎሮሳውያኑ በ2024 የተጀመረውን ፕሮጀክት በመቀጠል የውስጥ ግንኙነትን ለማሻሻል በሚረዱ አዳዲስ ስልቶች ላይ ለመወያየት ዕድል አግኝተዋል።እህት አሌሳንድሮ ስመሪሊ የስልጠና ክፍለ ጊዜን ሲያስተዋውቁ እንደተናገሩት፥ የዕለት ተዕለት ሥራን በማከናወን ረገድ ለውጤታማ ግንኙነቶች አስፈላጊነት አፅንዖት ሰጥተዋል።

የስብሰባው ዋና ክፍል ተግባራዊ ልምምድ ማድረግ ሲሆን፥ ተሳታፊዎች በሰባት ቡድኖች ተከፍለው በሂደቱ ውስጥ በተነሱ ርዕሠ ጉዳዮች ላይ በመሥራት ከስብሰባዎች ውጤታማነት እስከ መምሪያዎች ትብብር እና የመረጃ ፍሰቶች አስተዳደር ድረስ በመወያየት ምልከታዎችን እና የአሠራር ሃሳቦችን አቅርበዋል።

በውዳሴ ላንተ ይሁን መንደር የተካሄደ ስብሰባ

ለሚያዝያ 20/2018 ዓ. ም. የተመደቡ የሥራ እንቅስቃሴዎች የተከናወኑት በካስቴል ጋንዶልፎ በሚገኘው “ውዳሴ ላንተ ይሁን” መንደር ሲሆን፥ ቀኑ የተጀመረው በቅድስት መንበር የመለኮታዊ አምልኮ እና የቅዱሳት ምስጢራት ጉዳይ ጽሕፈት ቤት ጸሐፊ ሊቀ ጳጳስ አቡነ ቪቶሪዮ ፍራንችስኮ ቪዮላ በመሩት የቅዱስ ቁርባን ስግደት እንደ ነበር ታውቋል።

ብጹዕ ካርዲናል ቼርኒ፥ “የድሆችን እና የምድርን ጩኸት መስማት” በሚለው የሲኖዶሱ የጥናት ቡድን 2 ሠነድ ላይ በማስተንተን ቃለ-ምዕዳናቸውን አሰምተዋል። ብጹዕነታቸው በአስተንትኖአቸው፥ ድሆችን ዋና ገፀ-ባህሪያት አድርጎ የመቁጠር አስፈላጊነትን አስረድተዋል።

በካስቴል ጋንዶልፎ “ውዳሴ ላንተ ይሁን” መንደር የቀረበ የመስዋዕተ ቅዳሴ ጸሎት
በካስቴል ጋንዶልፎ “ውዳሴ ላንተ ይሁን” መንደር የቀረበ የመስዋዕተ ቅዳሴ ጸሎት

የመጨረሻ ማበረታቻዎች

ብጹዕ ካርዲናል ሚካኤል ቼርኒ በስብሰባው ማጠቃለያ ባስተላለፉት መልዕክት፥ የስብሰባው ተሳታፊዎች በዓለም ዙሪያ በተለያዩ ክልሎች ለሚደርሱ አደጋዎች ትኩረት መስጠትን እንዲቀጥሉ እና በአደጋው ለተጎዱት ድጋፋቸው እንዲያቀርቡ አሳስበው፥ እንዲሁም ጳጳሳዊ ጽሕፈት ቤቱ ለበጎ አድራጎት አገልግሎቱ አዲስ የትብብር መንገዶችን እንዲያቀርብ አሳስበዋል።

በተጨማሪም ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ በካሜሩን ሐዋርያዊ ጉብኝታቸው ወቅት በማዕከላዊ አፍሪካ ካቶሊክ ዩኒቨርሲቲ ያደረጉትን ንግግር በመጥቀስ፥ “ማንኛውም ማኅበረሰብ በቅን ህሊና ላይ የተመሠረተ ካልሆነ በስተቀር ሊያድግ አይችልም” ማለታቸውን አስታውሰዋል።

ከቅዱስነቸው የቀረበውን ሃሳብ መሠረት በማድረግ ካርዲናሉ እንደተናገሩት፥ በቅድስት መንበር የሰው ልጅ ሁለንተናዊ ዕድገት አገልግሎት ጽሕፈት ቤት ዕለታዊ ተግባር በሐዋርያዊ አገልግሎት እና በደጋፊነት ውስጥ እንደ ማበረታቻ እና እንደ ፈተና መቅረቡን አስታውሰዋል።

ሁሉም ነገር ሊነገር እና ሊታሰብ በሚቻልበት ዲጂታሉ ዓለም ውስጥ “ቅን ሕሊና እና ቅዱስ ዕረፍት” ወደ ጋራ የሰው ልጅ ዕድገት ለሚደረገው ጉዞ ጠንካራ መሠረት እንደሆነ ገልጸው፥ በሌላ አነጋገር ኢየሱስ ክርስቶስ ቃል የገባውን “የተሞላ ሕይወት” ማስፋፋት እንደሆነ አስረድተዋል።

 

12 May 2026, 16:25