ፈልግ

በኒውክሌር ጦርነት እና በሰው ሠራሽ አስተውሎት ላይ ውይይት እየተካሄደ እንደሚገኝ ተገለጸ

የኖቤል ተሸላሚዎችን ያሳተፈ፥ በኒውክሌር ጦርነት እና በሰው ሠራሽ አስተውሎት ላይ የሚወያይ የባለሙያዎች ጉባኤ በካስቴል ጋንዶልፎ የ “ወዳሴ ላንተ ይሁን” መንደር ሐምሌ 7/2018 ዓ. ም. መጀመሩ ታውቋል። ጉባኤው የኖቤል ተሸላሚዎችን፣ ባለሙያዎችን፣ የዩኒቨርሲቲ ተወካዮችን በማሳተፍ ዓለማችንን እየጎዱ ባሉ ትልልቅ ፈተናዎች ላይ እንደሚወያይ ታውቋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

ከ200 በላይ የኖቤል ሽልማት አሸናፊዎች፣ የቀድሞ የሀገር መሪዎች፣ የዩኒቨርሲቲ ተወካዮች እና ባለሙያዎች ማክሰኞ ሐምሌ 7/2018 ዓ. ም. በካስቴል ጋንዶልፎ በሚገኝ የአትክልት ሥፍራ ተሰብስበው በሰው ሠራሽ አስተውሎት እና በኒውክሌር ጦርነት ላይ ውይይት መጀመራቸው ታውቋል።

በሰው ሠራሽ አስተውሎት እና በኒውክሌር ጦርነት ላይ እየተወያየ እስከ ሐሙስ ድረስ የሚቆየው ዓለም አቀፍ ጉባኤው፥ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ በሰው ሠራሽ አስተውሎት ዘመን የሰውን ልጅ ከጉዳት ለመታደግ ጥረት ካደረጉበት፥ “የሰው ልጅ ታላቅነት” ከተሰኘ ጳጳሳዊ መልዕክት ላይ ተነሳሽነትን ማግኘቱ ታውቋል።

ጉባኤው በማጠቃለያው በሰው ሠራሽ አስተውሎት፣ በኒውክሌር ጦርነት፣ በራስ ገዝ የጦር መሣሪያዎች፣ በአዳዲስ የዲጂታል ፕሮቶኮሎች እና በዲጂታል ዘመን የመሣሪያ ትጥቅ የሌለበት ሰላምን አስመልክቶ የሚጸድቀውን የስምምነት ሠነድ እንደሚፈርም ታውቋል።

ለሦስት ቀናት የሚቆየው ጉባኤው በተለይም በትብብር፣ በሰው ልጅ ክብር፣ በተቀናጀ ልማት እና በሰላም ላይ ያተኮሩ የሰው ሠራሽ አስተውሎት አስተዳደርን የሚመሩ መርሆችን ለማቅረብ በማለም፥ “በኒውክሌር ዘመን የሰው ልጅ ቤተሰብ ደካማነት”፣ “ቴክኖሎጂ ለሰው ልጅ አገልግሎት” እና “የሰው ሠራሽ አስተውሎት እና የጦርነት የሞራል ተግዳሮቶች” በሚሉት ርዕሠ ጉዳዮች ላይ እንደሚወያይ ታውቋል።

የጉባኤው የመጀመሪያዎቹ ሁለት ቀናት በካስቴል ጋንዶልፎ በሚገኝ “ወዳሴ ላንተ ይሁን” የአትክልት ሥፍራ የሚካሄዱ ሲሆን፥ ሦስተኛው እና የመጨረሻው ቀን የሮም ማዘጋጃ ቤት መቀመጫ በሆነው በ “ካፒቶሊን ሂል” እንደሚካሄድ ታውቋል።

በዚህ የታሪክ ወቅት የጋራ መርሆዎች አስፈላጊነት

በቅድስት መንበር የሰው ልጅ ሁለንተናዊ ዕድገት ጽሕፈት ቤት የ “ውዳሴ ላንተ ይሁን” ከፍተኛ የትምህርት ማዕከል ልዩ ሃላፊ እና የጽሕፈት ቤቱ ምክትል ሃላፊ የሆኑት ብጹዕ ካርዲናል ፋቢዮ ባጆ ለጉባኤው ተካፋዮች ባደረጉት የመግቢያ ንግግራቸው፥ “ጉባኤያችንን የሚናካሂደው በታሪክ ውስጥ በከፍተኛ ደረጃ በሚከሰቱ የጂኦፖለቲካዊ ውጥረቶች፣ የዓለም አቀፍ ሥርዓት መበታተን እና የቴክኖሎጂ ውድድር መባባስ በተሞላበት ወቅት ነው” ሲሉ አስረድተው፥ እነዚህ ጉዳዮች በሰው ሠራሽ አስተውሎት እና በራስ ገዝ ቴክኖሎጂዎች ፈጣን ዕድገት እንዴት እንደሚታገዙ ገልጸዋል።

በዚህ ረገድ የስብሰባውን አስፈላጊነት እና በተለያዩ ዘርፎች ውስጥ ውይይትን የማስፋፋት አስፈላጊነትን አስረድተው፥ “የፈጠራ ፍጥነት ብዙውን ጊዜ ከማሰላሰያ ጊዜ በልጦ በተገኘበት በዚህ ወቅት፥ ዓለም ወደ እውነተኛ የሰው ልጅ ግቦች ዕድገት ሊመሩ የሚችሉ የጋራ መርሆዎች ያስፈልገዋል” ሲሉ አስረድተዋል።

ጉባኤውን የሚሳተፉት የዶመስ ኮሚኒስ ፋውንዴሽን ፕሬዝዳንት የሆኑት ብጹዕ ካርዲናል ሲልቫኖ ማሪያ ቶማሲ በበኩላቸው ለተሳታፊዎቹ ባደረጉት ንግግር፥ “ይህ ጉባኤ ሊከሰቱ የሚችሉ አደጋዎችን ለመተንተን ብቻ አይደለም” ሲሉ አፅንዖት ሰጥተዋል።

“ተስፋን ለማደስ፣ ውይይት እንደሚቻል ለማሳየት፣ ዛሬም ቢሆን ጥበብ ከዕውቀት ጋር አብሮ ሊሄድ እንደሚችል፣ የሰው ልጅ የራሱን የወደፊት ሕይወት የማስተዳደር አቅም እንዳላጣ ለማሳየት ተሰብስቧል” ሲሉ ተናግረዋል።

የሰው ልጅ በራሱ ዕጣ ፈንታ ላይ ታይቶ የማይታወቅ ኃይል በመጣበት በዚህ ወቅት፥ ኅሊና ያላቸው የወደፊት ትውልዶች ወንዶች እና ሴቶች ከግጭት ይልቅ ትብብርን፣ ከፍርሃት ይልቅ ውይይትን እና ወደኋላ ከማለት ይልቅ ተስፋን እንደመረጡ መናገር እንዲችሉ” በማለት አጥብቀው ተናግረዋል።

ሰው ሠራሽ አስተውሎትን የማስተዳደር አስፈላጊነት

የጉባኤው የመጀመሪያ ውይይት ያተኮረው፥ እንደ ሌሎች በርካታ ውይይቶች ሁሉ፥ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ በግንቦት ወር “የሰው ልጅ ታላቅነት” በሚል ርዕሥ ይፋ ባደረጉት ጳጳሳዊ መልዕክትን መሠረት ያደረገ ሲሆን፥ በርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ መልዕክት ላይ ጠቅለል ያለ የማብራሪያ ንግግር ያደረጉት፥ በቅድስት መንበር የምንኩስና ሕይወት ተቋማት ጽሕፈት ቤት ሃላፊ ብጹዕ ካርዲናል አንጌል ፈርናንዴዝ አርቲሜ ናቸው።

ቀጥሎም በርካታ ታዋቂ ሰዎች ወደ ውይይቱ የገቡ ሲሆን ከእነርሱም መካከል የኖቤል የሰላም ሽልማት አሸናፊ እና የኮሎምቢያ የቀድሞ ፕሬዝዳንት የነበሩት ዩዋን ማኑዌል ሳንቶስ ይገኙበታል። የርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ የሰው ሠራሽ አስተውሎት ትጥቅ የማስፈታት ጥሪን የተቀበሉት ዩዋን ማኑዌል ሳንቶስ፥ “በሰው ልጅ ላይ የተጋረጡትን ሁሉን የህልውና ስጋቶች ለመቋቋም ተስፋ ማድረግ የምንችለው በተመሳሳይ መንፈስ በመንቀሳቀስ ብቻ ነው” ሲሉ ተናግረዋል።

“ውጤታማ አስተዳደር ከሌለ የሰው ሠራሽ አስተውሎት በሰው ልጅ ክብር፣ ኃላፊነት፣ ተጠያቂነት እና በሕግ የበላይነት የሚመራ መልካም ኃይል መሆኑን ማረጋገጥ አስቸጋሪ እና የማይቻል ይሆናል” ብለዋል።

የኖቤል የሰላም ሽልማት አሸናፊ እና የባንግላዲሽ የቀድሞው ዋና አማካሪ የነበሩት ፕሮፌሰር ሙሐመድ ዩኑስ በበኩላቸው፥ በሥልጣኔ መጨረሻ እና በሚቀጥለው ጅማሬ ላይ እንዴት እየኖርን እንዳለን እና በዓለም የወደፊት ሁኔታ መቅረጽ ውስጥ ወጣቶችን በማሳተፍ አስፈላጊነት ላይ ተናግረዋል።

ውይይቱ ከተሳተፉት ሌሎች ተናጋሪዎች መካከል፥ የአምነስቲ ኢንተርናሽናል ዋና ፀሐፊ ዶ/ር አግኔስ ካላማርድ፣ የዓለም አቀፍ የደህንነት እና ሥነ-ምግባራዊ የሰው ሠራሽ አስተውሎት መሥራች እና የቦርድ አባል ዶ/ር አሚር ባኒፋቴሚ፣ የኒውክሌር ጦርነት መከላከል ዓለም አቀፍ የፊዚክስ ባለሙያዎች ተባባሪ ፕሮፌሰር እንደ ጎርጎሮሳውያኑ የ1985 ዓ. ም. የኖቤል የሰላም ሎሬት ድርጅት መሥራች ጄምስ ሙለር፣የፑግዋሽ ኮንፈረንስ ዋና ፀሐፊ ፕሮፌሰር ካረን ሆልበርግ (የኖቤል የሰላም ሎሬት ድርጅት፣ 1995)፤ እና በካሊፎርኒያ የሳንታ ባርባራ ዩኒቨርሲቲ የኖቤል ሽልማት አሸናፊ እና የቻንስለሩ ሊቀ መንበር ፕሮፌሰር ፕሮፌሰር ዴቪድ ግሮስ እንዲሁም ሌሎች ታዋቂ ባለሞያዎች ይገኙበታል።

 

15 Jul 2026, 16:57