ብጹዕ ካርዲናል ፓሮሊን በዓለም ዙሪያ የሚሰደዱ ክርስቲያኖችን በጸሎት አስታወሱ
የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን
ብጹዕ ካርዲናል ፓሮሊን ነሐሴ 11/2018 ዓ. ም. ምሽት በቅድስት አጋታ የኢዮቤልዩ ዓመት ፍጻሜ ላይ የቀረበውን መስዋዕተ ቅዳሴ የመሩ ሲሆን፥ መታሰቢያነቱም የቅድስት አጋታ አጽም ከቁስጥንጥንያ ወደ ጣሊያን ካታኒያ ግዛት የመጣበት ዘጠኝ መቶኛ ዓመት ለማክበር እንደሆነ ታውቋል።
ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ በዓሉን ለማክበር በሲሲሊ ከተማ የተሰበስቡ ምዕመናንን በመንፈስ በቀላቀል የላኩትን ቡራኬ እና የአንድነት መልዕክት አድርሰው፥ “ይህን የኢዮቤልዩ ዓመት ማክበር ማለት እግዚአብሔር በዘመናት ሁሉ ለቤተ ክርስቲያኑ ታማኝ መሆኑን፣ በፈተና ጊዜ መደገፉን፣ ከችግር ነጻ ማውጣቱን እና በቅዱሳን ምስክርነት ያለማቋረጥ እንዳበበች ማወቅ ማለት ነው” ሲሉ ብጹዕነታቸው አፅንዖት ሰጥተዋል።
የቅድስት መንበር ዋና ጸሐፊ ብጹዕ ካርዲናል ፒየትሮ ፓሮሊን በዕለቱ ባሰሙት ቃለ ምዕዳን፥ “በዓለም ዙሪያ በተለያዩ አካባቢዎች ተበታትነው የሚገኙ እና ለእግዚአብሔር እና ለወንጌሉ ሲሉ ስደት የሚደርስባቸውን በርካታ ወንድሞች እና እህቶች በጸሎት ማስታወስ እንደሚገባ አሳስበዋል።
ሙዚየሞች ውስጥ የማይገባ ቅድስና
“ቅድስት አጋታ በካታኒያ ታሪክ ውስጥ ብቻ የምትጠቀስ ሳትሆን ከዛሬው የእግዚአብሔር ሕዝብ ጋር መጓዟ ቀጥላለች” ብለዋል። ቅዱስ አጎስጢናስን እና ቅዱስ ቴርቱሊያንን የጠቀሱት ብጹዕነታቸው፥ እነዚህ ቅዱሳን ሊመሰገኑ የሚገባው በሥቃያቸው ሳይሆን ሕይወትን በጽናት በመኖራቸው መሆኑን በማስረዳት የሰማዕታትን አስፈላጊነት አስታውሰዋል። የሂፖ ቅዱስ እና የክርስትና እምነት ተሟጋች የነበረው ቅዱስ አጎስጢኖስ “የሰማዕታት ደም የሽንፈት ምልክት ሳይሆን ቤተ ክርስቲያን ያለማቋረጥ እንደገና የምታብብበት ዘር ነው” ማለቱን አስታውሰዋል።
“የቅድስት አጋታ ቅድስና በሙዚየሞች ውስጥ የሚቀመጥ ሳይሆን ነገር ግን እምነትን፣ ተስፋን እና ምጽዋትን የሚያመነጭ፣ በዛሬው ዓለም እምነትን ማነሳሳት የሚችል አድርገን መውሰድ ይገባል” ብለዋል።
እግዚአብሔር ዘወትር ታማኝ ሆኖ ይኖራል
በመስዋዕት ቅዳሴው ላይ በተነበቡት የዕለቱ ምንባባት ላይ በማስተንተን ባሰሙት ቃለ-ምዕዳን፥ የኢየሱስ ክርስቶስ መሆን ከማንኛውም ፈተና በላይ መሆኑን በአፅንዖት ተናግረው፥ ይህም በቅድስት አጋታ ሕይወት በግልጽ መታየቱን፣ “ሰማዕትነቷ ከሁሉ በፊት የዓመፅ ታሪክ ሳይሆን ምንም ዓይነት ዓመፅ ሊያጠፋው ያልቻለው የፍቅር መገለጫ ነው” ብለው፥ የተሳሳተ ግንዛቤ የነበረው፣ ስደት እና አቅመ ቢስነት ያጋጠመው ሐዋርያው ጳውሎስ ስለ ኢየሱስ ክርስቶስ በሚያስደንቅ ሁኔታ መመስከር መቀጠሉን አስታውሰዋል።
ኃይል የእግዚአብሔር እንጂ የሰው አይደለም
በአስተንትኖአቸው ቤተ ክርስቲያንን ያስታወሱት ብጹዕ ካርዲናል ፓሮሊን፥ “ቤተ ክርስቲያን በእግዚአብሔር ጸጋ እንጂ በራሷ ጥረት የምትኖር ወይም በአባሎቿ ችሎታ የተመሠረተች አይደለችም” ብለው፥ ሥራውን በሰዎች ድክመት ውስጥ መሥራት በቀጠለው በእግዚአብሔር ታማኝነት ላይ የተመሠረተች ናት” ሲሉ አስገንዝበዋል።
በቅዱሳት መጻሕፍት ውስጥ የተጠቀሱ ጥሪዎችን ያስታወሱት ብጹዕነታቸው፥ ‘አትፍሩ!’ የሚለው የሥነ-ልቦና ማበረታቻ ብቻ ሳይሆን የክርስትና ሕይወታችን መሠረት መሆኑን አስረድተው፥ “ኢየሱስ ክርስቶስ ከፈተና እና ከመከራ የሚበልጥ ነገር ሊሰጠን ቃል ገብቷል” ብለዋል።
በብዙ የዓለማችን ክፍሎች በስደት እና መከራ ውስጥ ለሚገኙት ክርስቲያኖች ትኩረት የሰጡት ብጹዕነታቸው፥ “በዚህ ቅጽበት በዓለም ዙሪያ በተለያዩ ክፍሎች ተበታትነው የሚገኙትን፣ ለእግዚአብሔር እና ለወንጌሉ ሲሉ ስደት እና መከራ የሚደርስባቸውን ወንድሞቻችን እና እህቶቻችን በጸሎት እናስታውሳቸው” ብለው፥ የደም መፍሰስ ለሌለበት ሰማዕትነትም መጠራታችንን አንዘንጋ” ሲሉ አክለዋል።
የየቀኑ ቅድስና እና የታማኝነት ሰማዕትነት
“ለኢየሱስ ክርስቶስ ያለንን ፍቅር ያለ ቅድመ ሁኔታ የምንገልጽባቸው ሁለት መንገዶች አሉ” ያሉት ብጹዕ ካርዲናል ፓሮሊን፥ እነዚህም የደም መስዋዕትነት የሚከፈልበት ሰማዕትነት እና እያንዳንዱ ሰው በዕለታዊ ሕይወቱ ውስጥ ሊያገኘው የሚችለው የታማኝነት ሰማዕትነት ናቸው” ሲሉ አስረድተዋል።
በችግር መካከል ፍቅራቸውን በታማኝነት የሚጠብቁ ባለትዳሮችን፣ ልጆቻቸውን በክርስትና እምነት ለማሳደግ የሚጥሩ ወላጆችን፣ ለብልጭልጭ ባህል መገዛት የማይፈልጉ ወጣቶችን፤ ሕይወታቸውን በልግስና የሚሰጡ ገዳማውያንን እና ገዳማውያትን፣ መከራቸውን ለእግዚአብሔ በአደራ የሚሰጡ አረጋውያንን እና በጥቅም ላይ ከመደራደር ይልቅ ፍትህን፣ ከምቾት ይልቅ እውነትን እና ከበቀል ይልቅ ይቅርታን የሚመርጡትን በምሳሌነት ጠቅሰው፥ እነዚህ በሙሉ ሁለተኛው የቫቲካን ጉባኤ የተናገራቸው የዕለት ተዕለት ቅድስና መሆናቸውን አጥብቀው ተናግረዋል።
ክፋት በክፋት አይሸነፍም
የቅድስት መንበር ዋና ጸሐፊ ብጹዕ ካርዲናል ፓሮሊን በማጠቃለያቸው፥ ካታኒያ እጅግ ብዙ የእምነት፣ የባህል፣ የጋራ አምልኮ እና የበጎ አድራጎት ቅርስ እንዳላት አስታውሰው፥ ነገር ግን ይህ ቅርስ ሳይባክን ፍሬ ማፍራት እንዳለበት አሳስበዋል።
“ክፋት በክፋት ሳይሆን ታሪክን በሚቀይረው፣ ከቅዱስ መስቀል በተገኘው በጎ አድራጎት እና የቅዱሳንን ትምህርት በመከተል በርካታ አካባቢያዊ ተግዳሮቶችን፣ ድህነትን፣ የኑሮ አለመመጣጠንን፣ ወጣቶች ዕጣ ፈንታቸውን በሌላ አካባቢ እንዲፈልጉ የሚገደዱበትን ሁኔታ፣ ቤተሰቦች የሚያጋጥሟቸውን ትግል እና አዳዲስ ቁሳዊ እና መንፈሳዊ ድህነትን መጋፈጥ ይቻላል” ብለዋል።