ፈልግ

በሰሜን ጋዛ ፍንዳታ ከተከሰተ በኋላ የተነሳ እሳት ከደቡብ እስራኤል ሆኖ ሲታይ በሰሜን ጋዛ ፍንዳታ ከተከሰተ በኋላ የተነሳ እሳት ከደቡብ እስራኤል ሆኖ ሲታይ 

የመጀመሪያዎቹ እስራኤላኢያን ታጋቾች አርብ ከሰዓት በኋላ ሊለቀቁ እንደሆነ ተነገረ

በቅድስት ሀገር እየተካሄደ ያለው ጦርነት በኳታር አሸማጋይነት ሐሙስ ዕለት ሊጀመር የነበረው ጊዜያዊ የሰብዓዊ የተኩስ አቁም ፋታ ወደ አርብ ዕለት መዛወሩን ኳታር ገልፃለች።

  አቅራቢ ዘላለም ኃይሉ ፥ አዲስ አበባ

በሐማስ እና በእስራኤል መካከል በተደረሰ ጊዜያዊ የተኩስ አቁም ስምምነት መሰረት ለአራት ቀናት የሚቆየው የተኩስ አቁም ፋታ ከመጀመሩ ከጥቂት ሰዓታት በፊት የእስራኤል መከላከያ ባወጣው መግለጫ "ጦርነቱ አላበቃም " ሲል በጋዛ የሚኖሩ ፍልስጤማውያንን አስጠንቅቋል። 

በኳታር፣ በአሜሪካ እና በግብፅ አስተባባሪነት የተደረገው ስምምነቱ ረቡዕ ዕለት ይፋ የተደረገ ሲሆን፥ ሃማስ በእስራኤል ላይ ባደረገው ወረራ ታግተው የነበሩ በደርዘን የሚቆጠሩ ሰዎችን ለመልቀቅ እና ጋዛ ውስጥ ለሚገኙ በጦርነቱ ለደከሙት ፍልስጤማውያን እፎይታን ለማምጣት ያለመ ነው ተብሏል።

የተኩስ አቁም ፋታው ከመጀመሩ በፊት ባሉት 20 እና 30 ደቂቃዎችም የመጨረሻዎቹ የአየር ጥቃቶችም ተፈጽመዋል። ለሰባት ሳምንታት ያህል የማያባራ ጥቃት በጋዛ ላይ የፈጸመው የእስራኤል መከላከያም ፋታው እስኪጀመር እስከ መጨረሻዋ ሰዓትም ድረስ ጥቃቱን አላቆመም ነበር።

ኳታር ስምምነቱ ተግባራዊ እንዲሆን ከታቀደበት ከአንድ ቀን በኋላ ህዳር 14 ቀን 2016 ዓ.ም. ዕለተ አርብ ላይ ተግባራዊ እንደሚሆን አስታውቃለች። በስምምነቱም በእስራኤል የተያዙ የፍልስጤም እስረኞችም እንደሚፈቱ ለማወቅ ተችሏል።

ታጋቾች 10 ሰዓት ላይ ይለቀቃሉ

የኳታር የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ ማጂድ አል-አንሷሪ እንደተናገሩት ኳታር አንዳንድ የፍልስጤም እስረኞችን እስራኤል እንደምትፈታ አረጋግጠዋል። ሃማስም በበኩሉ ታጋቾችን ዕለተ አርብ ከሰዓት በኋላ 10 ሰዓት ላይ እንደሚፈታ የተናገሩ ሲሆን፥ በስምምነቱ መሰረት ሐማስ 50 ታጋቾችን እንዲሁም እስራኤል 150 የፍልስጤም እስረኞችን በአራት ቀናት እንደሚለቁ ተገልጿል።

ዛሬ ከሰዓት በኋላ የሚለቀቁት ሁሉም ታጋቾች ሴቶች እና ህጻናት መሆናቸውን ገልፀው፥ የአንድ ቤተሰብ አባላት የሆኑ ታጋቾች በአንድ ቡድን ሆነው እንደሚፈቱም ተናግረዋል።

ኳታር በተቻለ መጠን ጊዜያዊ የሰብዓዊ የተኩስ አቁም ፋታ ስምምነቱ ከሚጀመርበት ሰዓት ጀምሮ ዕርዳታ ወደ ጋዛ መግባት እንደሚጀምር ተስፋ አደርጋለሁ ካለች በኋላ፥ “በጋዛ ውስጥ ካለው ከፍተኛ ፍላጎት አንፃር ይህ ጥቂቱ የዕርዳታ አቅርቦት ይሆናል” ብለዋል።

በእውነቱ፥ የተኩስ አቁም ስምምነቱ ለታገች ቤተሰቦች የተስፋ ጭላንጭል ያመጣ ቢሆንም፥ ‘የተባበሩት መንግስታት የእርዳታ ፈንድ ለፍልስጤም ስደተኞች’ የተባለው ተቋም እንደገለፀው ይህ የአራት ቀን የተኩስ አቁም ፋታ ዕርዳታን ወደ ክልሉ በሚፈለገው መጠን ለማስገባት በቂ እንዳልሆነ አስጠንቅቋል።

ሂዝቦላህ

ይህ በእንዲህ እንዳለ ሂዝቦላህ የተባለው የሊባኖስ ታጣቂ ቡድን በሰሜን እስራኤል በሚገኙ ወታደራዊ ጣቢያዎች ላይ ከ50 በላይ ሮኬቶችን በመተኮሱ የእስራኤል የአየር ሃይል በደቡባዊ ሊባኖስ በሚገኝ መኖሪያ ቤት ላይ ባካሄደው ጥቃት አምስት የቡድኑን ከፍተኛ ተዋጊዎችን እንደገደለ ተነግሯል።

ታጣቂ ቡድኑ መስከረም 27 በእስራኤል-ሀማስ ጦርነት መጀመሪያ ላይ በሀገሪቱ ሰሜናዊ ክፍል ላይ የእስራኤልን ወታደራዊ ቀጠናዎች ላይ ጥቃት መውሰድ ከጀመረበት ጊዜ አንስቶ፥ ይህ በእስራኤል ድንበር ላይ የተወነጨፉት የሮኬት ማዕበሎች በጣም ከባዱ የሮኬት ድብደባ እንደሆነ ተነግሯል።

ሂዝቦላህ በእስራኤል እና በሊባኖስ ድንበር ላይ የማደርገውን እንቅስቃሴ በመጨመር በጋዛ ሰርጥ ውስጥ እስራኤል እየወሰደች ያለውን እና በከፍተኛ የአየር፣ የምድር እና የባህር ሃይል ጥቃት ከ13,000 በላይ ፍልስጤማውያን ሞትን እና ከፍተኛ ውድመት እያስከተለ ያለውን ጫና ለማቃለል እየሰራው ነው ይላል።
 

24 November 2023, 12:38