ሊቀ ጳጳስ ጋላገር፣ በሩሲያ ውስጥ ያለችው ቤተ ክርስቲያን ድልድዮችን የምትገነባ ትሁን አሉ!
የዚህ ዝግጅት አቅራቢ መብራቱ ኃ/ጊዮርጊስ-ቫቲካን
ከሩሲያ ፌዴሬሽን የካቶሊክ ማህበረሰብ ቀሳውስት፣ ገዳማዊያን/ዊያት ጋር የተገናኙት ሊቀ ጳጳስ ፖል ሪቻርድ ጋላገር “ብዙውን ጊዜ በአስቸጋሪ ሁኔታዎች ውስጥ” የሐዋርያዊ እንክብካቤ፣ የትምህርት እና የበጎ አድራጎት አገልግሎታቸውን ለሚያከናውኑት ታማኝነት እንዲሁም ከሌሎች ክርስቲያኖች ጋር የቤተ ክርስቲያን ኅብረት እና ውይይትን ለማስተዋወቅ ላሳዩት ቁርጠኝነት ምስጋናቸውን ገልጸዋል።
በጥልቅ ፍቅር እና ጓደኝነት ድባብ ውስጥ አቀባበል የተደረገላቸው ሊቀ ጳጳስ ጋላገር “የሊቀ ጳጳስ ሊዮ 14ኛ የፍቅር ሰላምታ” ለካህናትና ለገዳማዊያን/ዊያት ማህበረሰብ በማስተላለፍ ነበር በወቅቱ ባደረጉት ንግግር የገለጹት።
ሁለተኛው የቫቲካን ጉባኤ በቤተ ክርስቲያኗ ሕይወት እምብርት ላይ በጥብቅ ያስቀመጠውን በጥምቀት አማካኝነት የሚደረገውን የቅድስና ጥሪ በማስታወስ፣ ሊቀ ጳጳሱ በእያንዳንዱ ሰው ጥሪ አማካኝነት የቅድስና ጥሪ “ሁሉም ሰው የተጠራበት” በሆነው የበጎ አድራጎት ሙላት ውስጥ እንዴት እንደሚገለጽ አብራርተዋል።
ቤተ ክርስቲያኒቱ የምታድገው እና የምትገነባው በእውነተኛ ምስክሮች አማካኝነት ነው፣ በቦታው ያሉትን “አንድ የተወሰነ ኃላፊነት ተሰጥቷችኋል፡ የምታውጁትን ወንጌል በሕይወታችሁ እንዲታይ ማድረግ” ነው ብለዋል።
“ኅብረት እና አንድነት በሚነግሥበት” ሊቀ ጳጳስ ጋላገር አፅንዖት ሰጥተው እንደ ተናገሩት፣ “ምስክሮች ተዓማኒ እና ፍሬያማ ይሆናሉ” ሲሉ ተናግረዋል።
የሐዋርያዊ እንክብካቤ እና በጎ አድራጎት
ለካህናት እና ገዳማዊያን/ዊያት ሲናገሩ የሐዋርያዊ አገልግሎት ቁርጠኝነት አስፈላጊነትን በመጥቀስ፣ ሊቀ ጳጳስ ጋላገር የቀድሞ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በአዚዚ “ከሕዝቡ ጋር ‘አንዳንድ ጊዜ ከፊት፣ አንዳንድ ጊዜ መሃል እና አንዳንድ ጊዜ ከኋላ’ መራመድ - ከፊት ለመምራት፣ በመሃል ለመደገፍ፣ ከኋላ ማንንም ላለመተው፤ ነገር ግን ከሁሉም በላይ አብረው ለመራመድ፣ እርስ በርስ ለመረዳዳት፣ ይቅርታን እንዴት መጠየቅ እና ይቅር ማለት እንደሚቻል ለማወቅ” አብሮ መጓዝ አስፈላጊ መሆኑን መናገራቸውን አስታውሰዋል።
የውይይት ተግዳሮት
የቤተ ክርስቲያኗ ቁርጠኝነት፣ ሊቀ ጳጳሱ እንደጠቀሱት፣ “ከሌሎች አብያተ ክርስቲያናት እና ከክርስቲያን የቤተ ክርስቲያን ማህበረሰቦች፣ ከሌሎች ሃይማኖቶች እና መንገዳችንን የማይጋሩ” ጋር የውይይት መንገዶችን በመገንባት አስፈላጊ እንደ ሆነም ተናግረዋል።
የርዕሰ ሊቀ ጳጳስ ሊዮ 14ኛን በላቲን ቋንቋ "Magnifica humanitas" (ሰብዓዊ ታላቅነት) እና አሁንም በላቲን ቋንቋ " In Illo uno unum" (አንድ በሆነው በእርሱ ሁላችንም አንድ ነን) በተሰኘው የጵጵስና ዘመናቸው መሪ ቃል በመጥቀስ፣ ሊቀ ጳጳስ ጋላገር “የራስን ማንነት ሳይተው፣ ነገር ግን ለእውነት እና በሌላው ውስጥ ላሉት ስጦታዎች በአክብሮት በመክፈት” ውይይት መደረግ እንዳለበት አፅንዖት ሰጥተው ተናግረዋል።
ለሰላም ድልድዮችን መገንባት
በመጨረሻም፣ ቤተ ክርስቲያኗ የሰላም ፈጣሪ እና የድልድዮች ገንቢ እንድትሆን ተጠርታለች ያሉት ሊቀ ጳጳስ ጋላገር ይህ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ ራሳቸው ለቤተ ክርስቲያኗ አደራ የሰጡት ተልእኮ ሲሆን “የጦር መሣርያ ትጥቅን መፍታት፣ የኃይል ወይም የጦር መሳሪያ የማይጠቀም የአኗኗር ዘይቤ እና ግጭቶችን የመፍታት መንገድ፣ ይልቁንም የተናደዱትን ሰዎች ልብን የሚያለሰልስ እና በፍቅር፣ በትህትና እና በውይይት የመዋጋት ፍላጎትን የሚያስወግድ መንገድ መከተል፣ ትሑት እና ጽናት ያለው ማሕበረሰብ” መፍጠር ይገባል ሲሉ ተናግረዋል።
“ድልድይ መገንባት ማለት በሁለት ዳርቻዎች መካከል ያለውን ርቀት ማወቅ ማለት ነው - መለያየት፣ ጥላቻ እና አለመግባባት - እና ይህ ርቀት የማይሻር መሆኑን መቀበል አለመቻል ማለት ነው” ሲሉ ሊቀ ጳጳስ ጋላገር ተናግረዋል።
ከዚያም አገረስብከቱን የእግዚአብሔር እናት አማላጅነት ጥበቃ ሲር እንዲሆን የተማጸኑት ሊቀ ጳጳስ ጋላገር “ፍቅር፣ ፍትህና ሰላም የሚነግስበት ዓለም ለመገንባት አስተዋጽኦ እንድናደርግ ጸጋን ትሰጠን ዘንድ” እንማጸናት ብለዋል።
የምድር ጨው ስለመሆናቸው
በጥልቅ ጸሎት እና በስሜት ድባብ ውስጥ፣ ሊቀ ጳጳስ ጋላገር ስብከታቸውን የጀመሩት “በሩሲያ ፌዴሬሽን ውስጥ የካቶሊክ ማህበረሰብን በእምነት ጉዞ ላይ የበለጠ ጉጉት እንዲቀጥሉ” ማበረታቻ በመስጠት ነበር።
ከዚያም ወደ ሰላም ግንባታ ጭብጥ ተመለሱ።
“እዚህ ከእናንተ ጋር፣ በዚህ ክቡር በዓል ዓለም አቀፋዊቷን ቤተ ክርስቲያን ተወክላለች፣ ከተለያዩ አገሮች፣ ባህሎች እና ታሪኮች የመጣን ነን፣ ሆኖም እዚህ በሞስኮ ልብ ውስጥ እንደ አንድ ቤተሰብ ተሰብስበናል፣ በእግዚአብሔር ላይ በተመሳሳይ እምነት አንድ ሆነን ተስብስበናል” ሲሉ ሊቀ ጳጳስ ፖል ሪቻርድ ጋላገር ተናግረዋል።
የውይይት እና የሰላም መንገድ
"ወንጌልን መኖር እንዲሁም በዋናው የውይይት እና የሰላም መንገድ ላይ ለጋራ ጥቅም አብሮ መጓዝ ማለት ነው" ያሉት ሊቀ ጳጳሱ በጉድጓዱ አጠገብ ኢየሱስ ከሳምራዊቷ ሴት ጋር ያደረገውን ውይይት በማስታወስ፣ "ማንነታችንን የሚያጠፋ ስምምነት አይደለም፣ ነገር ግን የልብ መጋጠሚያ ነው" ብለዋል።
ወንጌል፣ አንድ የሚያደርገንን ነገር ያለማቋረጥ እንድንፈልግ ያሳስበናል።
"ማህበራዊ ትብብራችን፣ ለድሆች፣ ለታመሙ፣ ለጠፉት እና ለሚሰቃዩት የምናቀርበው አገልግሎት እምነታችን ወሰን አያውቅም" ያሉት ሊቀ ጳጳሱ በዚህ መንገድ፣ የሊቀ ጳጳስ ሊዮ 14ኛ ግብዣ፣ እንዳስታወሱት፣ "በዕለት ተዕለት ሕይወታችን እውነተኛ የሰላም የእጅ ጥበብ ባለሙያዎች እንድንሆን"፣ "የውይይት እና የመግባባት ድልድዮችን በመገንባት፣ ልብን በማስታረቅ እና ቁስሎችን በመፈወስ" ልናገለግል ይገባል ብለዋል።