ፈልግ

በዓለም ጤና ድርጅት የሚመራው የዶክተሮች ቡድን በጋዛ የሚገኘውን አል ሺፋ ሆስፒታልን ሲጎበኝ በዓለም ጤና ድርጅት የሚመራው የዶክተሮች ቡድን በጋዛ የሚገኘውን አል ሺፋ ሆስፒታልን ሲጎበኝ 

የጋዛ ሆስፒታል 'የሞት ቀጠና' እንደሚመስል ተነገረ

በጋዛ የሚገኘውን አል ሺፋ ሆስፒታልን የጎበኙት ዓለም አቀፍ ዶክተሮች እንደገለፁት እስራኤል በህንፃው ላይ ያደረሰችውን ጥቃት ተከትሎ ሆስፒታሉ አሁን ላይ 'የሞት ቀጠና' ይመስላል ብለዋል።

  አቅራቢ ዘላለም ኃይሉ ፥ አዲስ አበባ

በጋዛ የሚገኘውን አል ሺፋ ሆስፒታልን የጎበኙት ዓለም አቀፍ ዶክተሮች እንደተናገሩት ሆስፒታሉ ወደ 'የሞት ቀጠናነት' ተቀይሯል ብለዋል። የእስራኤል ሃይሎች ሃማስ ለወታደራዊ ዘመቻዎች እንደ ጦር ሰፈርነት እየተጠቀመበት ነው በማለት ባለፈው ሳምንት ወደ ሆስፒታሉ ግቢ ገብተዋል።

አሁን ግን የቦምብ ጥቃቱ ባደረሳቸው ውድመቶች እና ጠባሳዎች፣ እንዲሁም ከመግቢያው አጠገብ ከሚገኘው የጅምላ መቃብር ምክንያት የአል ሺፋ ሆስፒታል ትርምስምሱ ወጥቶ ይታያል።

በዓለም ጤና ድርጅት የሚመራው የሕክምና ቡድን እንደገለፀው ባለፈው ቅዳሜ ከተደረገው ሰዎችን ከሆስፒታሉ የማስወጣት ተግባር በኋላ አሁንም 25 የጤና ባለሙያዎች እና 300 ታካሚዎች በተቋሙ ውስጥ እንደቀሩ ተነግሯል። አንዳንዶቹ በአንቲባዮቲክ መድሃኒቶች እጥረት ምክንያት ቶሎ መዳን ይችሉ የነበሩ ቁስሎቻቸው የከፋ ደረጃ ላይ እንደደረሰ ለማረጋገጥም ችለዋል።

የእስራኤሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ከፍተኛ አማካሪ የሆኑት ማርክ ሬጅቭ ሆስፒታሉ ውስጥ ለተከሰተው ሁኔታ ሃማስን ተጠያቂ አድርገዋል። 'በእርግጥ በሆስፒታሉ ውስጥ ያሉት ሁኔታዎች በጣም አስቸጋሪ ናቸው፥ ይህም የሆነው ሃማስ ሆን ብሎ ሆስፒታሉን የጦር ቀጠና ስላደረገው ነው’ በማለት ሃማስን ከሰዋል።

በማዕከላዊ እና በደቡባዊ ጋዛ የተካሄደው የአየር ድብደባ

ይህ በእንዲህ እንዳለ እስራኤል በማዕከላዊ እና በደቡባዊ ጋዛ ተጨማሪ የአየር ጥቃቶችን አድርሳለች። የዜና ዘገባዎች እንደገለፁት ከሆነ በጥቃቱ 13 ሰዎች ተገድለዋል።

በሌላ ዜና፥ የኳታር ጠቅላይ ሚኒስትር እንደተናገሩት ታጋቾችን የመልቀቅ ስምምነት ላይ “በጣም ጥቃቅን” መሰናክሎች ብቻ እንደሚቀሩ እና እነዚህም በዋናነት የአተገባበር እና የሎጂስቲክስ ጉዳዮች እንደሆኑ ገልፀዋል።

ዋሽንግተን ፖስት እንደዘገበው እስራኤል፣ ሃማስ እና አሜሪካ አንዳንድ ታጋቾች እንደሚለቀቁ መስማማታቸውን እና በምላሹም ሁለቱም ወገኖች ለአፍታ ተኩስ እንደሚያቆሙ ተነግሯል።

መስከረም 26/2016 ዓ.ም. ሃማስ በእስራኤል ላይ በፈጸመው የመጀመሪያ ጥቃት ከ1,400 በላይ ሰዎች የተገደሉ ሲሆን፥ እስራኤል ከ220 በላይ ሰዎች አሁንም ድረስ በጋዛ ታግተው እንደሚገኙ ትናገራለች።
እስራኤላውያን በጋዛ ላይ ጥቃት መፈጸም ከጀመሩበት ቀን ጀምሮ እስከ አሁን 12,300 የሚገመቱ ሰዎች እንደተገደሉ ተነግሯል። 
 

20 Nov 2023, 15:26